ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ ትልቁን የጦር መርከቧን ወደ ካሪቢያን አስጠጋች
አሜሪካ ትልቁን የጦር መርከቧን ከሜድትራኒያን ወደ ካሪቢያን ባሕር አስጠጋች።
የቬንዝዌላው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ አሜሪካ "ጦርነት እየጫረች ነው" ብለዋል።
የአሜሪካ መከላከያ ጸሐፊ ፒት ሄግሴት እስከ 90 ተዋጊ ጀቶችን የሚይዘው ግዙፍ የጦር መርከብ (USS Gerald R Ford) ወደ ካሪቢያን እንዲጠጋ አዘዋል።
ማዱሮ "አዲስ ውስጣዊ ጦርነት እያጫሩ ነው። 'ዳግመኛ እጃችንን ጦርነት ውስጥ አናስገባም' ቢሉም አዲስ ጦርነት እየቀሰቀሱ ነው" ብለዋል።
አሜሪካ በካሪቢያን አካባቢ ያለውን ወታደራዊ ይዞታዋን እያሰፋች ነው። በአካባቢው ከጦር መርከቦች በተጨማሪ የኒውክሌር ሰርጓጅ መርከብ እና ኤፍ-35 የጦር ጀት አከማችታለች።
አሜሪካ የጦር መሣሪያዎቹ ያስፈለጓት የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን ለመግታት እንደሆነ ትገልጻለች።
የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች ናቸው ባለቻቸው አሥር ጀልባዎች ላይም ጥቃት ፈጽማለች።
ያለፈው አርብ በደረሰው ጥቃት "ስድስት አደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪ አሸባሪዎች ተገድለዋል" ሲሉ ፒት ሄግሴት ተናግረዋል።
አሜሪካ ጥቃቱን የፈጸመችው በካሪቢያን ባሕር ላይ ሲሆን፤ በጀልባው የተሳፈሩት 'ትሬን ደ አራግዋ' የተባለው የወንጀለኞች ቡድን አባላት መሆናቸውን ሄግሴት ገልጸዋል።
ተንታኞች አሜሪካ የፈጸመችው ጥቃት አስፈላጊነት ላይ ጥያቄ አንስተዋል። በአካባቢውም አሜሪካ ውግዘት ደርሶባታል።
የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን እየተዋጋሁ ነው ቢልም፤ ዓላማው ማዱሮን ከሥልጣን ማውረድ ነው ሲሉ የአሜሪካ ምክር ቤት አባላት እና ተንታኞች ተችተዋል።
ማዱሮ የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪ ቡድን 'መሪ ናቸው' ሲሉ ትራምፕ ቢከሱም ማዱሮ አስተባብለዋል።
በቻተም ሀውስ ቲንክ ታንክ የላቲን አሜሪካ ተንታኝ ዶ/ር ክሪስቶፈር ሳባቲኒ "አሜሪካ ታስፈራራለች እንጂ ወረራ አትፈጽምም ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ግባቸው አዲስ አስተዳደር ማምጣት ነው" ብለዋል።
አሜሪካ የጦር መሣሪያዎችን ወደ ቀጣናው አስጠግቶ ፍርሃት በመፍጠር የማዱሮ ደጋፊዎችን አቋም ማስቀየር እንደምትሻ ዶ/ር ክሪስቶፈር ያምናሉ።
አሜሪካ ወደ ካሪቢያን ያስጠጋችው የጦር መርከብ "የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን እና የወንጀለኛ ቡድኖች እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር" እንደሚውል ገልጻለች።
ትራምፕ በተደጋጋሚ ቬንዝዌላ ላይ ጥቃት ሊሰነዘር እንሚችል አስጠንቅቀዋል።
"የባሕር አካባቢው በቁጥጥራችን ሥር ነው። እግረኛ ጦርንም አማራጭ ልናደርግ እንችላለን" ብለዋል።
ትራምፕ በቬንዝዌላ ያሉ አደንዛዥ ዕፅ ማምረቻዎች ላይ ጥቃት ሊሰነዝሩ እንደሚችሉ ሲኤንኤን ዘግቧል።
አሜሪካ ግዙፉን የጦር መርከቧን ለመጨረሻ ጊዜ ያሰማራቸው እአአ በ2023 ነው።
የጦር መርከቡ ወደ ካሪቢያን ባሕር መጠጋቱ በአሜሪካ እና በቬንዝዌላ መካከል ያለውን ውጥረት አባብሷል።
ዴሞክራቶች እና ሪፐብሊካኖች አሜሪካ በጀልባዎች ላይ እያደረሰች ያለው ጥቃት ሕጋዊነት ላይ ጥያቄ እያነሱ ነው።
የኬንተኪ ሴናተር የሆኑት ሪፐብሊካኑ ራንድ ፖል፤ አሜሪካ ጥቃት ከመፈጸሟ አስቀድሞ የሕዝብ እንደራሴዎችን ይሁንታ ማግኘት እንዳለባት ተናግረዋል።
ትራምፕ ግን የምክር ቤቱ ፈቃድ የሚያስፈልጋቸው "እግረኛ ጦር ካሰማሩ" እንደሆነ ገልጸዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ጸሐፊ ማርኮ ሩብዮ "አደንዛዥ ዕፅ የያዘ ጀልባ በእሳት ሲጋይ ማየት ካልፈለጋችሁ ጀልባውን ወደ አሜሪካ አትላኩ" ብለዋል።
አሜሪካ እስካሁን ባደረሰችው ጥቃት የተገደሉ ሰዎች 43 ደርሰዋል።