ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኔቶ አዛዥ ችግር በገጠመው የሩሲያ ሰርጓጅ መርከብ ላይ ቀለዱ
የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን (ኔቶ) አዛዥ ማርክ ሩቴ ሰኞ ዕለት የሩሲያን ባሕር ሰርጓጅ መርከብ በሚመለከት ቀልድ ጣል ሲያደርጉ፤ ሞስኮ መርከቡ በቴክኒክ ችግር ምክንያት ያለሥፍራው መታየሩን አስተባብላለች።
የሩሲያ ኖቮሮሲያስክ የሚል መጠሪያ ያለው ሰርጓጅ መርከብ የባሕር አሰሳ ሕግን ለመከተል ከፈረንሳይ ወጣ ብሎ በእንግሊዝ ቻናል አካባቢ የታየ ሲሆን፤ በዩናይትድ ኪንግደም ተዋጊ መርከብ እና ሂሊኮፍተር ክትትል ተደርጎበታል።
የኔዘርላንድስ ባለሥልጣናት ቅዳሜ ዕለት ሰርጓጅ መርከቡ በሰሜን ባሕር መታየቱን አስታውቀዋል።
በስሎቫኒያ ንግግር ሲያደርጉ "የተሰበረው" መርከብ "እያነከሰ" ነበር ብለው የቀለዱት ማርክ ሩቴ፤ በአቅራቢያው መካኒክ ፍለጋ እየተሯሯጡ ይመስላል ብለዋል።
ሩቴ "በሜድትራኒያን የቀረ የሩሲያ ደኅና መርከብ ምንም የለም" ሲሉም አክለው ተናግረዋል።
የሩሲያን ያፈተለኩ የደኅንነት መረጃዎችን የሚያትም አንድ የቴሌግራም ገፅ፤ መስከረም 27 በኖቮሮሲያስክ ሰርጓጅ መርከብ የፍንዳታ ስጋትን እንዲጨምር ያደረገ የነዳጅ ፍሰት እንደነበር ዘግቧል።
የእንግሊዝ ባሕር ኃይል መርከቡ ከሜድትራኒያን ባሕር ከግዳጅ እየተመለሰ እያለ ለሦስት ቀናት እንደተከተለው አስታውቋል።
ከኔቶ ጋር ይህን ተግባር መፈፀሙን የገለፀው ባሕር ኃይሉ ከእንግሊዝ ቻናል ወደ ሰሜን ባሕር ሲያቀና 'ኤችኤምኤስ አይረን ዱክ' የተባለው መርከብ ከባሕሩ በላይ ብቅ ያለውን የሩሲያ ሰርጓጅ መርከብ እና ድጋፍ ሰጪውን መከታተሉን ገልጿል።
የኔዘርላንድስ መከላከያ ሚኒስቴር ቅዳሜ ዕለት የሩሲያውን ሰርጓጅ መርከብ እና ለድጋፍ የሚከተለውን መርከብ ተከታትሎ መሸኘቱን አስታውቋል።
ሞስኮ ሰኞ ዕለት ክሩዝ ሚሳኤል የተሸከሙ የመርከቦች ቡድን ውስጥ አባል የነበረው ሰርጓጅ መርከብ "መርሐ ግብር የተያዘለት መርከብ ለመርከብ መለዋወጥ" እያደረገ ነበር ብሏል።
የሩሲያ ጥቁር ባሕር መርከቦች የፕረስ አገልግሎት "በበርካታ መገናኛ ብዙኃን በነዳጅ እና ኤሌክትሪክ የሚሠራው ኖቮሮሲያክ ሰርጓጅ መርከብ በፈረንሳይ ባሕር ዳርቻ ብልሽት እንዳጋጠመው እና ለአደጋ ጊዜ ከባሕር መውጣቱን በሚመለከት እየተሰራጨ ያለው መረጃ ከእውነታው ያፈነገጠ ነው" ብሏል።
"በዓለም አቀፍ የአሰሳ ሕግ መሠረት ሰርጓጅ መርከቦች በእንግሊዝ ቻናል ከባሕር ወጣ ብለው መጓዝ እንዳለባቸው ይደነግጋል" ሲል መግለጫው አክሏል።
ከዚህ ሁነት ሁለት ሳምንት ቀደም ብሎ የዩናይትድ ኪንግደም ባሕር ኃይል በሩሲያ መርከቦችን ከእንግሊዝ ቻናል እስኪወጡ ድረስ ክትትል ማድረጉን አስታውቋል።
ባለፈው ሰኔ ወር በሐሰተኛ ምልክት ሲንቀሳቀስ የነበረ የሩሲያ የጦር መርከብ በእንግሊዝ ቻናል በድብቅ መጓዙን የቢቢሲ ምርመራ አረጋግጧል።