ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የጦር መሣሪያ ክምችት መሟጠጥ የኢራን ግጭት ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል?
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸው "የማያልቅ ወሳኝ የጦር መሳሪያዎች አቅርቦት" እንዳሏት ተናግረዋል። የኢራን የመከላከያ ሚኒስቴር በበኩላቸው አሜሪካ ካቀደችው በላይ "ጠላትን የመቋቋም አቅም" አለን ብለዋል።
የጦር መሣሪያዎች ክምችት እና አቅርቦት ብቻው የግጭቶችን ውጤት አይወስኑም። በሩሲያ በሁለቱም ረገድ የምትበለጠው ዩክሬን ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነች። ይህም ቢሆን ግን የጦር መሣሪያ ክምችት በጦርነት ውስጥ ወሳኝ መሆኑ የሚካድ አይደለም።
የዘመቻው ፍጥነት ከመጀመሪያው ጀምሮ ከፍተኛ ነበር። ሁለቱም ወገኖች ከሚያመርቱት በላይ መሣሪያዎችን በፍጥነት እየተጠቀሙ ይገኛሉ።
በቴል አቪቭ የሚገኘው የብሔራዊ ደህንነት ጥናት ተቋም (አይኤንኤስኤስ) አሜሪካ እና እስራኤል ከሁለት ሺህ በላይ ጥቃቶችን ፈጽመዋል ሲል ግምቱን አስቀምጧል። እያንዳንዱ ጥቃት በርካታ ጥይቶችን የሚይዝ ነው።
ኢራን 571 ሚሳኤሎችን እና 1 ሺህ 391 ድሮኖችን አስወንጭፋለች ብሏል አይኤንኤስኤስ። ብዙዎቹ ጉዳት ሳያደርሱ መከላከል ተችሏል።
ሁለቱም ወገኖች ጦርነቱ በቀጠለ ቁጥር አሁን ባለው አቅም ለመቀጠል አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል።
ኢራን
የምዕራባውያን ባለሥልጣናት ኢራን የምትተኮሰው ሚሳኤል ቁጥር መቀነሷን እየገለጹ ነው። በጦርነቱ የመጀመሪያ ቀናት በመቶዎች የሚቆጠሩት ሚሳኤሎች ይተኮሱ የነበረ ቢሆንም አሁን ቁጥራቸው በጥቂት ደርዘኖች ተገድቧል።
ከጦርነቱ በፊት ኢራን ከ2 ሺህ በላይ የአጭር ርቀት ባላስቲክ ሚሳኤሎች ክምችት እንዳላት ተገምቷል። ምን ያህል የጦር መሣሪያዎች በእጃቸው ላይ እንዳለ ግን በትክክል አይታወቅም። እነዚህ አሃዞች በይፋ ከታወቁ ለባላንጣዎች ጥሩ ግብዓት ስለሚሆኑ ነው የማይገለጹት።
የአሜሪካ ጦር ከፍተኛ አዛዥ ጀነራል ዳን ኬይን ረቡዕ ዕለት እንደተናገሩት ኢራን የምታስወነጭፈው የባለስቲክ ሚሳዔል ከመጀመሪያው ቀን በ86 በመቶ ቀንሰዋል። የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) በበኩሉ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ብቻ በ23 በመቶ ቀንሰዋል ብለዋል።
ኢራን ከጦርነቱ መጀመር በፊት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሻህድ የተሰኙ አጥፍቶ ጠፊ ድሮኖችን በብዛት እንዳመረተች ይታመናል። ቴክኖሎጂውን ወደ ሩሲያም ልካለች። ሩሲያ ቴክኖሎጂውን ተጠቅማ የራሷን የሻሄድ ድሮን በማምረት ዩክሬን ውስጥ አስከፊ ጥቃት ለመፈጸም እየተጠቀመችበት ነው። አሜሪካም ዲዛይኑን ተጠቅማ ድሮኖችን አምርታለች።
ኬይን ግን የኢራን የድሮን ማስወንጨፍ አቅም ከግጭቱ የመጀመሪያ ቀን በ73 በመቶ ቀንሷል ብለዋል። ኢራን ከፍተኛ የሆነው ዘመቻ ተቋቁማ ለመቀጠል እየታገለች ያለች ይመስላል።
ቁጥሩን ለመቀነስ የተወሰነው የጦር መሣሪያ ክምችቶችን ለመጠበቅ የሚደረግ ሙከራ አካል ሊሆን ቢችልም በበቂ እያጠቁ መቀጠል ግን በለጠ ከባድ ይሆናል።
የአሜሪካ እና የእስራኤል ጄቶች በኢራን የአየር ክልል ላይ የበላይነት ይዘዋል። አብዛኛዎቹ የኢራን የአየር መከላከያዎች ወድመዋል። አሁን አስተማማኝ የሚባል የአየር ኃይልም የላትም። እንደ ሴንትኮም ገለጻ የጦርነቱ ቀጣዩ ምዕራፍ የኢራንን የሚሳኤል እና የድሮን ማስወንጨፊያዎችን፣ የጦር መሣሪያ ክምችትን ማደን እና የጦር መሣሪያ ፋብሪካዎችን በማውደም ላይ ያተኮረ ይሆናል።
አሜሪካ እና እስራኤል የኢራንን የመዋጋት አቅም ማዳከም ቀላል ሊሆንላቸው ይችላል። ሁሉንም የጦር መሳሪያ ክምችቶቿን ማጥፋት ግን አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል።
ኢራን ከፈረንሳይ በሦስት እጥፍ የምትበልጥ አገር ነች። ይህም የጦር መሳሪያዎቿን ከአየር ጥቃት ደብቆ ለማቆየት ያስችላታል።
የቅርብ ጊዜ ታሪክ የሚያሳየውም በአየር ጥቃት የሚካሄዱ ጦርነቶች ውስንነት እንዳለበት ነው።
የእስራኤል ጦር ለሦስት ዓመታት ከፍተኛ የቦምብ ድብደባ ከፈጸመ በኋላም በጋዛ የሚገኘውን ሐማስን ማውደም አልቻለም። በየመን የሚገኙት የሁቲ አማጽያን ለአንድ ዓመት ያህል በአሜሪካ የአየር ጥቃት ቢፈጸምባቸውም መቋቋም ችለዋል። አንዳንድ የጦር መሣሪያዎቻቸውን አትርፈዋል።
አሜሪካ
አሜሪካ በዓለም ላይ ቀዳሚው የጦር ኃይል ባለቤት ናት። የጦር መሣሪያ ክምችቶቿም ከየትኛውም አገር የሚልቁ ናቸው።
የአሜሪካ ጦር ኃይል አሁንም የሚተማመነው በተወሰነ መጠን በሚመረቱ ውድ የጦር መሳሪያዎች ላይ ነው። ዶናልድ ትራምፕ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ላይ ከጦር መሣሪያ አምራቾች ምርታቸውን እንዲጨምሩ ጫና ለመፍጠር ስብሰባ እንደጠሩ ተዘግቧል። ይህ ደግሞ የአሜሪካ የጦር መሣሪያ ክምችት ጭምር ሊመናመን እንደሚችል አመላካች ነው።
የኢራን ጦር በመዳከሙ አሜሪካ አሁን ላይ ጥቃት ለመሰንዘር አንጻራዊ ነፃነት ስላላት አንዳንድ ጫናዎች ሊቀነሱላት ይችላሉ።
ኬይን እንዳሉት ከሆነም አሜሪካ እንደ ቶማሃውክ ክሩዝ ሚሳኤሎች ያሉ ውድ እና የተራቀቁ የረጅም ርቀት መሳሪያዎችን መጠቀም አቁማለች። የአሜሪካ አየር ኃይል አሁን ላይ ርካሽ የሚባሉ እንደ ጄዳም ያሉ ቦምቦችን እየተጠቀመ ይገኛል።
በዋሽንግተን የሚገኘው የስትራቴጂክ እና ዓለም አቀፍ ጥናቶች ማዕከል (ሲኤስአይኤስ) ባልደረባ የሆኑት የቀድሞ የአሜሪካ የባሕር ኃይል ኮሎኔል ማርክ ካንቺያን፣ መጀመሪያው ላይ በርቀት ከተደረጉት ጥቃቶች በኋላ፣ አሜሪካ "አሁን ርካሽ ሚሳኤሎችን እና ቦምቦችን መጠቀም ትችላለች" ብለዋል።
አሜሪካ ይህንን የውጊያ አካሄድ ተጠቅማ "ለዘላለም በሚባል ደረጃ" መቀጠል እንደምትችል ተናግረዋል። ጦርነቱ በቀጠለ ቁጥር የዒላማዎች ዝርዝር እየቀነሱ ስለሚሄዱ የዘመቻው ፍጥነት እየቀነሰ ይሄዳል ማለት ነው።
የአየር መከላከያ
ማርክ ካንቺያን እንደሚሉት አሜሪካ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የጄዳም ቦምቦች ባለቤት ናት። ውድ የሆነው የአየር መከላከያ ስርዓት አቅርቦት ግን አናሳ ነው። በግጭቱ የመጀመሪያ ላይ ከኢራን የሚሰነዘሩ የበቀል ጥቃቶች ለማክሸፍ የአየር መከላከያ ስርዓቶቹ ወሳኝ ነበሩ።
የፓትሪዮት ሚሳኤሎች ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። ከአሜሪካ በተጨማሪ የአረብ አጋሮቿ እና ከዩክሬን ይፈልጉታል። እያንዳንዱ ሚሳኤል 4 ሚሊዮን ዶላር ያወጣል።
አሜሪካ በዓመት ወደ 700 የሚጠጉ የፓትሪዮት ሚሳኤሎችን ታመርታለች ተብሎ ይታመናል። ኢራን የባለስቲክ ሚሳኤሎችን ማስወንጨፏን ከቀጠለች አሜሪካ ያሏትን ውስን ክምችቶች መጨረስ ትጀምራለች።
የሲኤስአይኤስ ባለሙያ ካንቺያን እንደሚሉት ከሆነ አሜሪካ 1 ሺህ 600 የሚጠጉ የፓትሪዮት ሚሳኤሎች ሊኖሯት ይችላል ሲሉ ገምተዋል። ይህ ቁጥር በቅርብ ቀናት ውስጥ ተመናምኗል።
አሜሪካ ከአየር ወደ መሬት የሚደረገውን ጦርነት "ለረጅም ጊዜ" መቀጠል እንደምትችል ቢናገሩም፣ የአየር መከላከያ ጦርነቱ "ይበልጥ አሰልቺ" ይሆናል።
"ፕሬዝዳንት ትራምፕ የፓትሪዮትን ቁጥር ለመቀነስ ፈቃደኛ ከሆኑ፣ ኢራንን የበለጠ መቋቋም እንደምንችል አስባለሁ። ይህ ግን የፓስፊክ ቀጠናን ወደ ግጭት ውስጥ የማስገባት አደጋ ይኖረዋል።"
ትራምፕ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ላይ ከአሜሪካ የጦር መሣሪያ አምራቾች ጋር ለመገናኘት መዘጋጀታቸው የጦር መሳሪያ ክምችት አደጋ እንዳለበት የሚያሳይ ምልክት ነው። የአሜሪካ የጦር ሚኒስትር ፒት ሄግሴት ግን "ኢራን ከእኛ በላይ እየተዋጋች መዝለቅ አትችልም" ሲሉ ተናግረዋል። ይህ ሃሳባቸው ምናልባት ትክክል ሊሆን ይችላል።