ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ የቬንዙዌላ ዕፅ አመላላሽ ነው ያለችው ጀልባ ላይ ባደረሰችው ጥቃት ሶስት ሰዎች ተገደሉ
ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ሰኞ የአሜሪካ ጦር ኃይል የቬንዙዌላ ጀልባ ላይ ጥቃት ማድረሱን አስታወቁ።
ዓለም አቀፍ ውሀ ላይ እየተንቀሳቀሰ የነበረው አነስተኛ ጀልባ ወደ አሜሪካ አደንዛዥ ዕፅ ይዞ እየሄደ ነበር ብለዋል ፕሬዝደንቱ።
ትራምፕ "አመፀኛ ዕፅ አመላላሾች ላይ" በተደረገ ጥቃት ሶስት ግለሰቦች መገደላቸውን ቢገልፁም ጀልባው ዕፅ ይዞ እንደነበር የሚያሳይ ማስረጃ አላቀረቡም።
ጥቃቱ የተፈፀመው፤ የቬንዙዌላው ፕሬዝደንት ኒኮላስ ማዱሮ ሀገራቸው ከአሜሪካ "ወረራ" ራሷን እንደምትከላከል ከገለፁ በኋላ ነው።
ማዱሮ የአሜሪካውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ "የሞት እና የጦርነት ጌታ" ሲሉ ዘልፈዋል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት አሜሪካ፤ ደቡብ ካሬቢያን ላይ ፀረ አደንዛዥ ዕፅ ያለችውን ኦፕሬሽን አካሂዳ 11 ሰዎች ከተገደሉ በኋላ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት እየሻከረ መጥቷል።
"ዛሬ ንጋት በኔ ትዕዛዝ መሠረት የአሜሪካ ጦር ኃይል አመፀኛ እና ነውጠኛ የዕፅ አዘዋዋሪዎች ላይ ሁለተኛ ጥቃት ፈፅሟል" ሲሉ ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገፃችው ፅፈዋል።
"እኚህ አደገኛ እና ነውጠኛ የዕፅ አዘዋዋሪዎች የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ላይ አደጋ ይደቅናሉ።"
ትራምፕ ውቅያኖስ ላይ ያለ አነስተኛ ጀልባ በጥቃቱ ሲወድም የሚያሳይ የ30 ሰከንድ ቪድዮም አጋርተዋል።
ከኦቫል ኦፊስ መግለጫ የሰጡት ትራምፕ፤ ጀልባው የአደገኛ ዕፅ አዘዋዋሪዎች ስለመሆኑ ተመዝግቦ የተቀመጠ ማስረጃ እንዳላቸው አስታውቀዋል።
"የሚጫነውን ዕቃ ማየት ብቻ ነው የሚጠበቅባችሁ። ተለቅ ያሉ ኮኬይን እና ፌንታኒል የያዙ ቦርሳዎች በየቦታው ይታያሉ። ይህን ቀድተን ይዘናል። ሁሉንም በጥንቃቄ መዝግበን ይዘናል" ብለዋል።
ፕሬዝደንቱ በቅርብ ጊዜያት ወደ አሜሪካ የሚገባው አደገኛ ዕፅ መጠን መቀነሱን ቢናገሩም አዘዋዋሪዎቹ በምድር በኩል አሁንም እየገቡ እንደሆነ አልካዱም።
ፕሬዝደንት ማዱሮ ከአሜሪካ ጋር ያላቸው ግንኙነት "[በአሜሪካዎች] ቦምብ ጥቃት ዛቻ ምክንያት" መውደሙን ተናግረዋል።
"ከሻከረ ግንኙነት ተሻግሮ አሁን እንዳይጠገን ሆኖ ተሰብሯል።"
ማዱሮ አክለው መንግሥታቸው "ራሱን ለመከላከል ሕጋዊውን እርምጃ እንደሚወስድ" አስታውቀዋል።
የሕግ ባለሙያዎች 11 ሰዎች የተገደሉበት የመጀመሪያው የአሜሪካ ጥቃት ዓለም አቀፍ ውሀ ላይ በመፈፀሙ የሰብዓዊ መብት እና የባሕር ሕግን የጣሰ ሊሆን ይችላል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሀገራቸው ቬንዙዌላ ውስጥ ጥቃት ልትፈፅም ትችል እንደሁ የተጠየቁት ፕሬዝደንት ትራምፕ "ምን እንደሚፈጠር አብረን እናያለን" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ቬንዙዌላ "ወደኛ የምትልከው የአደገኛ ቦዘኔ አባላትን፣ የአደገኛ ዕፅ አዘዋዋሪዎችን እና ዕፆችን ነው" ብለው የወቀሱት ፕሬዘደንቱ ከመጀመሪያው ጥቃት በኋላ ካሬቢያን ላይ ያለው እንቅስቃሴ መቀነሱን ገልፀዋል።