ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ግጭቶች ቆመው ለሰላም እና ለእርቅ ዕድል እንዲሰጥ አቡነ ማትያስ ጥሪ አቀረቡ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ አቡነ ማትያስ በአገር ውስጥ የሚታዩ ግጭቶች ቆመው ለሰላም እና እርቅ ዕድል እንዲሰጥ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የበኩሉን ጥረት እንዲያደርግ ጥሪ አቀረቡ።
ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ዐቢይ ጉባኤ መጀመሩን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕከት በአገር ውስጥ የሚታዩ የርስ በርስ ግጭቶች እንዲቆሙ እና ለሰላም እና ለእርቅ ዕድል እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
አቡነ ማትያስ ቤተክርስቲያን የገጠማትን ፈተና እና መወሰድ ያለባቸውን እርምጃዎች ባመለከቱበት በዚህ መልዕክታቸው ላይ "በአገራችን ያለው ያለመረጋጋት በሕዝባችን አጠቃላይ ሥነ ልቡና በአገሪቱ አንድነትና ዕድገት የሚያስከትለው ጫና በቀላሉ የሚታይ አይሆንም" ብለዋል።
አቡነ ማትያስ መልዕክታቸውን በመቀጠል ችግሩ እየታየ ያለው በዋናነት በአገራችን ፖለቲከኞች በመሆኑ ነገሩ የተወሳሰበና የተራዘመ እንዲሆን ማድረጉን ጠቅሰዋል።
"በመሆኑም ይህ የርስ በርስ ግጭት ቆሞ ችግሮችን በውይይትና በድርድር በመፍታት የወንድማማች እልቂት የሚያስቆም የሰላምና የዕርቅ ዕድል ቅድሚያ እንዲሰጠው ጉባኤው የበኩሉን ጥረት ማድረግ ይገባዋል" ሲሉ ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጥሪ አቅርበዋል።
አክለውም "የነገው ትውልድ ልማታዊ ተስፋ እውን ሊሆን የሚችለው ሰላምና አንድነት ሲኖር ነውና መንግሥት፣ ተፎካካሪ ፖለቲከኞችና ነፍጥ ያነሡ ወገኖች ሁሉ ለሰላም መስፈንና ለልማት ዕድገት መረጋገጥ ሲባል ወደ መግባባት እንዲመጡ" በማለት ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ዐቢይ ጉባኤ መጀመሩን አስመልክቶ ባስተላለፉት በዚህ መልዕከት ላይ በቤተክርስቲያን አመራሮች መካከል "ከሁሉም በላይ በውስጣችን የአንድነት ጉድለት በስፋት ይታያል" ሲሉ ተናግረዋል።
ፓትሪያርኩ በመልዕክታቸው ላይ ታይቷል ያሉት ክፍተት ሲዘረዝሩም "ለተሰየምንለት መለኮታዊ ተልዕኮ አንድ ሐሳብ፣ አንድ ቃል፣ አንድ ልብ ሆነን መሰለፍ ያለመቻል ክፍተት እየተንጸባረቀ ነው"ብለዋል።
ይህ ክፍተት የእምነቱን ተከታዮች በጥበብ እና በስልት ለማገልገል አለማስቻሉን የጠቀሱት አቡነ ማትያስ "ክፍተቱ የሚድያ ቀለብ" መሆኑን ጠቅሰዋል።
በእነዚህ ዐበይት ጉዳዮች እና በሌሎች ጉድለቶች ላይ "ፈጣን፣ ቆራጥ እና አዋጭ የሆነ ሥራ ካልሠራን ለወደፊት የቤተክርስቲያንን ኅልውና ጥያቄ ውስጥ" እንደሚከት ተናግረዋል።
ከዚህም ባሻገር የአገሪቱ የሰላም ሁኔታ "መቀዛቀዝ" ተጨማሪ ጉድለት በቤተክርስቲያን ላይ እያስከተለ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በአገሪቱ ባለው የሰላም እጦት የተነሳ የቤተክርስቲያኒቱ ተከታዮች "የመንፈስና የሥነ ልቡና ሰላም ማጣታቸውን" የጠቀሱት አቡነ ማትያስ፣ ለሞት፣ ለጉዳት፣ ሃብታቸው ለዝርፊያና ለውድመት መዳረጉንም ዘርዝረዋል።
"ይህም ሁሉ ሆኖ ፍትሕን እያገኙ አይደለም፤ አብያተ ክርስቲያናትም በምእመናን ፍልሰት እየተዘጉም እየተቃጠሉም ነው" ሲሉ ቤተክርስቲያን እና ምዕመኖቿ ላይ እየደረሰ ነው ያሉትን በመልዕክታቸው ላይ ጠቅሰዋል።
አቡነ ማትያስ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚሰነዘሩ "የስም ማጥፋት ዘመቻ" የቤተ ከርስቲያንን እምነት ከመንቀፍ እና ከማብጠልጠል አልፎ "የቅዱሳን ሥዕል በአደባባይ እስከ መቅደድ ተደርሷል" በማለት ከወራት በፊት በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የታዩ ክስተቶችን ጠቅሰዋል።
ሊቀ ጳጳሱ አክለውም የቤተ ክርስቲያኒቱ መለያ የሆኑ ንዋየ ቅድሳትና ልብሰ ተክህኖ፣ መዝሙርና ሥርዓተ አምልኮ በመጠቀም "ቤተ ክርስቲያናችንን በአደባባይ እየተዳፈሩ" ይገኛሉ ሲሉ ቤተክርስቲያኒቱ ገጠማት ያሉትን ወቅታዊ ችግር ገልፀዋል።
ይህ ድርጊት የአገሪቱን ሕገ መንግሥት "በቀጥታ የሚጻረር" ነው ያሉት አቡነ ማትያስ ሆኖም ግን በሕግ የሚጠይቅ እና የሚያስቆም አልተገኘም ብለዋል።
ቤተክርስቲያንም በዝምታ መመልከት የመረጠች መምሰሏን ያነሱት ፓትሪያርኩ "መፍትሔው ዝምታ ሳይሆን በሕግ አግባብ ነገሩን ለመፍታት መንቀሳቀስ እንደሆነ ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል" ብለዋል።