አሜሪካ በ30 ዓመት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ሙከራ እንድታደርግ ትራምፕ አዘዙ

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ጦር የኒውክሌር መሣሪያ ሙከራ ማድረግ እንዲቀጥል አዘዙ።

እንደ ቻይና እና ሩስያ ካሉ አገራት ጋር "በሰላም ለመቀጠል" ከ30 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ሙከራ እንዲደረግ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

"ሌሎች አገራት የኒውክሌር መሣሪያ ሙከራ እያደረጉ ነው። እኛም ሙከራ እንድንቀጥል አዝዣለሁ" ብለዋል።

ትራምፕ ይህን ያሉት ከቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ዢፒንግ ጋር በደቡብ ኮርያ ከመገናኘታቸው አስቀድሞ ነው።

አሜሪካ ከየትኛውም አገር በላቀ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዳላት ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

በሁለተኛ ደረጃ የምትገኘው ሩስያ እንደሆነች ጠቅሰው፤ ቻይና "በሩቁ በሦስተኛነት ትከተላለች" ብለዋል።

አሜሪካ እአአ ከ1992 ወዲህ የኒውክሌር መሣሪያ ሙከራ አላካሄደችም።

ሩስያ ከሰሞኑ በኒውክሌር ኃይል የሚሠራ የሚሳዔል ሙከራ ስታደርግ ትራምፕ በጽኑ አውግዘዋል።

ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ "ኒውክሌር መሣሪያ አውዳሚ ነው" ቢሉም ሥልጣን ላይ ሳሉ የአሜሪካን የጦር መሣሪያ ከማዘመን ውጭ "አማራጭ" እንደሌላቸው ገልጸዋል።

የቻይና የኒውክሌር መሣሪያ አቅም "በአምስት ዓመታት ውስጥ" ከአሜሪካ እኩል እንደሚሆን ተናግረዋል።

የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ሙከራው እንዴት እንደሚከናወን ዝርዝር መረጃ ባይሰጡም "በቅርቡ ይጀመራል" ብለዋል።

አሜሪካ ከ30 ዓመታት በፊት ለመጨረሻ ጊዜ የኒውክሌር መሣሪያ ሙከራ ያደረገችው በነቫዳ ግዛት ከምድር በታች በሚገኝ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ነበር።

'ዲቫይደር' የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ፕሮጀክት፤ የአሜሪካ 1,054ኛ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ሙከራ ነው።

በዓለም የመጀመሪያውን አቶሚክ ቦምብ ለመሥራት ጉልህ አስተዋጽኦ ነበረው።

የአሜሪካ መንግሥት ነቫዳ የሚገኘውን ወታደራዊ ካምፕ አሁንም ይጠቀምበታል።

የአሜሪካ ብሔራዊ የኒውክሌር ሳይንስ እና ታሪክ ሙዚየም በበኩሉ "አስፈላጊ ከሆነ በዚሁ ቦታ በድጋሚ ሙከራ ይደረጋል" ብሏል።