ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከበሮ እና ጽናጽልን ሌሎች ቤተ እምነቶች እንዳይጠቀሙ መከልከል ትችላለች?
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በሚያዝያ ወር መጀመሪያ "ከበሮ፣ ጸናጽል እና መቋሚያን" በአዕምሯዊ ንብረትነት ማስመዝገቧን ይፋ ስታደርግ በርካታ የእምነቱ ተከታዮች የቤተ ክርስቲያኗን ክብር እንዳይደፈር የሚያደርግ እርምጃ መሆኑ በመጥቀስ ድጋፋቸውን ችረዋል።
የቤተ ክርስቲያኒቱ መገናኛ ብዙኃን አገልግሎት፤ ምዝገባው በመካሄዱ እነዚህ መገልገያዎች "የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አዕምሯዊ ንብረት መሆኑ እንደተረጋገጠ" ዘግቧል።
ለጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን ወሳኝ የሕግ እርምጃ የሆነው ይህ ምዝገባ ይፋ መሆኑን ተከትሎ የተነሳው ጥያቄ እና ክርክር፤ 'ሌሎች ቤተ እምነቶችን እነዚህን መገልገያዎች እንዳይጠቀሙ ሊከለከሉ ይችላል?' የሚል ነው።
በአምልኮ ሥርዓቶቻቸው ላይ እንደ ከበሮ ያሉ መገልገያዎች ሲጠቀሙ በሚታዩት የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አማኞች እና በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች መካከል ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ምልልሶች ሲደረጉ ሰንብተዋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ የቤተ ክርስቲያኗ ኃላፊዎች ያላቸው አረዳድ እና የምዝገባ የምስክር ወረቀቱን የሰጠው የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን አቋም የተለያየ ነው።
የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ያስመዘገበችው ምንድነው?
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የቅርስ ጥበቃ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ ኃላፊ መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ እንደሚያስረዱት እነዚህን የቤተ ክርስቲያኗን ንዋየ ቅዱሳት የማስመዝገብ ሂደት የተጀመረው ከ2015 ዓ.ም. ነው።
የቤተ ክርስቲያኗ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ምዝገባው እንዲካሄድ ወሳኔ ያሳለፈው ቤተ ክርስቲኗ "የአምልኮ ሥርዓቷን የምታከናውንባቸው ንዋያተ ቅዱሳት በአሁን ሰዓት አንዳንድ አልባሌ ቦታዎች ላይ እየተገኙ፣ እየተጠቀሙ ያሉበት ሁኔታ" በመኖሩ እንደሆነ መልአከ ሰላም ዳዊት ገልጸዋል።
"መብትንም ከማስከበር አንጻር፣ ብጹዕናውንም ከማቆየት አንጻር የግድ መመዝገቡ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱንም" ተናግረዋል። በዚህም መሠረት ሚያዝያ 3/2017 ዓ.ም. ከአስር በላይ መገልገያዎች የምዝገባ ሂደታቸው መጠናቀቁን ተናግረዋል።
መልአከ ሰላም ዳዊት እንደሚያስረዱት ብዙዎችን ያነጋገሩት ከበሮ፣ ጽናጽል እና መቋሚያም የምዝገባ ሂደታቸው የተጠናቀቀው በዚሁ ዕለት ነው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ይህንን የምዝገባ ሂደት እንዳጠናቀቀች መግለጿን ተከትሎ በብዙዎች ዘንድ የተፈጠረው አረዳድ ቤተ ክርስቲያኗ "ለከበሮ፣ ለጽናጽል እና ለመቋሚያ የአዕምሮ ንብረት ማረጋገጫ እንዳገኘች" ነው።
ይሁን እንጂ ቤተ ክርስቲያኗ ያስመዘገበችው ከበሮ፣ ጽናጽል እና መቋሚያን ሳይሆን የእነዚህ መገልገያዎች "ንድፎች" ነው። እነዚህ የአዕምሯዊ ንብረቶች የተመዘገቡትም "በቅጂ (ኮፒራይት) እና ተዛማጅ መብቶች" ዘርፍ ስር ነው።
በቤተ ክርስቲያኗ የሕግ አገልግሎት መምሪያ ስር የሚገኘው የሕግ ባለሙያዎች ዐቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አያሌው ቢታኔ፤ በቤተ ክርስቲያኗን አዕምሯዊ ንብረቶች የማስመዝገብ ሂደት ውስጥ ተሳተፉ የሕግ ባለሙያ ናቸው።
አቶ አያሌው እንደሚገልጹት የከበሮ፣ የጽናጽል እና የመቋሚያ ንድፎች በአዕምሯዊ ንብረት እንዲመዘገቡ ማመልከቻ ሲቀርብ በእነዚህ የአምልኮ መሳሪያዎች ንድፍ ላይ ያሉ ምልክቶች ምን ዓይነት ተምሳሌትነት እና ሃሳብ እንደያዙ በዝርዝር መቅረቡን አስረድተዋል።
የሕግ ባለሙያው፤ ቤተ ክርስቲያኗ የምትጠቀምበትን "ጠባብ እና ሰፊ" ጎኖች ያሉትን ከበሮ በማሳያነት ያነሳሉ።
"[የከበሮው ንድፍ ኢየሱስ ክርስቶስ] 'በጠባብ ደረት ተወሰነ' የሚለውን ነገር የሚያሳይ፣ ሙሉ የሆነው የዓለማት ገዢ መሆኑን የሚያሳይ፤ በተጨማሪም ደግሞ ቀይ፣ ከቀለምም አንጻር የምትጠቀመው ቀለም አላት። ከለላው ደግሞ ግርፋቱን የምታሳይበት፤ ቆዳ ራሱ የምትጠቀምበት ምክንያት አለው። እነዚህን ሃሳቦች በሙሉ ያካተተ ንድፈ ሀሳብ ነው" ሲሉ የንድፉን ተምሳሌታዊነት አብራርተዋል።
የቅጅ እና ተዛማጅ መብት ምንድነው?
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የአዕምሯዊ ንብረቶች የተመዘገቡበት "የቅጅ (ኮፒራይት) እና ተዛማጅ መብቶች" ዘርፍ ምንነት ለመረዳት 'የአዕምሯዊ ንብረት ምንድነው?' ከሚለው እንነሳ።
የአዕምሯዊ ንብረት የሚባሉት "በሰው ልጅ አዕምሮ የሚፈጠሩ የፈጠራ ሥራዎች" ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ በሦስት ዘርፎች የአዕምሯዊ ንብረት ምዝገባ ይደረጋል።
የመጀመሪያው የአዕምሯዊ ንብረት "ቴክኒካዊ ባህሪ" ባለው የፈጠራ ሥራ ላይ "ብቸኛ የፈጠራ ባለቤትነት መብት" የሚያሰጠው "ፓተንት" ነው። ሁለተኛው ደግሞ አንድ ምርት እና አገልግሎት ከሌላው እንዲለይ በልዩ ምልክትነት የሚመዘገበው "የንግድ ምልክት" ነው።
ሦስተኛ እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ምዝገባ ያደረገችበት የአዕምሯዊ ንብረት ዘርፍ ደግሞ የቅጅ እና ተዛማጅ መብቶች (Copyright and Neighbouring Rights) የሚባለው ነው።
አቶ ኤልያስ ጥሩነህ በአእምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን፤ የአእምሯዊ ደንበኞች የጉዳይ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ናቸው። ለቤተ ክርስቲያኗ በተሰጠው የምዝገባ ምስክር ወረቀት ላይ ያረፈው ስም እና ፊርማ የእኚሁ ኃላፊ ነው።
መሪ ሥራ አስፈጻሚው እንደሚያስረዱት፤ "የቅጅ እና ተዛማጅ መብቶች" የተባለው የአዕምሯዊ ንብረት ዘርፍ ከሌሎቹ ሁለት ዘርፎች የተለየ ነው። ፓተንት "ለፈጠራ ሥራ" (Innovation) መብት የሚሰጥ መሆኑን የሚያስረዱት አቶ ኤልያስ፤ ኮፒራይት ደግሞ "የኪነ ጥበባዊ ሥራን" (creative work) መብት የሚያስጠብቅ መሆኑን ይገልጻሉ።
በቀላል አገላለጽ፤ አንድ ሰው ለመጀሪያ ጊዜ ከበሮ የተባለን መሳሪያ ቢሠራ በፓተንት ማስመዝገብ ይችላል። ሌላ ግለሰብ ደግሞ ከበሮ ለተባለው መሳሪያ አዲስ ኪነ ጥበባዊ ንድፍ ቢሠራ የቅጅ እና ተዛማጅ መብቶችን ማስጠበቅ ይችላል።
በቅጅ እና ተዛማጅ መብቶች እንዲሁም በሌሎቹ የአዕምሯዊ ንብረቶች መካከል ያለው ልዩነት ይህ ብቻ አይደለም። አንድን አዕምሯዊ ንብረት በቅጅ እና ተዛማጅ መብቶች ማስመዝገብ እንዲሁም በፓተንት ዘርፍ ማስመዝገብ የሚሰጠው ክብደት የተለያየ መሆኑንም አቶ ኤልያስ ይገልጻሉ።
አቶ ኤልያስ እንደሚያስረዱት አንድ የአዕምሯዊ ንብረትን በፓተንት የሚመዘገበው ፈጠራው "በዓለም አቀፍ ደረጃ አዲስ ስለመሆኑ" ከተረጋገጠ በኋላ ነው። ይህ የሚረጋገጠውም የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ባለሙያዎች በሚያደርጉት ምርመራ መሆኑ ይናገራሉ።
መሪ ሥራ አስፈጻሚው፤ "መርማሪ ባለሙያዎች ናቸው 'ይሄ የእገሌ ይሁን' ብለው የሚወስኑት፤ ኃላፊነትም ይወስዳሉ። መሥሪያ ቤቱም ለሰጠው ሥራ ኃላፊነት ይወስዳል ማለት ነው" ሲሉ የፓተንት ምዝገባ የባለቤትነት መብትን የሚያረጋግጥ መሆኑን ያስረዳሉ።
አንድ የአዕምሯዊ ንብረት ፈጣሪ ለሥራው የፓተንት የባለቤትነት መብት የሚያገኘው ይህንን ምዝገባ ሲያደርግ ብቻ መሆኑን ይገልጻሉ።
በቅጅ እና ተዛማጅ መብቶች ስር የሚወድቁ ሥራዎች በተቃራኒው መብታቸው መከበር የሚጀምረው በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ከተመዘገቡበት ጊዜ አንስቶ ሳይሆን፤ ባለቤቱ ሥራውን "በሠራበት ሰዓት እና ለሕዝብ ባቀረበበት ጊዜ መብቱ የተጠበቀ" እንደሚሆን አቶ ኤልያስ ይገልጻሉ።
በ1996 ዓ.ም. የወጣው "የቅጅ እና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ" አዋጅ አንድ ሥራ በዚህ ዘርፍ የመብት ጥበቃ ለማግኘት የሚያስፈልገው "ወጥ (ኦርጅናል)" መሆን እንዲሁም ሥራው "የተቀረጸ ወይም ግዙፍነት ያገኘ" መሆን ብቻ እንደሆነ ደንግጓል።
አዋጁ፤ እነዚህ መመዘኛዎች ከተሟሉ "ሥራውን በማውጣት ምክንያት ብቻ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ [ሥራው] ጥበቃ ያገኛል" ሲል አስፍሯል።
ይህም ማለት ለምሳሌ፤ አንድ ሙዚቀኛ በሠራው ዘፈን ላይ የኮፒራይት መብት እንዲጠበቅለት ለማድረግ የግድ ሥራውን ማስመዝገብ አይጠበቅበትም። ሙዚቃው ከተቀረጸበት እና ለሕዝብ ከቀረበበት ጊዜ ጀምሮ መብቱ ይጠበቅለታል።
ግለሰቡ የኮፒራይት መብቱ ሥራውን ይፋ ካደረገበት ጊዜ ጀምሮ የሚጠበቅለት ቢሆንም የሥራው ብቸኛ ባለቤት የመሆኑን ጉዳይ ማረጋገጥ ከፈለገ ግን መሄድ ያለበት ወደ ፍርድ ቤት እንደሆነ አቶ ኤልያስ ይናገራሉ።
የእሳቸው ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት በቅጅ እና ተዛማጅ መብቶች የሚያደርገው ምዝገባ እና የሚሰጠው የምስክር ወረቀት፤ አስመዝጋቢው አካል የሥራው "ባለቤት ስለመሆኑ የሚያረጋግጥ አይደለም" ይላሉ።
እንደ አቶ ኤልያስ ገለጻ ይህ የሆነው የኮፒራይት ምዝገባ ሂደት፤ እንደ ፓተንት ምዝገባ ምርመራ ስለማይደረግበት ነው። በ2006 ዓ.ም. የወጣው "የቅጅ እና ተዛማጅ መብቶች የሚያስገኙ ሥራዎች ምዝገባ" ደንብም ይህንን ያስረዳል።
ደንቡ፤ በቅጅ እና ተዛማጅ መብቶች የሚደረግ ምዝገባ ሲካሄድ መስፈርቶች መሟላታቸውን ለማረጋገጥ "የፎርማሊቲ ምርመራ" እንደሚካሄድ የሚገልጽ ሲሆን፣ "የሥረ-ነገር ምርመራ" ግን እንዳማይካሄድ አስፍሯል።
አመልካቹ የሥራው ባለቤት መሆኑን ለማረጋጥ የሚጠየቀው "ቃለ መሃላ" ብቻ እንደሆነ ደንቡ ደንግጓል። አቶ ኤልያስም በተመሳሳይ፤ "እኛ [አንድን ሥራ በኮፒራይት] ስንመዘገብ የቀረበልንን ማስረጃ መርምረን፤ 'አዲስ ነው አዲስ አይደለም?' የሚለውን አይተን አይደለም" በማለት "ባለ መብት ነኝ" በሚል ለሚመጣ አካል ምዝገባ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
መሥሪያ ቤቱ በኮፒራይት ዘርፍ የሚያደርገው ምዝገባ የሚያረጋግጠው አመልካቹ አካል "ሥራውን በማስመዝገብ ቀዳሚው መሆኑን" እንደሆነ አክለዋል።
የተመዘገበው ሥራ "አዲስ ነው አይደለም፣ የነበረ ነው አይደለም የሚለውን ሊወስን የሚችለው ፍርድ ቤት ነው" የሚሉት አቶ ኤልያስ፤ ምዝገባ ያደረገ አካል የሚሰጠውን የምስክር ወረቀት በፍርድ ቤት እንደ ማስረጃ ሊጠቀምበት እንደሚችል ገልጸዋል።
"[የምዝገባ ሰርቲፊኬት] 'እንደ ማስረጃ ይቀርባል' ማለት ግን ፍርድ ቤቱ የቀረበለትን ነገር በሙሉ ልክ ነው ብሎ ይወስናል ማለት አይደለም። እዚያ ጋር የግንዛቤ ችግር አለ። እዚህ የተመዘገበ ነገር በሙሉ፤ በተለይ በቅጅ መብት የተመዘገበን ነገር ሙሉ በሙሉ መብቱ እንደተገኘ አድርጎ ማሰብ ትክክል አይደለም፤ ሕጉም እንደዚያ አይፈቅድም" ሲሉ አብራርተዋል።
የቅጅ እና ተዛማጅ መብቶች ምን ዓይነት ጥበቃዎች ያስገኛል?
የቅጅ እና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ የወጣው ከ21 ዓመት በፊት በ1996 ዓ.ም. ነው። በዚህ አዋጅ መሠረት የቅጅ እና ተዛማጅ መብቶችን የሚያስገኙ ሥራዎች "የኢኮኖሚያዊ መብቶች" እና "የሞራል መብት" ጥበቃ ያገኛሉ።
"ኢኮኖሚያዊ መብቶች" የሚባሉት ሥራውን በማባዛት፣ በማሠራጨት፣ በማከፋፈል፣ "ወደ ሌላ ዓይነት በመቀየር" እና በሌሎች መንገዶች የሚገኝ የኢኮኖሚ ጥቅምን የሚመለከት ነው። እነዚህ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚያስገኙ ድርጊቶችን "የመፈጸም እና ሌላ ሰው እንዲፈጽማቸው የመፍቀድ ብቸኛ መብት" የሥራው ባለቤት እንደሆነ አዋጁ ላይ ሰፍሯል።
"የሞራል መብት" ደግሞ ከኢኮኖሚያዊ ጥቅም ጋር የተለየ እንደሆነ የባለሥልጣኑ ደንበኞች የጉዳይ መሪ ሥራ አስፈጻሚው አቶ ኤልያስ ይገልጻሉ።
ይህ የመብት ዓይነት፤ "[የሥራውን አመንጪ] ሥራውን ማንም አልፎ እንዳይነካበት፣ እንዳያስተካክልበት ወይም ደግሞ በሌላ እንዳይተረጉምበት፣ የተለያዩ ሞራልን ሊነኩ የሚችሉ ተግባራት እንዳይደረግበት የሚከለክል ነው" በማለት ያስረዳሉ።
በአዋጁ መሠረት በሞራል መብትነት ከተዘረዘሩት መካከል "ክብሩን እና መልካም ስሙን የሚያጎድፍ የሥራ መዛባት፣ መቆራረጥ ወይም በሌላ መልክ መቀየርን የመቃወም" መብት ይገኝበታል።
የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ያገኘችውን ምዝገባ የመብት ጥበቃው መጀመሪያ አድርገው የሚቆጥሩት የቤተ ክርስቲያኗ የሕግ ባለሙያዎች ዐቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አያሌው፤ ከአሁን በኋላ ቤተ ክርስቲያኗ በተመዘገቡት መገልገያዎች ላይ የሚኖራትን መብት ማስከበር እንደምትጀምር ገልጸዋል።
የቤተ ክርስቲያኗ የቅርስ ጥበቃ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ ኃላፊ የሆኑት መልአከ ሰላም ዳዊትም ይህንን ሀሳብ ይጋሩታል። "ቤተ ክርስቲያኒቷ የከበሮ፣ የጽናጽል፣ የተለያዩ ንዋያተ ቅዱሳቷን የምታመርትበት እና የምታዘጋጅበት የራሷ የሆነ ተቋም ሊኖራት ይገባል። ያንን ለማድረግ በዝግጅት ላይ ነው ያለችው" ሲሉ የቤተ ክህነቱን ዕቅድ አስረድተዋል።
ከማምረቻው መቋቋም በኋላ እንደ ከበሮ፣ ጽናጽል እና መቋሚያ ያሉ መገልገያዎችን "ቤተ ክርስቲያኗ ፈቅዳ እውቅና ከምትሰጠው አካል ውጪ፤ ቤተ ክርስቲያኗ ሳታውቅ ማንም ማምረት አይችልም፣ ከዚያ ውጪም ማሠራጨት አይችልም" ሲሉ ኢኮኖሚያዊ መብቶቹ የሚከበሩበትን አግባብ ገልጸዋል።
ከበሮ እና ሌሎች ቤተ እምነቶች
መልአከ ሰላም ዳዊት እና አቶ አያሌው ከአዕምሯዊ ንብረት ምዝገባው ጋር በተያያዘ በዋነኝነት የሚያነሱት "እንደ ከበሮ ያሉ የቤተ ክርስቲያኗን የአምልኮ መፈጸሚያ መሳሪያዎች ሌሎች አካላት እየተጠቀሙባቸው ነው" የሚለውን ሀሳብ ነው።
እነዚህ መሳሪያዎች "ራሱን የቻለ ሥርዓት፣ ምሳሌ፣ ትርጉም ያላቸው የአገልግሎት መፈጸሚያ ቅዱስ እቃዎች" መሆናቸው የሚናገሩት መልአከ ሰላም ዳዊት፤ "ይህንን ቅዱስ እቃ የራሱ ያልሆነ አካል የራሱ እንደሆነ አስመስሎ ለመጠቀም ሲሞክር" የቤተ ክርስቲያኗን "መብቷንም እንደሚጋፋ" ገልጸዋል።
"ሁሉም ሰው ብድግ አድርጎ እንደፈለኩ ልጠቀምበት እያለ ያለበት፣ እንደ ፈለገውም ደግሞ ቅርጹንም እየቀያየረ ላዘጋጀው እያለ ቤተ ክርስቲያኒቷንም ስም ለማጠልሸት የሚጠቀበት፣ የቤተ ክርስቲያኒቷ አካል ሳይሆኑ መስለው ምዕመናንን የማደናገር ሥራ የሚሠሩበት ሁኔታዎች እየተፈጠሩ በምጣታቸው ቤተ ክርስቲያኒቷ ይህንን ለማስተካከል ነው እየሠራች ያለችው" ሲሉም የተፈጠረውን ስጋት ያብራራሉ።
አሁን የተደረገው ምዝገባም እንደ ከበሮ ያሉትን ንዋያተ ቅዱሳን "ያለምንም ፈቃድ ቤተ ክርስቲያኗ ሳታውቅ" ለመጠቀም "የሚያስብ አካል ካለ ቤተ ክርስቲያኒቱ በሕግ አግባብ የመጠየቅ መብት" እንደሚያጎናጽፋት ይናገራሉ።
የቤተ ክርስቲያኗ የሕግ ባለሙያዎች ዐቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢው አቶ አያሌውም ተመሳሳይ ሀሳብ ያነሳሉ። ምዝገባ በተደረገባቸው ንድፎች የተዘጋጁ እንደ ከበሮ፣ ጽናጽል እና መቋሚያ ያሉትን መገልገያዎች "ማን እና እንዴት መጠቀም እንዳለበት መወሰን የምትችለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ነች" ይላሉ።
ቤተ ክርስቲያኗ ሁለት መንገዶችን በመጠቀም ሌሎች ቤተ እምነቶች እነዚህን መገልገያዎች እንዳይጠቀሙ ማድረግ እንደምትችል የሕግ ባለሙያው አቶ አያሌው ይገልጻሉ። በቀዳሚነት የሚጠቅሱት በኢኮኖሚያዊ መብቶች ውስጥ የሚካተቱትን የማባዛት፣ የማሠራጨት እና የማከፋፈል ብቸኛ መብቶችን መጠቀምን ነው።
በዚህ መሠረት ቤተ ክርስቲያኗ እነዚህን መገልገያዎች "ለማን መሸጥ እንዳለባቸው" እንደምትወስን ተናግረዋል።
"'ይህንን መጠቀም የምትችለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በስሯ ያሉት ተቋማት ብቻ ናቸው' ብላ ምን ማድረግ እንዳለባት መወሰን የምትችለው እሷ ነች ማለት ነው" ሲሉ ሀሳባቸውን ያጠናክራሉ።
ሁለተኛው መንገድ ደግሞ በአዋጁ ላይ የተጠቀሰው እና በሞራል መብት ውስጥ የተካተተውን "ክብሩን እና መልካም ስሙን የሚያጎድፍ የሥራ መዛባት፣ መቆራረጥ ወይም በሌላ መልክ መቀየርን የመቃወም" በሚል ለሥራው ባለቤት የተሰጠው መብት ነው።
ንድፎቹ ሲመዘገቡ "ለምን ዓላማ እና እንዴት መዋል እንዳለባቸው በግልጽ መቀመጡን" የሚናገሩት አቶ አያሌው፤ "ያሬዳዊ ቃና የሌለው ሌላ ቤተ እምነት 'ቁሱን ገዝቼዋለሁ እና እንደፈለግሁ መጠቀም እችላለሁ' ማለት አይችልም" በማለት ይከራከራሉ።
ይህ የሚሆን ከሆነ፤ "ቤተ ክርስቲያኗ ለይታ ያስቀመጠችውን ንድፈ ሀሳብ መሠረት ያላደረገ ሕገ ወጥ የሆነ አጠቃቀም ነው" በሚል መቃወም እንደሚቻል ያስረዳሉ። "መቋሚያውም ከተጠቀመጠለት ንድፈ ሀሳብ ውጪ ከዋለ የቤተ ክርስቲያኗ ዓላማ ተጻራሪ ነው ማለት ነው" ሲሉ ይህ ዓይነቱ ድርጊት በአዋጁ ላይ በሞራል መብቶች ስር የተቀመጠውን የቤተ ክርስቲያኗን መብት "እንደሚጋፋ" ይናገራሉ።
በአእምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን፤ የአእምሯዊ ንብረት ደንበኞች የጉዳይ መሪ ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት የአቶ ኤልያስ ጥሩነህ እንዲሁም የሕግ ባለሙያ እና አእምሯዊ ንብረት ምዝገባ ወኪል የሆኑት አቶ ኤልያስ ፍቅሩ ግን በዚህ ሃሳብ አይስማሙም።
ለቤተ ክርስቲያኗ በተሰጠው የምዝገባ ምስክር ወረቀት ላይ ስም እና ማህተማቸው የሚገኘው የባለሥልጣኑ የደንበኞች ጉዳይ መሪ ሥራ አስፈጻሚው አቶ ኤልያስ፤ "በገበያ ላይ ያለን ንብረት አትጠቀሙ ማለት ማንም አይችልም። ይሄ ያንን መብት የሚሰጥ አይደለም" ይላሉ።
ይህ ዓይነቱ መብት የሚገኘው የፓተንት መብት ምዝገባ በተደረገበት ሥራ ላይ መሆኑን አቶ ኤልያስ ይናገራሉ።
"የፓተንት መብቱን ያስመዘገበው ሰው ከሆነ ያንን 'ማንም አይጠቀም' ማለት ይችላል። በዚያ ዓይነት መልክ የተፈጠረን ነገር በሙሉ መከልከል ይችላል። ተመርምሮ፣ ለእርሱ ብቻ ተብሎ የተሰጠ እና የተወሰነለት ስለሆነ ሕጉም ስለሚፈቅድለት" ሲሉ ያስረዳሉ።
አሁን ምዝገባ የተደረገበት የኮፒራይት ዘርፍ ግን "እውቀቱን" እንጂ "ንብረትን" መሠረት ያደረገ እንዳልሆነ ያነሳሉ። "ይሄንን ዲዛይን 'ከእኔ ውጪ ማን አባዛ አለህ?' ማለት ይችላል። ከበሮ 'መጠቀም አትችልም' ግን ማለት አይቻልም" ሲሉ ልዩነቱን ያብራራሉ።
መሪ ሥራ አስፈጻሚው አቶ ኤልያስ ከሞራል መብት ጋር የሚነሳውን ክርክርም አይቀበሉትም። "ይሄ intellectual ንብረት ነው። intellectual ንብረቱ፤ ዲዛይኑ ነው እንጂ ከበሮው አይደለም" ይላሉ።
የሞራል መብት ጥያቄ የሚነሳው፤ ንድፉ ወደ ከበሮ ወይም ሌላ ቁስነት በሚቀይርበት እና በሚባዛበት ወቅት የሚፈጠርን "የሥራ መዛባት፣ መቆራረጥ ወይም በሌላ መልክ መቀየርን" በተመለከተ መሆኑንም ያስረዳሉ።
አቶ ኤልያስ፤ "እኔ ልጠይቅህ የምችለው በሰጠውህ ዲዛይን መሠረት ካልተሠራ ወይም የጨመርክበት ነገር ካለ 'ለምን ይህንን ጨምርክ? የእኔ ዲዛይን ዓላማ ይህ ነው፤ ስለዚህ አሳስተህብኛል ሞራሌን ነክተሃል' ብዬ ልጠይቅ እችላለሁ" ሲሉ ይህ መብት ተግባራዊ የሚሆንበትን አግባብ አመልክተዋል።
"የሠራሁት ዲዛይን 'ለእንደዚህ ዓይነት ዓላማ የሚውል ከበሮ ነው፤ ስለዚህ በእንደዚህ ዓይነት ቦታ ላይ ስለተጠቀማችሁት' ተብሎ ያንን መብት ተግባራዊ ማድረግ አይችልም። ሲጀመርም ያ መብት አልተሰጠውም" ይላሉ።
"የሞራል መብት ያለው ዲዛይኑ ላይ ነው" የሚሉት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፤ በዚያ ንድፍ የተሠራ ቁስ የሚውልበት ዓላማ በገዢው ፍላጎት እንደሚወሰን ይጠቅሳሉ። አቶ ኤልያስ፤ "ሰውን ይህንን ጉዳይ ለዚህ ነገር ብቻ ተጠቀምበት ብለህ ብትሰጠው ሲጀመር አይቀበልህም፣ የሚከለክል ሕግም የለም" በማለት ይደመድማሉ።
ከዚህ ቀደም በአዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን የኮፒራይት መዝገባ ባለሙያ ሆነው የሠሩት የሕግ ባለሙያ እና የአዕምሯዊ ንብረት ምዝገባ ወኪሉ አቶ ኤልያስ ፍቅሩም ይህንኑ መከራከሪያ ይደግፋሉ። የሕግ ባለሙያው፤ በንድፎቹ ላይ ያለ የኮፒራይት መብት ሌሎች ቤተ እምነቶች ቁሱን ለመጠቀም ያላቸውን መብት "በፍጹም አይገድብም" ይላሉ።
"አሁን የተሰጠው የምዝገባ የምስክር ወረቀት በተለይ የኮፒራይት ምዝገባ ነው። ይሄ የኮፒራይት ምዝገባ ደግሞ የተመዘገበውን ቁስ መጠቀምን፣ አገልግሎት ላይ ማዋልን ክልከላ የሚጥል አይደለም። ከህትመት፣ ከማሠራጨት፣ ከማባዛት ጋር የተያያዘ ነው" ሲሉ ተመሳሳይ ሀሳብ አንስተዋል።
የተመዘገቡት ቅርሶች ጥንታዊነት እና የኮፒራይት የቆይታ ጊዜ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ባገኘቻቸው የምስክር ወረቀቶች ላይ "የሥራ አመንጪ" ተብለው የተጠቀሱት ሁለት አካላት ናቸው፤ ራሷ ቤተ ክርስቲያኗ እና ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ።
የቤተ ክርስቲያኗ የቅርስ ጥበቃ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ ኃላፊው መልአከ ሰላም ዳዊት፤ የተመዘገቡት አዕምሯዊ ንብረቶች "ከየት መጣነቱን እና እስከአሁን ያለውን ሂደት" ለማጥናት የተቋቋመው ኮሚቴ የተመራው በብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ እንደሆነ ይናገራሉ።
በምስክር ወረቀቱ ላይ የእኚህ አባት ስም የሰፈረው በምዝገባው ሂደት ላይ ከቤተ ክርስቲያኗ በተጨማሪ "ያንን የሚያስተዳድረው፣ የሚመራው አካል" በማስፈለጉ እንዲሁም ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ "በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውክልና የተሰጣቸው የኮሚቴው ሰብሳቢ" በመሆናቸው እንደሆነ ያስረዳሉ።
በአዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን፤ የአዕምሯዊ ንብረት ደንበኞች የጉዳይ መሪ ሥራ አስፈጻሚው አቶ ኤልያስ ጥሩነህም፤ የኮፒራይት መብትን ለማስጠበቅ የግለሰብን አስፈላጊነት ያስረዳሉ።
ኮፒራይት የሚጠበቀው ከአዕምሮ ለመነጨ ሥራ እንደሆነ የሚያስታውሱት አቶ ኤልያስ፤ "ድርጅት አዕምሮ ስለሌለው ማመንጨት አይችልም" ይላሉ። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ኢኮኖሚያዊ መብቶች እና ሞራላዊ መብቶች ለሁለት አካላት ተከፋፍሎ እንደሚሰጥ ያስረዳሉ።
ተቋሙ፤ የሥራውን ኢኮኖሚያዊ መብት ሲወስድ፤ "የስሜት ጉዳይ" የሆነው የሞራል መብት ደግሞ ሥራውን የፈጠረው ሰው ሆኖ ይቆያል። የሞራል መብት ለተቋማት የሚተላለፍ እንዳልሆነም ያክላሉ።
በአንድ የፈጠራ ሥራ ላይ የሚኖር የኮፒራይት መብት ተጠብቆ የሚቆይበት ጊዜ የተወሰነ እንደሆነ የቅጅ እና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ ያስረዳል።
አዋጁ፤ ኢኮኖሚዊ መብቶች ፀንተው የሚቆዩት "የሥራው አመንጪ በሕይወት በሚቆይበት ዘመን" እንደሆነ አስፍሯል። ግለሰቡ ከሞተ በኋላ ደግሞ ወራሾች "እስከ 50 ዓመታት" መብቱ እንደሚጸናላቸው ያስረዳል።
የሞራል መብቶች የቆይታ ጊዜም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው። በአዋጁ መሠረት የሞራል መብቶች የሚቆዩት "የሥራ አመንጪው ከሞተ በኋላ ኢኮኖሚያዊ መብቶች ፀንተው [እስከ]ሚቆዩበት ጊዜ" ድረስ ነው።
አንድ የአዕምሮ ንብረት የኮፒራይት ጥበቃ የሚያገኘው ከፈጠረው አዕምሮ ጋር በተያያዘ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ኤልያስ፤ በዚህም ምክንያት የኢኮኖሚ መብቱ ለተቋም ቢተላለፍ እንኳ ግለሰቡ ሕይወቱ ካለፈ በኋላ ከለላ የሚያገኘው ለ50 ዓመታት ብቻ እንደሆነ ያብራራሉ።
ከግለሰቡ ሞት 50 ዓመታት በኋላ የፈጠራ ሥራው "የሕዝብ ሀብት" እንደሚሆን መሪ ሥራ አስፈጻሚው ይገልጻሉ።
አቶ ኤልያስ፤ "የሕዝብ ሀብት ማለት፣ ያ ዓይነት ዲዛይን ወይም በዚያ ዲዛይን የተሠራው ከበሮ የሕዝብ ነው። ኢኮኖሚያዊም ሞራላዊ መብትም ባለቤት የላቸውም፤ የሚጠብቃቸው የለም" ሃሳቡን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ካስመዘገበቻቸው የከበሮ፣ የጽናጽል እና የመቋሚያ ንድፎች ጋር ተያይዞ የሚነሳው አንዱ ክርክር የንድፎቹ ጥንታዊነት ነው።
በአዋጁ መሠረት ኮፒራይት የሚፀናበት ሥራውን በሠራው ሰው በሕይወት እስካለ እና ከዚያ በኋላ በሚኖሩ 50 ዓመታት መሆኑ፤ አሁን ምዝገባ ያገኙት ንድፎች የጥበቃ ጉዳይ ጥያቄ ሊያስነሳ እንደሚችል የሕግ ባለሙያ እና የአዕምሯዊ ንብረት ምዝገባ ወኪሉ አቶ ኤልያስ ፍቅሩ ይስማሙበታል።
በሕግ ባለሙያው አቶ ኤልያስ ማብራሪያ መሠረት፤ ቤተ ክርስቲያኗ ሕጋዊ ተቋም በመሆኗ "የፈጠራ መብት [የሚያስገኝ ሥራ] በቀጥታ አትሠራም"፤ ይህንን ዓይነት መብት የሚያስገኝ ሥራ የሚፈጥሩ "በውስጧ ያሉ ባለሙያዎች" ናቸው።
በእንደዚህ ዓይነት መልኩ የተሠራ አንድ ፈጠራም በቅጅ እና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ የሚኖረው ሥራውን ባከናወነው "የተፈጥሮ ሰው" ምክንያት እንጂ "አርቴፊሻል ሰውነት ባላቸው ተቋማት" ምክንያት እንዳልሆነ የሕግ ባለሙያው አቶ ኤልያስ ያስረዳሉ።
በዚህም የተነሳ የመብት ጥበቃው የሚቆየው ሥራውን ባከናወነው ሰው ዕድሜ ዘመን እና ከዚያ በኋላ ለሚኖሩ የ50 ዓመታት እንደሆነ ይናገራሉ።
"[ንድፉን] የሠራው ሰው መብቱን የሚያስተላልፈው ወደ ቤተ ክርስቲያኗ ነው። ስለዚህ መቆጠር የሚጀምረው ያ ሰው ከሠራበት ጊዜ ጀምሮ በዕድሜ ዘመኑ እና 50 ዓመት ጥበቃ አለው። [...] ቤተ ክርስቲያኗ መብቱን የምታገኘው ከዚያ ሰው ስለሆነ፤ ያ ሰው የሌለውን መብት ደግሞ ማግኘት ስለማትችል የመብት ጥበቃው ከዚያ አያልፍም። በዚህ መስመር ከሄድን 'ንድፉ መቼ ተሠራ?' የሚል ጥያቄ ያመጣል ማለት ነው" በማለት የሕግ ባለሙያው ያብራራሉ።
አክለውም የአንድ ሥራ የኮፒራይት መብት ጥበቃ የሚፀናበት ጊዜ ሲጠናቀቅ የሕዝብ ሀብት እንደሚሆን ያስታውሳሉ። አንድ ሥራ "የሕዝብ ሀብት" ከሆነ በኋላ በድጋሚ "ባለቤትነት (ownership) ሊቋቋምበት" እንደማይችልም ያነሳሉ።
"አንዴ የሕዝብ ሀብትነት (public domain) ውስጥ የገባውን ፈጠራ ማሻሻያ እስካላደረግክበት ድረስ እንደገና አንስተህ ባለቤትነት (ownership) ልታቋቁምበት አትችልም። ያደረግከው ማሻሻያ ደግሞ የፈጠራ ክህሎትን የሚጠይቅ መሆኑ ሲታመንበት ነው እንደገና 'ለምዝገባ ብቁ ነው' ተብሎ ባለቤትነት የሚሰጠው" ሲሉ ሙግቱን ያስረዳሉ።
በአእምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን፤ የደንበኞች ጉዳይ መሪ ሥራ አስፈጻሚው አቶ ኤልያስ ጥሩነህ ይህ ሀሳብ ሲነሳላቸው፤ "የኮፒራይት ምዝገባ ሲከናወን የስረ ነገር ምርመራ አይከናወንም" የሚለውን አሠራር በድጋሚ ያስረዳሉ።
ይህ ንድፍ "አዲስ ነው ወይስ የነበረ?" የሚለውን የሚወስነው ፍርድ ቤት እንደሆነ አጽንኦት ይሰጣሉ።
"ይሄ ዲዛይን 'የጥንት ነው' የሚባል ከሆነ፤ 'ይሄ የጥንት ዲዛይን ነው፤ አዲስነት የለውም' የሚል አካል በፍርድ ቤት መጠየቅ ይችላል። ያ በፍርድ ቤት ተመርምሮ ውሳኔ የሚሰጥበት ስለሆነ። እኛ የምንመዘግበው መብትን የሚያስጨብጥ አይደለም" ሲሉ የሥራውን አዲስነት የመበየን ኃላፊነት የፍርድ ቤት መሆኑን ያስረግጣሉ።