ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መንግሥት "የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት እንዲያረጋግጥ" ጠየቀች
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ፣ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ አርሲ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች በእምነቱ ተከታዮች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አሰመልክቶ ባወጣው መግለጫ መንግሥት የዜጎችን የመኖር መብት እንዲያረጋግጥ ጠየቀ።
በምሥራቅ አርሲ ዞን በጉና፣ በመርቲ፣ በሸርካ እና በሆሎንቆ ዋቤ ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ የቤተ ክርስቲያኒቱ የእምነት ተከታዮች ላይ "ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች" በተፈጸመ ጥቃት 25 ሰዎች መሞታቸውን ቋሚ ሲኖዶሱ ጥቅምት 20/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫው ላይ አመልክቷል።
ቋሚ ሲኖዶሱ በመግለጫው ላይ ጥቅምት 14 ሌሊት በጉና እና መርቲ ወረዳዎች 17 የእምነቱ ተከታዮች፣ ጥቅምት 17 ሌሊት ደግሞ በሸርካ ወረዳ ሦስት፣ እንዲሁም ጥቅምት 18 ሌሊት በሆንቆሎ ዋቤ ወረዳ አምስት የእምነቱ ተከታዮች በድምሩ 25 "ኦርቶዶክሳውያን አገራችን እና ምድራችን ብለው በሰላም በተኙበት በድንገት ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች" መገደላቸውን አስታውቋል።
ሲኖዶሱ ግድያው ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ ነው ያለ ሲሆን፣ ይህንን አስመልክቶ ከምሥራቅ አርሲ አገረ ስብከት የተላከውን ሪፖርት የተመለከተው "በከባድ እና በጥልቅ የሐዘን ስሜት" መሆኑን ገልጿል።
በምሥራቅ አርሲ አገረ ስብከት እንዲህ ዓይነት ድርጊት በተደጋጋሚ ሲፈጸም መቆየቱን የገለፀው ቋሚ ሲኖዶሱ "እንዲህ ዓይነቱ አስነዋሪ ድርጊት በቅዱሳት መጻሕፍትም ሆነ በሰው ልጅ ሰብዓዊ መብት" ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው ብሏል።
በእምነቱ ተከታዮች ላይ የተፈጸመውን ግድያ፣ በነጻነት የማምለክ ሕገ መንግሥታዊ መብትን የሚጋፋ፣ ተከባብሮ እና ተቻችሎ የመኖር መንፈሳዊ እሴትን የሚያጠፋ "ክብረ ነክ እና ሊወገዝ የሚገባው ኢ-ሥነ ምግባራዊ ድርጊት" ሲል ጠርቶታል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ ድርጊቱን በጽኑ በማውገዝ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ይህንን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እንዲያወግዙ "በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠውን በሕይወት የመኖር እና የእምነት ነጻነት መብትን እንዲያስከብሩ" ጥሪ አቅርቧል።
አክሎም መንግሥት ይህንን ድርጊት የፈጸሙትን ግለሰቦች ለሕግ በማቅረብ የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብር እና በቀጣይም ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይደገም የሕግ ከለላ በመስጠት ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስቧል።
ይህንን የቤተክርስቲያኒቷን ቋሚ ሲኖዶስ መግለጫ ተከትሎ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ መንግሥት የዜጎችን በሰላም ወጥቶ የመግባት ነፃነት የማረጋገጥ ዋነኛ ኃላፊነት እንዳለበት በመጥቀስ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።
ጉባኤው ይህ በእምነቱ ተከታዮች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት "ከዚህም በላይ ተባብሶ ተጨማሪ ሐዘን እና ሰቆቃ ከመከሰቱ አስቀድሞ አስፈላጊውን የሕግ ማስከበር ሥራ እንዲሠራ" ጥሪ አቅርቧል።
ባለፈው ሳምንት ረቡዕ እና ሐሙስ በተፈጸመው የመጀመሪያው ጥቃት ከተገደሉ ሰዎች ውስጥ "ስምንቱ የአንድ ቤተሰብ አባላት" እንደሆኑ ቢቢሲ ከቤተሰባአው እና ከተለያዩ ምንጮች ሰምቷል።
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የተገደሉት በጉና ወረዳ ሲሆን ታጣቂዎች ባለፈው ሳምንት ረቡዕ እና ሐሙስ በፈጸሟቸው ጥቃቶች 14 ሰዎች መገደላቸውን ሁለት የተጎጂዎች ቤተሰብ አባላት እና የአካባቢው የቤተክርስቲያን ኃላፊዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሌላ ከፍተኛ የቤተ ክርስቲያን ኃላፊ ደግሞ "አባ ጀማ" በተባለው አካባቢ ከተፈጸመው ጥቃት ጋር በድምሩ "17 ሰዎች" መገደላቸውን ገልጸዋል።
አርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ ጥቅምት 17/2018 ዓ.ም. ሌሊት በተፈፀመ ጥቃት ደግሞ "ሦስት ሰዎች" መገደላቸውንም ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች አስረድተዋል።
በማግሥቱ ማክሰኞ ሌሊት አምስት ሰዓት ገደማ ላይ ደግሞ ሌላኛው የአርሲ ዞን ወረዳ በሆነው ሆንቆሎ አቤ ሦስተኛ ጥቃት መፈጸሙን ሁለት ምንጮች ተናግረዋል።
በዚህ ጥቃት "አምስት ሰዎች" መገደላቸውን የሚገልጹት አንድ ወረዳው ቤተ ክርስቲያን ኃላፊ፤ ሟቾቹ "የአንድ ቤተሰብ አባላት" መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የተጎጂ ቤተሰብ አባላት እና የቤተ ክርስቲያን ኃላፊዎች ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች "በሃይማኖታቸው ምክንያት ዒላማ ተደርገዋል" የሚል እምነት አላቸው። በአካባቢው ተደጋጋሚ መሰል ጥቃቶች መፈጸማቸውንም ለዚህ በማሳያነት ይጠቅሳሉ።
ከመጀመሪያው ጥቃት በኋላ የጉና ወረዳ ባለሥልጣናት ጥቃቱ ወደ ተፈጸመበት አካባቢ ተጉዘው በታጣቂዎች ላይ "የአጸፋ እርምጃ" ስለመውሰዳቸው ሪፖርት እንደደረሳቸው አንድ ከፍተኛ የቤተ ክርስቲያን ኃላፊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የሆንቆሎ ዋቤ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሐሰን መሐመድ ረቡዕ ዕለት በወረዳው ስለተፈጸመው ጥቃት ከቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ለቀረበላቸው ጥያቄ "አጣርተን በቂ መረጃ እንሰጣለን" ብለዋል።
በተመሳሳይ ቀን ስለ ጉዳዩ ጥያቄ የቀረበላቸው የአርሲ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኢብራሂም ከድር በበኩላቸው፤ "ሐሰት ነው" ሲሉ ተፈጽመዋል የተባሉትን ግድያዎች አስተባብለዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ ሐሙስ ምሽት ባወጣው መግለጫ በአርሲ ዞን በጥቅምት ወር ብቻ "ከ25 በላይ ሰዎች" መገደላቸውን አስታውቋል።