ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ እና ሩሲያን ሊያጋጭ ይችላል የተባለው ዩክሬን እንዲሰጣት የጠየቀቸው ቶማሃውክ ሚሳዔል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለዩክሬን ረዥም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳዔል ሊሰጡ እንደሚችሉ ከተናገሩ በኋላ ይህ ጦር መሣሪያ ሊያስከትል የሚችለው ውጤት መነጋገሪያ ሆኗል።
ትራምፕ አርብ ዕለት ከዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ዋት ሐውስ ውስጥ በተገናኙበት ጊዜ ከተወያዩባቸው ነጥቦች አንዱም የዚህ መሣሪያ ጉዳይ ነው።
ዜሌንስኪ ሩሲያን መልሶ ለማጥቃት ከአሜሪካ ወሳኝ ወታደራዊ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ሲጠይቁ ቆይተዋል።
ወደ አሜሪካ ባቀኑበት ወቅትም ከትራምፕ ጋር በነበራቸው ውይይት ቶማሃውክ ሚሳዔልን በተመለከተ አወንታዊ ምላሽ እንደሚያገኙ ጠብቀው ነበር።
ባለንበት የአውሮፓውያን ዓመት ዜሌንስኪ ወደ አሜሪካ ሦስት ጊዜ ተጉዘዋል።
ዩክሬን በቅርቡ 'ዘ ፍላሚንጎ' የተባለ የራሷን ረዥም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳዔል መጠቀሟ ተዘግቧል።
ሆኖም አሜሪካ ቶማሃውክ የተባለውን የረዥም ርቀት ሚሳዔል እንድትሰጣት ትፈልጋለች።
ነገር ግን ትራምፕ ሚሳዔሉን ከመስጠት ይልቅ ሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነቱን ባለበት አቁመው በንግግር መፍትሄ እንዲፈልጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ዜሌንስኪ ግን አሁንም ወሳኝ ያሉትን ሚሳዔል ከአሜሪካ የመታጠቅ ተስፋ እንዳለ ይናገራሉ።
ዩክሬን ለምን ቶማሃውክ ሚሳዔልን ፈለገች?
ሩሲያ በአውሮፓውያኑ 2022 ዩክሬንን ከወረረች ጀምሮ ዩክሬን ረዥም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳዔል እንዲሰጣት ስትጠይቅ ቆይታለች።
ዩክሬን በጦርነቱ የሚደረስባትን ጥቃት ለመበቀል እና የሩሲያን ምጣኔ ሃብት ለማዳከም የሩሲያን ከተሞች ከሩቅ ዒላማ ማድረግ ትፈልጋለች።
አሜሪካ ለዩክሬን የረዥም ርቀት ሚሳዔል ከሰጠች ጦርነቱ እንደሚባባስ እና የአሜሪካ እና የሩሲያ ግንኙነት የበለጠ እንደሚበላሽ ሞስኮ አስጠንቅቃለች።
ከዚህ ቀደም የተወሰኑ የቶማሃውክ ሚሳዔል ዓይነቶች ከአሜሪካ ለዩክሬን ተሰጥተዋል።
ሚሳዔሎቹ 2,500 ኪሎ ሜትር የሚወነጨፉ ስለሆኑ ወደ ሩሲያ ግዛት ይደርሳሉ።
ቶማሃውክ በከፍተኛ ፍጥነት በመወንጨፍ ይታወቃል። ከመሬት በ10 ሜትር ከፍታ ርቀት ስለሚጓዙ በቀላሉ ማክሸፍ አይቻልም።
ሚሳዔሉ ዒላማ በመምታትም ይታወቃል። አቅጣጫን የመከተል ብቃቱ አስተማማኝ ነው።
ቶማሃውክ የረዥም ርቀት ሚሳዔል ለዩክሬን ቢሰጥ ከየትኛው ቦታ ሊተኮስ ይችላል? የሚለው ጥያቄ ይሆናል።
ሚሳዔሉ የሚተኮሰው ከመርከብ ወይም ከሰርጓጅ መርከብ ነው። ዩክሬን ሚሳዔሉን ለመተኮስ የሚያስችል መርከብ አሁን ላይ የላትም።
አሜሪካ ሚሳዔሉን ከመሬት መተኮስ የሚያስችል ማስወንጫፊያ በቅርቡ ሠርታለች።
ሆኖም ግን የዩክሬን ወታደሮች ያለበቂ ሥልጠና ከመሬት መተኮስ አይችሉም።
የአሜሪካ ሚና ምን ይሆናል?
ዒላማውን የማይስት ረዥም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳዔል ጥቅም ላይ ሲውል የአሜሪካ የስለላ መረጃን በመመርኮዝ ይሆናል።
አሜሪካ በምታቀርበው የስለላ መረጃ ላይ በመመሥረት ዩክሬን ጥቃት ስትሰነዝር ቆይታለች።
ከወራት በፊት አሜሪካ ለዩክሬን የደኅንነት መረጃ ማጋራትን በጊዜያዊት አቋርጣ ነበር።
ፋይናንሻል ታይምስ እንደዘገበው፤ የአሜሪካ የደኅንነት መረጃ ዩክሬን በሩሲያ የነዳጅ እና የኃይል ተቋማትን ዒላማ በማድረግ እንድትመታ አግዟል።
ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንደሚሉት፤ አሜሪካ የምታቀብለው መረጃ ዩክሬን ሚሳዔል ስትተኩስ አቅጣጫ እና ርቀትን ከግምት አስገብታ እንድታነጣጥር ይረዳሉ።
ዩክሬን የሩሲያን የአየር መከላከያ አልፋ ጥቃት እንድትፈጽም የሚያግዘውም ይኸው የስለላ መረጃ ነው።
ዩክሬን ቶማሃውክ ሚሳዔል ከተሰጣት ሚሳዔሉን ለመተኮስ በሚደረገው ዝግጅት የአሜሪካ ባለሙያዎች የግድ መሳተፍ እንዳለባቸው ተንታኞች ይናገራሉ።
ቶማሃውክ በሺዎች የሚቆጠሩ ሚሳዔሎችን ይይዛል። ሩሲያ ያላት የመሣሪያ ብዛት ከፍተኛ ስለሆነ እንዲህ ያሉ መሣሪያዎች ለዩክሬን መልሶ ማጥቃት ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ።
አሜሪካ ከቻይና ጋር ጦርነት ልትገባ ትችላለች የሚል ስጋት ስላለ የዩክሬን እና ሩሲያን ጦርነት ገጽታ ሊቀይር የሚችል ከፍተኛ መሣሪያ ለዩክሬን ላይሰጥ ይችላል።
ሆኖም ግን ለዩክሬን የሚሰጠው መሣሪያ ጥቂትም ቢሆን የጦርነቱን አካሄድ ሊቀይር የሚችልበት ዕድል እንዳለ የሚያምኑ ተንታኞች አሉ።
ዩክሬን የሚሰጧትን ሚሳዔሎች ከሌሎች የጦር መሣሪያዎች ጋር በማቀናጀት ከተጠቀመች የጦርነቱ አካሄድ ሊለወጥ ይችላል።
ሩሲያ የባሕር መሣሪያዎችን ከሰው አልባ አውሮፕላን ጋር በማዋሀድ ዩክሬን ላይ ጥቃት ትፈጽማለች።
ዩክሬን የሩሲያን ነዳጅ ማዕከላትን በትክክል ዒላማ አድርጋ በሚሳዔል መምታቷ የሩሲያ ምጣኔ ሃብት ላይ መዋዠቅ አስከትሏል።
ቶማሃውክ ዩክሬን መሰል ጥቃቶችን እንድታጠናክር ይረዳል።
ትራምፕ ከሩሲያ እና ከዩክሬን ጋር ያላቸው ግንኙነት ተለውጧል?
ባለፉት ወራት ትራምፕ ሩሲያን በተመለከተ የሚሰጧቸው አስተያየቶች ጠንካራ ሆነዋል።
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የተኩስ አቁም ላይ እንዲደረስ እየተባበሩ አይለም ብለው ትራምፕ ያምናሉ።
"ጦርነቱ ካልቆመ ቶማሃውክ ለዩክሬን እንደምንልክ ልነግረው እችላለሁ። ላንልክም፣ ልንልክም እንችላለን። ሩሲያ ቶማሃውክ እንዲተኮስባት የምትፈልግ አይመስለኝም" ብለዋል ትራምፕ።
የሩሲያው ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ "አሁን ከሁሉም አቅጣጫ ነገሮች የተካረሩ ይመስላል። ስለ ቶማሃውክ መወራቱ እጅጉን አስጊ ነው" ሲሉ ለትራምፕ ምላሽ ሰጥተዋል።
ከዚህ ቀደም ቃል አቀባዩ ቶማሃውክ ይላካል ብለው እንደማያስቡ ተናግረዋል። ሚሳዔሉ ለዩክሬን ከተሰጠ ግን "የጦርነቱ መልክ ይለወጣል" ብለዋል።
ሞስኮ ቶማሃውክ ከተተኮሰባት ኒውክሌር ተሸካሚ ሚሳዔል ነው ብላ ልትወስድ እንደምትችል ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
"ሩሲያ ይሄንን እንዴት ልትወስደው ትችላለች? ምን ዓይነት ምላሽ ትሰጣለች?" ብለዋል።
የቀድሞ የሩሲያ ፕሬዝዳንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ "እንዴት ሩሲያ ምላሽ ትሰጣለች? የሚለው ጥያቄ ትክክለኛ ነው። ሚሳዔል ከተላከ ለየትኛውም ወገን አይበጅም። ይህም ትራምፕን ይጨምራል" ብለዋል።
ሜድቬዴቭ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሩሲያ መንግሥት አቋም የተለየ ይዘት ያላቸው አስተያየቶችን በማኅበራዊ ሚዲያ እያጋሩ ነው።
ያለፈው ነሐሴ ላይ የሰጡትን አስተያየት ተከትሎ ትራምፕ ሁለት የኒውክሌር ሰርጓጅ መርከቦች ወደ ሩሲያ ማስጠጋታቸውን ገልጸዋል።
ዜሌንስኪ እና ትራምፕ ከሰሞኑ በስልክ ተወያይተዋል። የዩክሬንን የአየር መከላከያ እና ረዥም ርቀት ሚሳዔል ማጠናከር የንግግራቸው ቀዳሚ ርዕሰ ጉዳይ ነበር።
ኪየቭን ጨምሮ የዩክሬን ከተሞች በሩሲያ ሚሳዔል እና ሰው አልባ አውሮፕላን ከፍተኛ ድብደባ ሲፈጸምባቸው ቆይተዋል።
ሩሲያ የዩክሬንን ኃይል ማመንጫ ተቋማት ዒላማ ታድርጋለች። በተለይም ክረምት እየተቃረበ ሲመጣ የኃይል መቆራረጥ እንዲከሰት ያደርጋል።
ባለፈው ወር የትራምፕ የዩክሬን ልዩ ልዑክ ኪት ኬሎግን እንዳሉት፤ ፕሬዝዳንቱ በሩሲያ ላይ ጥቃቶች እንዲፈጸሙ ይሁንታ ሰጥተዋል።
ልዩ ልዑኩ ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ "በዩክሬን እና በሩሲያ ጦርነት አይመቱም የሚባሉ ቦታዎች የሉም" ብለዋል።