ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኤርትራ መንግሥት ካለፍርድ ለዓመታት ያሰራቸውን የክርስትና እምነት ተከታዮች ፈታ
የኤርትራ መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ ዕውቅና ከተሰጣቸው የክርስትና እምነት አብያተ ክርስቲያናት ውጪ አባል በመሆናቸው ለዓመታት ታስረው የቆዩ ወደ 98 የሚጠጉ ሰዎችን መልቀቁን ምንጮች ለቢቢሲ ተናገሩ።
መንግሥት እነዚህን ከእምነት እንቅስቃሴያቸው ጋር ለዓመታት ካለፍርድ ቤተ ውሳኔ በእስር ቤት ያቆያቸውን እስረኞች የፈታው ባለፉት ሳምንታት መሆኑን በአገር ውስጥ እና በውጪ ያሉ ገልጸዋል።
ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥት ከመካከላቸው 20 ሴቶች የሚገኙበትን 36 አማኞችን በዋስ ከእስር ለቅቋል።
ከተለቀቁት መካከል አብዛኞቹ ማይ ሰርዋ በተባለ እስር ቤት ውስጥ ከአምስት ዓመታት በላይ መደበኛ ክስ ሳይመሰረትባቸው እንዲሁም ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በእስር ላይ ቆይተዋል።
በተጨማሪም ምንጮች እንዳሉት ሌሎች 17 እስረኞች ባለፈው አርብ ከእስር ቤት እንዲወጡ ተደርገዋል።
ከሁለት ሳምንት በፊት ደግሞ ለሦስት ዓመታት ካለፍርድ በእስር ላይ የቆዩ 16 ሴቶችን ጨምሮ 26 ሰዎች ከእስር ተለቅቀዋል።
ቀደም ሲል ደግሞ 19 ሰዎች ከረን ውስጥ ከሚገኝ እስር ቤት መለቀቃቸውን ምንጮች የገለጹ ሲሆን፣ ከመካከላቸው ሦስቱ ሴቶች ናቸው።
የኤርትራ መንግሥት በሃይማኖታቸው ምክንያት ለዓመታት ያለፍርድ በእስር ላይ የቆዩትን ሰዎች የፈታበት ምክንያት ያልታወቀ ሲሆን፣ ይህንን የእስረኞችን መፈታት በተመለከተም በይፋ ያለው ነገር የለም።
የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች እንደሚሉት በርካታ በመንግሥት ያልተመዘገቡ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ካለፍርድ ሁለት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በእስር ላይ ይገኛሉ።
የሰብአዊ መብቶች ተከራካሪዎች አሁንም በመንግሥት ዕውቅና ያልተሰጣቸው የሃይማኖት ቡድኖች በርካታ ተከታዮች እና መሪዎቻቸው አሁንም በእስር ላይ እንደሚገኙ ይናገራሉ።
በኤርትራ ውስጥ በመንግሥት ዕውቅና ያላቸው አራት የእምነት ተቋማት ብቻ ናቸው። እነርሱም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን፣ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን፣ ኢቫንጄሊካል ሉተራን ቤተርክስቲያን እና የሱኒ እስልምና ናቸው።
የኤርትራ መንግሥት ዕውቅና ከሰጣቸው የሃይማኖት ተቋማት ውጪ ያሉት ቡድኖች የውጭ መንግሥታት መጠቀሚያ መሳሪያዎች ናቸው ሲል ይወነጅላቸዋል።
ስለዚህም ከአራቱ የእምነት ቡድኖች ውጪ ያሉ የሃይማኖት ቡድኖች በአገሪቱ ውስጥ ምንም ዓይነት ይፋዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ አይፈቀድላቸውም።
መንግሥት ዕውቅና የሰጣቸው የእምነት ቡድኖችም ቢሆኑ ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ሲሆን ንብረቶቻቸውም በመንግሥት ይወረሳሉ።
ቀደም ሲል የኤርትራ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የነበሯት ትምህርት ቤቶች እና የሕክምና ተቋማትን የመሳሰሉ የማኅበራዊ አገልግሎት መሥጫ ተቋማት ወደ መንግሥት ይዞታ እንዲዘዋወሩ ተደርጓል።
ከሁለት ሳምንት በፊት የኤርትራ ባለሥልጣናት ከፍርድ ቤት ውሳኔ ውጪ ከ18 ዓመታት በላይ አስረው ያቆይዋቸውን 13 ሰዎች መፍታታቸው መዘገቡ ይታወሳል።
ከእነዚህም መካከል የ69 ዓመቱ አዛውንት የቀድሞው የኦሊምፒክ ብስክሌት ተወዳዳሪ እና ነጋዴ የሆኑት ዘርዓጋብር ግብረ ሕይወት ይገኙበታል።
ይህ በርካታ እስረኞች ካለፍርድ ለዓመታት የሚታሰሩበት ማይ ሰርዋ እስር ቤት በኤርትራ ውስጥ ካሉ አስከፊ ሁኔታ ካለባቸው እስር ቤቶች አንዱ መሆኑ ይነገራል።
የፕሬዝዳንት ኢሳያስ መንግሥት የሃይማኖት ነጻነትን ማፈንን ጨምሮ ገደብ በሌለው የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት እና በሌሎች የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በተደጋጋሚ ክስ ሲቀርብበት ቆይቷል።
ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተለይታ ነጻ አገር ከሆነች ከ30 ዓመታት በላይ የሆናት ሲሆን፣ አገሪቱ የምትተዳደርበት ሕገ መንግሥት የሕዝብ ምክር ቤት የላትም።
ምርጫ አካሂዳ የማታውቀው ኤርትራ የነጻነት ትግሉን የመሩት ኢሳያስ አፈወርቂ ለ35 ዓመታት ገደማ አገሪቱን በፕሬዝዳንትነት እየመሩ ይገኛሉ።