ሩሲያ በኒውክሌር ኃይል የሚንቀሳቀስ የአዲስ ሚሳዔል ሙከራ ማድረጓን አስታወቀች

ሩሲያ በኒውክሌር ኃይል የሚንቀሳቀስ ቡሬቬስኒክ የተባለ ክሩዝ ሚሳዔል ሙከራ ማድረጓን የአገሪቷ ከፍተኛ ጄነራል ተናገሩ።

የሩሲያ ጦር ኤታማዦር ሹም ቫለሪይ ጌራሲሞቭ በቴሌቪዥን በተላለፈ ስብሰባ ላይ ለፑቲን ሲናገሩ "ለብዙ ሰዓታት መጓዝ የሚችል በኒውክሌር ኃይል የሚንቀሳቀስ ሚሳዔል ሙከራ አድርገናል። ሚሳዔሉ 14 ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት የሸፈነ ሲሆን፣ ይህ ግን መድረስ የሚችልበት የርቀት ወሰኑ አይደለም" ብለዋል።

ዝቅ ብሎ መጓዝ የሚችለው የሙከራ የጦር መሣሪያ መጀመሪያ ላይ የተዋወቀው እንደ አውሮፓውያኑ በ2018 ሲሆን፣ ያልተገደበ ርቀት መጓዝ በመቻሉ እና የሚሳዔል መከላከያዎችን አልፎ መሄድ በመቻሉ ሲደነቅ ቆይቷል።

ቀደም ብሎ ምዕራባውያን ባለሙያዎች የሚሳዔሉን ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታውን እና ሩሲያ በተሳካ ሁኔታ ሞከርኩ ማለቷ ላይ ጥርጣሬያቸውን ገልጸው ነበር።

የሚሳዔሉ የመጨረሻው ስኬታማ ሙከራ የተደረገው ከሁለት ዓመት በፊት እንደሆነ ፑቲን የተናገሩ ሲሆን ይህ ግን በገለልተኛ ወገን አልተረጋገጠም።

አንድ የጦር መሣሪያ ቁጥጥር ዘመቻ ቡድን እንዳለው ከአውሮፓውያኑ 2016 ጀምሮ ከተደረጉ የሚታወቁ ቢያንስ 13 ሙከራዎች መካከል በከፊል ስኬታማ የሆኑት ሁለቱ ብቻ ናቸው።

ጄነራል ጌራሲሞቭ እንዳሉት ከስድስት ቀናት በፊት የተሞከረው ሚሳዔሉ ለ15 ሰዓታት በአየር ላይ ቆይቶ ነበር።

ሚሳዔሉ የቁመት እና አግድሞሽ እንቅስቃሴውን መምራት እንደሚቻል መሞከሩን እና በታሰበው ዝርዝር መሠረት ሁሉን ያሟላ መሆኑን መናገራቸውን የሩሲያው ታስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

" በመሆኑም ሚሳዔሎችን እና የአየር መከላከያ ሥርዓቶችን አልፎ መሄድ እንደሚችል አሳይቷል" ሲል ታስ ጄነራል ገራሲሞቭን ጠቅሶ ዘግቧል።

ሚሳዔሉ እንደ አውሮፓውያኑ 2018 ለመጀመሪያ ጊዜ ከተዋወቀ አንስቶ ያለው ጥቅም በጦር እና መከላከያ ዙሪያ ከባድ ክርክር ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል።

የአሜሪካ አየር ኃይል የሆነው ብሔራዊ የአየር እና የሕዋ ደኅንነት ማዕከል በ2021 ባወጣው ሪፖርት " የኒውክሌር ኃይል ያለው ክሩዝ ሚሳዔል አህጉር አቋራጭ ርቀት የመጓዝ አቅም ያለውና የኒውክሌር ኃይል ያለው መሣሪያው ሩሲያን ልዩ መሣሪያ እንድትታጠቅ ያደርጋል" ሲል ድምዳሜ ላይ ደርሷል።

ሆኖም ዓለም አቀፉ የስትራቴጂያዊ ጥናት ተቋም በዚያው ዓመት ሩሲያ መሣሪያውን ተጨባጭ ለማድረግ ወሳኝ ተግዳሮቶች እንደገጠሟት ገልጿል።

"ብዙ ሙከራዎች ከሽፈዋል፤ ብዙ ሞቶችን ያስከተለ አደጋም አስከትሏል" ብሏል።

በተቋሙ ሪፖርት የተጠቀሰው የሩሲያ ጦር ጆርናል ሚሳዔሉ ከ10 ሺህ እስከ 20 ሺህ ኪሎሜትር ድረስ እንደሚጓዝ እና በሩሲያ የትኛውም ክፍል ለማረፍ እንደሚያስችል እንዲሁም በአሜሪካ አሕጉር ያሉ ዒላማዎች ድረስ የመድረስ አቅም እንዳለው ያስረዳል።

ይኸው ጆርናል ሚሳዔሉ ከመሬት ከ50 ሜትር እስከ 100 ሜትር ከፍታ ድረስ ዝቅ ብሎ መብረር እንደሚችል እና ለአየር መከላከያ ሥርዓቶች ቁጥጥር እንደሚያስቸግር ጠቅሷል።

ሚሳዔሉ በሰሜን የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ 'ስካይፎል' የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።

ባለፈው ዓመት ሮይተርስ የዜና ወኪል በሰራው የምርመራ ዘገባ በሰሜን ሞስኮ 475 ኪሎሜትር በሚርቀው ሥፍራ መሣሪያው የሚተኮስበት ሥፍራ እንደሆነ ገልጿል።

ከነሐሴ 24 ጀምሮ ያሉ የሳይተላይት ምስሎችን የተነተኑት ዲከር ኢቭሊት ለሮይተርስ እንደተናገሩት በሥፍራው በግንባታ ላይ ያሉ ዘጠኝ ማስወንጨፊያዎችን ለይተዋል።