ትራምፕ ላይ የቀረቡ ክሶችን የያዙ እና 'ተደብቀው ነበር' የተባሉ የኤፕስቲን ሰነዶች ይፋ ተደረጉ

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ዶናልድ ትራምፕ ወሲባዊ ጥቃት እንዳደረሱባት የከከሰች ሴት የሰጠችውን ቃለ ምልልስ የያዘ የወሲብ ወንጀለኛው ጄፍሪ ኤፕስቲን የምርመራ ሰነድ ይፋ ተደረገ።

የተጎጂዋን ቃል ምልልስ ጭምቅ ሐሳብ የያዘ ሰነድ በአሜሪካው የወንጀል ምርመራ ተቋም ኤፍቢአይ ሥር ነበር። የፍትሕ መሥሪያ ቤት ይፋ ካደረጋቸው ከወሲብ ወንጀለኛው ጄፍሪ ኤፕስቲን ጋር የተያያዙ ሰነዶች ውስጥ ተካትቷል።

ሰነዱ፤ የፍትሕ መሥሪያ ቤት ከዚህ ቀደም ይፋ ያደረገው የኤፕስቲን ፋይል ውስጥ አለመኖሩ ጥያቄ አስነስቶ ነበር። ዴሞክራቶች፤ ሰነዱን ለመደበቅ ጥረት ተደርጓል ብለው መክሰሳቸውም ይታወሳል።

ሰነዱ "በድጋሚ የተካተተ" በሚል ዝርዝር ውስጥ እንደነበረ የገለጸው የፍትሕ መሥሪያ ቤት፤ ሰነዱ ይፋ ያልተደረገው "በስህተት" መሆኑን አስረድቷል።

ትራምፕን እና ኤፕስቲንን ከከሰሰችው ሴት ጋር በአውሮፓውያኑ 2019 የተደገ ቃለ ምልልስ በሰነዱ ውስጥ ይገኛል።

ትራምፕ ከኤፕስቲን ጋር በተያያዘ ማንኛውንም ወንጀል እንዳልፈጸሙ በተደጋጋሚ ገልጸዋል።

ክሱን ያቀረበችው ሴት ለኤፍቢአይ እንደገለጸችው፤ በ1980ዎቹ ከትራምፕ ጋር ያስተዋወቃት ኤፕስቲን ነበር። በወቅቱ ከ13 እስከ 15 ዕድሜ ክልል ውስጥ ሳለች ሁለቱም ወሲባዊ ጥቃት እንደፈጸሙባት ከስሳለች።

ቃለ መጠይቁን ካደረገች በኋላ ኤፍቢአይ በድጋሚ አላነጋገራትም። ወሲባዊ ጥቃት እንደደረሰባት በገለጸችበት ወቅት ላይ ትራምፕ እና ኤፕስቲን ስለመተዋወቃቸው ግልጽ አይደለም።

ሰነዱ ይፋ ከተደረገ በኋላ ዋይት ሀውስ "መሠረተ ቢስ እና በመረጃ ያልተደገፈ" ሲል አጣጥሏል።

ፕሬስ ሴክሬተሪዋ ካሮላይን ሌቪት "በተደጋጋሚ እንዳልነው የኤፕስቲን ፋይሎች ይፋ መውጣታቸው ትራምፕን ከተጠያቂነት ነጻ የሚያደርግ ነው" ብለዋል።

በጆ ባይደን አስተዳደር ሥር የነበረው የፍትሕ መሥሪያ ቤት ትራምፕን ያልከሰሰው "አንድም ጥፋት አለመፈጸማቸውን ስለሚያውቅ ነው" ሲሉም አክለዋል።

በኤፕስቲን ፋይሎች ውስጥ የትራምፕ ስም ከአንድ ሺህ ጊዜ በላይ ተጠቅሷል። ይህም ኤፕስቲን ለሌሎች ሰዎች የጻፏቸውን ኢሜሎች ያካትታል።

በኤፕስቲን ጥቃት የደረሰባቸው ተጎጂዎች ትራምፕን አልከሰሱም።

ሆኖም ግን ኤፍቢአይ ከምስክሮች ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ትራምፕ ላይ ክሶች ቀርበዋል። አሁን ይፋ የተደረገው በ2019 ከአንድ ተጎጂ ጋር የተደረገው ቃል ምልልስ በዝርዝሩ ውስጥ ተካቷል።

ትራምፕ፣ ኤፕስቲን እና ሌሎችም ታዋቂ ግለሰቦች ወሲባዊ ብዝበዛ በማድረስ ተከስሰዋል። እነዚህ ክሶች ከጥቆማ የዘለሉ አይደሉም። ማስረጃዎችም አልቀረቡም።

የፍትሕ መሥሪያ ቤት ሰነዶቹን ይፋ ማድረግ ሲጀምር "የተወሰኑት ሐሰተኛ ናቸው። ትራምፕ ላይ የቀረቡ አቀጣጣይ ክሶችም ይገኙበታል" ብሏል።

ከ2020 ምርጫ አስቀድሞ ትራምፕ ላይ የቀረቡ ክሶች በሰነዶቹ መካተታቸውን መሥሪያ ቤቱ ጠቅሶ "ክሶቹ መሠረተ ቢስ እና ሐሰተኛ መሆናቸው ግልጽ ሊሆን ይገባል። ትራምፕን ለመቀናቀን እንደ መሣሪያ ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ" ብሏል።

አሁን ይፋ የተደረጉት ሰነዶች ሆነ ተብለው የተደበቁ ናቸው በሚል የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ሲዘግቡ ቆይተዋል።

ኤንፒአር ያወጣው ዘገባ እንደሚያሳየው፤ ኤፍቢአይ ከተጎጂዋ ጋር በ2019 አራት ቃለ ምልልሶች አድርጓል። ቃለ ምልልሶቹ ኤፕስቲን እና አጋሩ ማክስዌል ላይ ከተደረገው ምርመራ ጋር የሚገናኙ ናቸው።

ከ50 በላይ ገጾች ያሏቸው የቃለ ምልልሶቹ ሦስት ክፍሎች እና ጭምቅ ሐሳቡ በፍትሕ መሥሪያ ቤቱ ዝርዝር ውስጥ እንዳልተካተተ ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል።

ትራምፕ እና ኤፕስቲን ኋላ ላይ ቢጣሉም ረዥም ጊዜ የቆየ ወዳጅነት አላቸው። ጓደኝነታቸው እስከ አውሮፓውያኑ 2000 ድረስ እንደቀጠለ ተገልጿል። ትራምፕ እንደሚሉት ኤፕስቲን ከመታሰሩ ከሁለት ዓመት በፊት ተጣልተዋል።