ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኒውክሌር ጦርነት ሊያስነሳ የነበረው የኖርዌይ የአየር ሁኔታ ምርምር ሮኬት
በአውሮፓውያኑ ጥር 25/1995 ኖርዌይ 'ኖርዘርን ላይትስ' የተባለውን የሰማይ ላይ ደማቅ ብርሃን ለማጥናት የተኮሰችውን ሮኬት ሩሲያ በስህተት ወደ ሞስኮ የተወነጨፈ የኒውክሌር ሚሳዔል እንደሆነ ቆጥራው ነበር።
ከቀዝቃዛ ጦርነት ስሜት ገና በቅጡ ያላገገመው ዓለም በአንድ የአዘቦት ቀን ለሰዓታት የቆየ በድጋሚ ጦርነት ውስጥ የመግባት አስከፊ ስጋት ተጋርጦባት ነበር።
በአንድ ረቡዕ ከሰዓት በሰሜናዊ ሩሲያ በሚገኙ የራዳር ጣቢያዎች ተረኛ ወታደራዊ ቴክኒሻኖች በስክሪናቸው ላይ አንድ አስደንጋጭ የብርሃን ምልክት አስተዋሉ።
ከኖርዌይ የባሕር ዳርቻ የተተኮሰ ሮኬት በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ላይ እየተምዘገዘገ ነበር። ቴክኒሺያኖቹ ይህ ተወንጫፊ ወዴት እየሄደ ነው? ስጋትስ ይሆን? የሚል ጥያቄ ይመላለስባቸው ጀመር።
በዚያ የውሃ አካል ውስጥ ከሚገኘው የአሜሪካ ሰርጓጅ መርከብ የሚተኮስ አንድ ሚሳዔል በ15 ደቂቃ ውስጥ ስምንት የኒውክሌር ቦንቦችን ሞስኮ ላይ ማዝነብ እንደሚችል ያውቃሉ።
ይህ መረጃ በፍጥነት የዕዝ ሰንሰለቶችን አልፎ ወደ ሩሲያው ፕሬዝዳንት ቦሪስ የልሲን ደረሰ። ይህንን የሰሙት ፕሬዝዳንቱም የኒውክሌር ቦምቦችን ለማፈንዳት የሚያስችሉ መመሪያዎችን እና ቴክኖሎጂዎችን የያዘውን 'የኑክሌር ቦርሳ' (nuclear briefcase) በሥራ ላይ ያዋሉ የመጀመሪያው የዓለም መሪ ሆኑ።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ጀምሮ ኒውክሌር የታጠቁ አገራት የመከላከል ፖሊሲን ሲከተሉ ቆይተዋል። አገራቱ ይህንን ፖሊሲ ምርጫቸው ያደረጉት በየትኛውም ወገን የሚከተኮስ የኒውክሌር ቦንብ የጋራ እልቂትን እንደሚያስከትል በመገንዘባቸው ነበር።
በድንገት ኒውክሌር እንደተተኮሰባቸው ያሰቡት የሩሲያ መሪ እና አማካሪዎቻቸው የአጸፋ ጥቃት ጥቃት መፈጸም አለብን ወይስ የለብንም የሚለውን በፍጥነት መወሰን ነበረባቸው።
በመጨረሻም ግን ይህ አስጨናቂ ቅጽበት ወደ ጥፋት ሳይቀየር ረግቧል። የተፈጠረው ነገር በዚያኑ ምሽት ዜና ላይ ቀረበው ቀለል ያለ ኹነት ተደርጎ ነበር።
በዚያ ምሽት ዜና ያነበበው የቢቢሲ ኒውስ ናይት አቅራቢ ጄረሚ ፓክስማን ፕሮግራሙን ከማጠናቀቁ በፊት እንዲህ አለ፤ "ከመለያየታችን በፊት፤ የሩሲያ የዜና ወኪል ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግም ዛሬ የኒውክሌር ጦርነት አለመቀስቀሱን ልናሳውቃችሁ እንወዳለን።"
በዚያን ዕለት ከቀኑ ስምንት ሰዓት ገደማ ላይ፤ የሞስኮው ኢንተርፋክስ የዜና ወኪል ሩሲያ ወደ ግዛቷ እየመጣ የነበረን ሚሳዔል መትታ መጣሏን የሚገልጽ ዘገባ አውጥቶ ነበር።
ይህንን የተመለከቱ ጋዜጠኞች ወደ መከላከያ ሚኒስቴር ስልክ ሲደውሉ ያገኙት ምላሽ "ብሪታንያ ወደ ሩሲያ ምንም ዓይነት ሚሳዔል እንዳልተኮሰች እርግጠኛ ነን" የሚል ነበር።
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይም ከሰማው ዘገባ ውጪ ምንም ነገር እንደሌለ ገለጸ። በዚህ ዘገባ ምንክያት የዓለም የገንዘብ ገበያ ተናወጠ። ፖለቲከኞች፣ ወታደራዊ መሪዎች እና ጋዜጠኞች ደግሞ ለአንድ ሰዓት ያህል መረጃ ለማግኘት ላይ ታች ሲሉ አሳለፉ።
ዘጠኝ ሰዓት ገደማ ላይ የሩሲያው የዜና ወኪል ዘገባውን አስተካከለ። ምንም እንኳ የሩሲያ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት ሚሳዔል መተኮሱን ቢመዘግብም ሮኬቱ ያረፈው ኖርዌይ ግዛት ውስጥ መሆኑን አስታወቀ።
ኋላ ላይ የኖርዌይ መከላከያ ሠራዊት ባለሥልጣናት የተተኮሰው ሰላማዊ ሮኬት መሆኑን አረጋገጡ።
ሳይንሳዊ የምርምር ፕሮግራም አካል የሆነው ሮኬት የተወነጨፈው ስለ 'ኖርዘርን ላይትስ' መረጃ ለመሰብሰብ እንደነበር አስረዱ። 'ኖርዘርን ላይትስ' በሰማይ ላይ የተለያዩ ቀለማትን የያዘ ብርሃን የሚፈጥር ልዩ የአየር ሁኔታ ክስተት ነው።
ሮኬቱ በታቀደው መሠረት ከሩሲያ የአየር ክልል ርቆ በሚገኘው በአርክቲክ ውቅያኖስ ስፒትስበርገን ደሴት አቅራቢያ ባለ የውሃ አካል ላይ ነበር ያረፈው።
የሩሲያ ባለሥልጣናት ግን ዘገባው ስህተት መሆኑ ከታወቀ ከሰዓታት በኋላም ማመን አልመረጡም ነበር።
ስማቸው ያልተጠቀሰ የሩሲያ የመከላከያ ምንጮች ተኩሱ የሞስኮን የቅድመ ማስጠንቀቂያ ራዳር ሥርዓት ለመፈተሽ ታስቦ የተደረገ መሆን አለመሆኑን "ለመናገር ገና እንደሆነ" መግለጻቸውን የዜና ወኪሉ ዘግቧል።
ምንም እንኳ በዚያ ወቅት ቀዝቃዛው ጦርነት አብቅቶ የነበረ ቢሆንም፤ አንዳንድ የሩሲያ ባለሥልጣናት አሁንም ኒውክሌር ጥቃት ስጋት እንደሚያስጨንቃቸው ያሳየ ክስተት ነበር።
ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪዎች ከመጡ በኋላ በተጠራው ስብሰባ ላይ የነበሩት ኖርዌያዊው ተመራማሪ ኮልብጆርን አዶልፍሰን፤ "የእኛ [ሮኬት] ተኩስ ስለተሰጠው ትኩረት ስሰማ ደንግጬ ነበር" ይላሉ።
ይህንን ክስተት አስገራሚ ያደረገው አንዱ ጉዳይ ኖርዌይ ሊደረግ ስለታቀደው ሮኬት ማስወንጨፍ ለሞስኮ አሳውቃ የነበረ መሆኑ ነው።
ሩሲያውያኑ በዚያ መጠን ተደናገጡት ለ'ኖርዘርን ላይትስ' ምርምር የተተኮሰ ሮኬት እንዲህ ባለ ከፍተኛ የባለስቲክ አካሄድ ሲወነጨፍ የመጀመሪያው በመሆኑ ሊሆን እንደሚችል ተመራማሪው አዶልፍሰን ያስረዳሉ። ይህም ቢሆን ግን የሚያስደነግጥ መሆን አልነበረበትም ባይ ናቸው።
"ታኅሣሥ 14 ላይ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ለሚመለከታቸው አገራት ሁሉ እንደምናስወነጭፍ መረጃ ተልኮ ነበር" ይላሉ።
በዚህ መልኩ የተላከው ማስጠንቀቂያ ግን በሆነ ምክንያት ለሚመለከተው ክፍል ሳይደርስ ቀርቷል። ይህ ክስተት የአንድ መልዕክት አለመድረስ እንዴት ለከፋ ጥፋት መንስኤ ሊሆን ያሳየ ሆኗል።
አገራት የኑውክሌር መሣሪያን መታጠቅ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ዓለም እንዲህ ዓይነት ወደ ጥፋት ሊያመሩ ጫፍ የደረሱ ክስተቶችን አስተናግዳለች።
በአውሮፓውያኑ 1962 የተከሰተው የኩባ ሚሳዔል ቀውስ አሜሪካ እና ሶቪየት ወደ ኒውክሌር ጦርነት እንዲገቡ ጫፍ አድርሷቸው የነበረ የቀዝቃዛው ጦርነት ክስተት ነው።
በመንጋ እንደሚበሩ ዝይዎች፣ ጨረቃ እንዲሁም ኮምፒውተር ብልሽቶች እና የጠፈር አየር ሁኔታ ያሉ ሁኔታዎች ሐሰተኛ የኒውክሌር ማስጠንቀቂያዎችን ፈጥረው እንደነበር ቢቢሲ ፊውቸር በ2020 ባወጣው ዘገባ ያመለክታል።
በ1958 አንድ አውሮፕላን በስህተት የአንድ ቤተሰብ የአትክልት ስፍራ ላይ የኒውክሌር ቦምብ ጥሎ ነበር። እንደ ዕድል ሆኖ የሞቱት ዶሮዎች ብቻ ነበሩ።
በ1966 በአንድ የስፔን ገጠራማ መንደር ውስጥ ሁለት የአሜሪካ ወታደራዊ አውሮፕላኖች ተጋጭተው ነበር። አንዱ አውሮፕላን ኒውክሌር የጫነ ነበር።
በቅርብ ጊዜ በአውሮፓውያኑ 2010 ደግሞ የአሜሪካ አየር ኃይል 50 ገደማ ሚሳዔሎችን የሚቆጣጠርበት ግንኙነት ለጥቂት ጊዜ ተቋርጦ ነበር። ይህ ሁኔታ ሚሳዔሎቹን ለመከታተል ወይም አውቶማቲክ በሆነ መልኩ እንዳይወነጨፉ ማድረግን ከልክሎ ነበር።
አደገኛው ቅጽበት
በወቅቱ በርካታ ሩሲያውያን ለመጀመሪያ ጊዜ የኑክሌር ቦርሳው ጥቅም ላይ መዋሉን የሚናገረውን የፕሬዝዳንቱን ንግግር አልተቀበሉትም። የቺቺኒያ ጦርነት ላይ የነበረውን ትኩረት ለማስቀየር የተደረገ እንደሆነም ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ምንም እንኳ የምሽት ዜና ይህ ክስተት ቀለል ተደርጎ ቢቀርብም የጉዳዩ ትልቅነትን በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች ይሰጣሉ።
አንድ የቀድሞ የሲአይኤ ባለሥልጣን "በኒውክሌር ሚሳዔል ዘመን የታየ ብቸኛው እጅግ አደገኛ ቅጽበት" እንደሆነ ተናግረዋል።
ወታደራዊ አማካሪ ሆኑት ፒተር ፕራይ "ከዚህ ቀደም የትኛውም ኒውክሌር የታጠቀ መሪ፣ እውነተኛ ስጋት እንዳለ አስቦ እንዲሁም ዓለምን ወደ መጨረሻው ጥፋት የሚወስድ ውሳኔ ወዲያውኑ ማሳለፍ በሚችልበት ሥልጣን ላይ ሆኖ፤ የሩሲያው 'የኑክሌር ቦርሳ' ዓይነት መሣሪያ በቁም ነገር ከፍቶ አያውቅም ነበር" ሲሉ ጽፈዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የኒውክሌር ትጥቅ ማስፈታት ተመራማሪ የሆኑት ፓቬል ፖድቪግ በበኩላቸው ይህንን ክስተት አግዝፈው አይመለከቱትም።
"ይህንን ክስተት ከ10 ደረጃ ስጠው ብባል 3 ነው የምሰጠው። በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ከዚህ የባሱ ክስተቶች ነበሩ" ይላሉ።
የሩሲያ የኒውክሌር ባለሙያ የሆኑት ቭላድሚር ድቮርኪን በአንጻሩ፤ የኖርዌዩ ሮኬት ምንም ዓይነት የአደጋ ስጋት የሚፈጠር እንዳልነበረ ገልጸዋል።
ባለሙያው በ1998 ለዋሽንግተን ፖስት በሰጡት አስተያየት "የማስጠንቀቂያ ሥርዓቱ ከፍተኛ ጥቃት መሰንዘሩን የሚያሳይ ምልክት ቢሰጥ እንኳ ማንም እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ላይ አይደርስም፤ ምክንያታዊ ያልሆነ መሪ ጭምር" ብለዋል።
ከክስተቱ አምስት ቀናት በኋላ ሩሲያ ጉዳዩ "ባለመግባባት" የተፈጠረ እና የማይደገም መሆን እንዳለበት ገልጻለች።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይም ኖርዌይ መደበኛውን አሠራር መከተሏን ገልጸው፤ ቅሬታ ሊነሳባቸው እንደማይገባ ተናግረዋል።
ምንም እንኳን በዚህ ክስተት የተጋረጠው ጥፋት ቢወገድም፤ አንዲት የአየር ሁኔታ ምርምር ሮኬት እንዲህ ዓይነት ድንጋጤ መፍጠሯ አሁንም ድረስ የሚያነጋግር ጉዳይ ነው።