ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያ በየሳምንቱ የዩኬ ወታደራዊ ሳተላይቶች ላይ ክትትል ታደርጋለች
የሩሲያ ሳተላይቶች የብሪታኒያ ወታደራዊ ሳተላይቶችን እንደሚከታተሉ የዩኬ የጠፈር አዛዥ ኃላፊ ተናገሩ።
ሜጀር ጄነራል ፖል ቴድማን ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ላይ ለመጀመርያ ጊዜ ሞስኮ በዩኬ ኅዋ አሰሳ ላይ ያላትን ጣልቃ ገብነት ተናግረዋል።
ሩሲያ ምድር ላይ ሆና በምትቆጣጠራቸው ስርዓቶች የዩኬን ወታደራዊ ሳተላይቶች ለማፈን በየሳምንቱ ጥረት እንደምታደርግ ተናግረዋል።
ባለፈው ወር የጀርመን መከላከያ ሚኒስትር ቦሪስ ፒስቶሪስ ሩሲያ ጦራቸው የሚጠቀምበትን ሳተላይት ላይ የማወክ ተግባር መፈጸሟን ተናግረው ነበር።
ጄነራል ቴድማን ሩሲያ ተመሳሳይ ድርጊት በዩኬ ሳተላይቶች ላይ መፈጸሟን ተናግረዋል።
"የምንሰራውን ሥራ ለማወቅ ፍላጎት አላቸው። እናም በጣም ቅርብ ተጠግተውን ይበርራሉ" ሲሉ ተናግረዋል።
"እንቅስቃሴዎቻችንን የሚከታተሉበት መሣሪያዎች አሏቸው፤ መረጃዎችን ለመሰብሰብ ይሞክራሉ።"
ጄነራል ቴድማን የዩኬ ወታደራዊ ሳተላይቶች ከሩሲያ የሚመጣን እገዳ ለመመከት በበቂ የተደራጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም "በተከታታይ ሳተላይቶቻችን በሩሲያ እገዳ ሲደርስባቸው እያየን ነው" ብለዋል።
ምን ያህል ጊዜ እገዳ እንደደረሰ ሲጠየቁ "በየሳምንቱ" ሲሉ መልሰዋል።
ሩሲያ የሳተላይቶቹን ግንኙነት ለማፈን የምታደርገው ጥረት ሆን ተብሎ የሚደረግ መሆኑን ገልጸው፣ ይህ ተግባር ዩክሬን ላይ ወረራ ከፈጸመች ጊዜ አንስቶ መጨመሩን ተናግረዋል።
ብሪታኒያ በኅዋ ላይ ለግንኙነት እና ለቅኝት የምትጠቀምባቸው በርካታ ሳተላይቶች አሏት።
አሜሪካ፣ ቻይና እና ሩሲያ እያንዳንዳቸው ከመቶ ሳተላይቶች በላይ በኅዋ ላይ አሏቸው፥።
ባለፉት አስር ዓመታት የሩሲያ እና ቻይና ሳተላይቶች በ70 በመቶ በምህዋር ላይ የሚያደርጉትን በረራዎችን ጨምረዋል።
ጄነራል ቴድማን ሩሲያ እና ቻይና ፀረ ሳተላይት የጦር መሳሪያዎችን መሞከራቸውን ተናግረዋል።
ዩኬ እና ዩኤስ ሩሲያ በኅዋ ላይ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ለማስቀመጥ እየሰራች ነው በሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
አሜሪካ ቻይናን እንደ ስጋት ስትመለከታት ጄነራል ቴድማን ደግሞ ሩሲያን እንደ አሁን ጊዜ አደጋ ይገልጿታል።
"ቻይና የበለጠ የተራቀቁ መሳሪያዎች አሏት ማለት እችላለሁ፤ ነገር ግን ሩሲያኖች ደግሞ የኅዋ እንቅስቃሴዎችን ለማወክ የበለጠ የመጠቀም ፍላጎት አላቸው።"
ጄነራል ቴድማን በኅዋ ላይ ስለሚሆነው "የበለጠ እንደሚሰጉ" ገልጸው ስጋታቸው በኅዋ ላይ እየጨመረ የመጣው መጣበብ ጭምር መሆኑን ይናገራሉ።
በምህዋር ላይ 9,000 ሳተላይቶችን ጨምሮ 45 ሺህ ያህል አካላት አሉ።
በዚህ ዓመት ብቻ 300 ሮኬቶች ወደ ኅዋ ይወነጨፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።