በአርሲው ጥቃት እናት እና ሦስት ልጆችን ጨምሮ ስምንት ሰዎች የተገደሉበት ቤተሰብ

በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ውስጥ በአንድ ሳምንት ውስጥ በተፈጸሙ ጥቃቶች ሕጻናትን ጨምሮ "25 ሰዎች" መገደላቸውን የተጎጂዎች ቤተሰቦች እና በአካባቢው የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ኃላፊዎች ተናገሩ።

ባለፈው ሳምንት ረዕቡ እና ሐሙስ ዕለት በተፈጸመው የመጀመሪያው ጥቃት ከተገደሉ ሰዎች ውስጥ "ስምንቱ የአንድ ቤተሰብ አባላት" እንደሆኑ ሦስት ምንጮች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በአንድ ሳምንት ውስጥ ተከታታይ ጥቃቶች የተፈጸሙባቸው በአርሲ ዞን ውስጥ በሚገኙት ጉና፣ ሽርካ እና ሆንቆሎ ዋቤ ወረዳዎች ነው። ቢቢሲ ጥቃቶቹን በተመለከተ ያነጋገራቸው ሁለት የተጎጂዎች ቤተሰብ አባላት እና ሦስት የቤተክርስቲያን ኃላፊዎች በደኅንነት ስጋት ምክንያት ስማቸው እንዳይጠቀስ ጠይቀዋል።

ምንጮቹ እንደሚገልጹት በዞኑ በሚገኙት ጉና፣ ሽርካ እና ሆንቆሎ ዋቤ ወረዳዎች ተከታታይ ግድያዎች የተፈጸመው ካለፈው ሳምንት ረቡዕ ዕለት ጥቅምት 12/2018 ዓ.ም. አንስቶ ነው።

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የተገደሉት ሰሞነኛው ጥቃት በጀመረበት ጉና ወረዳ ነው። ታጣቂዎች ባለፈው ሳምንት ረቡዕ እና ሐሙስ በፈጸሟቸው ጥቃቶች 14 ሰዎች መገደላቸውን ሁለት የተጎጂዎች ቤተሰብ አባላት እና የአካባቢው የቤተክርስቲያን አመራር ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሌላ ከፍተኛ የቤተ ክርስቲያን አመራር ደግሞ "አባ ጀማ" በተባለው አካባቢ ከተፈጸመው ጥቃት ጋር በድምሩ "17 ሰዎች" መገደላቸውን ገልጸዋል።

አርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ ተከታይ ጥቃት የተፈጸመው በዚህ ሳምንት ሰኞ ጥቅምት 17/2018 ዓ.ም. ሌሊት እንደሆነ አንድ የቤተ ክርስቲያን አመራር ገልጸዋል። በዚህ ጥቃት "ሦስት ሰዎች" መገደላቸውንም አስረድተዋል።

በማግሥቱ ማክሰኞ ሌሊት አምስት ሰዓት ገደማ ላይ ደግሞ ሌላኛው የአርሲ ዞን ወረዳ በሆነው ሆንቆሎ አቤ ሦስተኛ ጥቃት መፈጸሙን ሁለት ምንጮች ተናግረዋል።

በዚህ ጥቃት "አምስት ሰዎች" መገደላቸውን የሚገልጹት አንድ ወረዳው ቤተ ክርስቲያን ኃላፊ፤ ሟቾቹ "የአንድ ቤተሰብ አባላት" መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

"የአንድ ቤተሰብ አባላት ሁለቱ ሴቶች ህጻናት ልጆች እና ሦስቱ ወንዶች ናቸው ከቤት አውጥተው የገደሏቸው" የሚሉት ኃላፊው፤ "ከአንድ ቤት ተወስደው እንደተገደሉ" ተናግረዋል።

አንድ ሰው ደግሞ ታግቶ እንደተወሰደ እና እስካሁን ድረስ ያለበት እንደማይታወቅ ጠቅሰዋል።

ከአንድ ቤተሰብ ስምንት ሰዎች የተገደሉበት ጥቃት

የመጀመሪያው ጥቃት በተፈጸመበት ጉና ወረዳ የተገደሉት 14 ሰዎች፤ በአንድ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ እና በጋብቻ የተሳሰሩ የተለያዩ ቤተሰብ አባላት እንደሆኑ አራት ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የተጎጂዎች ቤተሰብ አባላት እና የቤተ ክርስቲያን አመራሮች በዚህ ጥቃት ተገድለዋል ያሏቸውን 14 ሰዎች ስም ዝርዝር አጋርተዋል። ቢቢሲ ካነጋገራቸው ምንጮች ያገኘው ስም ዝርዝርም ተመሳሳይነት ያለው ነው።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለት የቤተሰብ አባላት፤ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው ከጥቃቱ የተረፉ የአራት እና የስምንት ዓመት ሕጻናትን እያሳከሙ ያሉ ናቸው።

አንዱ ምንጭ እህቱ እንደተገደለች ተናግሯል። ሌላኛው ደግሞ እናቱ፣ ዘጠኝ ዓመት የሆናቸው ሁለት መንታ ወንድሞቹ እና አንድ እህቱን ጨምሮ ስምንት የቤተሰቡ አባላት እንደተገደሉ አስረድቷል።

የወንድሙ ባለቤት እና የ16 ዓመት ሴት ልጅም መገደላቸውን ጠቅሷል። የአጎቱ ባለቤት እና በቤታቸው ውስጥ ይኖር ነበረ የ12 ዓመት ልጅም ከሟቾቹ መካከል እንደሆኑ ዘርዝሯል።

ምንጮቹ እንደሚናገሩት፤ ረቡዕ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ የመጀመሪያው ጥቃት የደረሰው "የሚካኤል" ዕለትን ለማክበር በአንድ ቤት በተሰበሰቡ ስድስት ሰዎች ላይ ነው።

ከእነዚህ ስድስት ሰዎች ውስጥ እናቱ ፋኖሴ ወርቄ እና የአጎቱ ሚስት መስቲካ ማሞ እንደሚገኙበት ገልጿል። ሻውሌ ይፍሩ እና እታገኘው አስፋው የተባሉ ባል እና ሚስትም ከተወሰዱት መካከል መሆናቸውን አክሏል።

ስድስቱ ሰዎች "ወደ ጫካ ከተወሰዱ" በኋላ መገደላቸውን ተናግሯል።

በዚህ ጥቃት ፍርሃት የገባቸው ዘጠኝ የሟች ቤተሰብ አባላት አንድ ቤት ውስጥ ተሰብስበው እንደነበር ሁለቱ ምንጮች ገልጸዋል። ሐሙስ ሌሊት ወደዚህ ቤት የገቡት ታጣቂዎች ዘጠኙን ሰዎች እና አጠገብ ባለ ቤት የነበረ አንድ ግለሰብን ጨምረው መውሰዳቸውን አስረድተዋል።

ዘጠኙ ሰዎች እና በረት ውስጥ የነበሩ ከብቶችን እየነዱ ከወሰዱ በኋላ "ተረአሊ" የሚባል ቦታ ላይ "ሁሉንም አንበርክከው እርምጃ" እንደወሰዱባቸው አንድ ምንጭ ገልጿል። ከተወሰዱት አስር ሰዎች ውስጥ የስምንቱ ሕይወትታቸው፤ ሁለት ሕጻናት እንደተረፉ ሦስት ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በዚህ ጥቃት ከተገደሉት ውስጥ የዘጠኝ ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሚኪያስ ሙላቱ እና ሶፎኒያስ ሙላቱ እንዲሁም የ18 ዓመቷ እህቱ ሄለት ሙላቱ እንደሚገኙበት አስረድቷል። የወንድሙ ሚስት የሺ መለሰ እና የ16 ዓመት ልጇ ስምረት ሸዋንግዛው ሲገደሉ ሌላኛዋ የወንድሙ ልጅ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባት እንደተረፈች ገልጿል።

በዚህ ጥቃት ከተገደሉት ሰዎች አንዷ የሆነችው የሰርካም ተስፋዬ ልጅ የሆነ የአራት ዓመት ሕጻንም በተመሳሳይ ጉዳት ደርሶበት መትረፉን ጠቅሷል። የተረፉት ሕጻናት የተገኙት በማግስቱ ጠዋት አንድ ሰዓት "ከፖሊስ ጋር" ግድያው ወደተፈጸመበት አካባቢ በሄዱ ነዋሪዎች እንደሆነም አክሏል።

ሁለቱ ሕጻናት፤ በቀድሞ ስሙ "ኃይለማርያም ማሞ ሆስፒታል" ተብሎ በሚጠራው አዳማ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ መወሰዳቸውን ሁለቱ ምንጮች ገልጸዋል።

የቤተሰብ አባላቱ በሁለቱ ሕጻናት ላይ የደረሰውን ጉዳት ሚያሳዩ ምሥሎችን ለቢቢሲ አጋርተዋል። ምሥሎቹ የስምንት ዓመቷ ሕጻና ጭንቅላቷ እና እጇ ላይ የደረሰባትን ጉዳት ያሳያሉ።

የአራት ዓመቱ ሕጻን ደግሞ የእጁ መገጣጠሚያ እና እግሩ ላይ ጉዳት እንደደረሰበት የቤተሰብ አባላቱ ተናግረዋል። ሕጻኑ በተለይ በእግሩ አጥንት ላይ የደረሰበት ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ የአጥንት ህክምና ወደሚሰጥበት የወላይታው የሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል መወሰዱን ገልጸዋል።

ስምንት የቤተሰቡ አባላት የተገደሉበት ግለሰብ፤ ወደ አካባቢው ተጉዞ እናቱን፣ እህቱን እና ወንድሞቹን መቅበር አለመቻሉን ይናገራል።

"'እንዳትመጡ የምትጠበቁት እናንተ ናችሁ' አሉን። ለነፍሳችን ፈራን። ኃላፊነት የሚወስድ ሰው ስለሌለ ሄደን እንኳ መቅበር አልቻልንም" የሚለው ስድስቱ የቤተሰቡ አባላት አንድ ቦታ ላይ መቀበራቸውን ገልጿል። እናቱ እና የአጎቱ ሚስት በተለያዩ አብተ ክርስቲያናት መቀበራቸውን አስረድቷል።

አባቱ ከስድስት ወር በፊት ሕይወታቸው ያለፈው በተመሳሳይ መልኩ በታጣቂዎች ከተወሰዱ በኋላ እንደነበር ያስታውሳል።

አባቱን ጨምሮ በወቅቱ የታገቱ ስምንት ሰዎችን ለማስለቀቀ ለእያንዳንዳቸው 500 ሺህ ብር መከፈሉን የሚናገረው ምንጩ፤ አባቱ ከተለቀቁ በኋላ በደረሰባቸው ድብደባ ምክንያት ከሦስት ቀን በኋላ ሕይወታቸው ማለፉን ጠቅሷል።

"ተስፋ የሚባል ነገር በውስጤ የለም። ከዚህ በኋላ ምናልባት ሕግ እንደዚህ አድርጎልን የሚለው ነገር ላይ ምንም አይነት ተስፋ በውስጤ የለም። ከዚህ በኋላ እዚያ ቦታ ላይ ተመልሰን እናገግማለን የሚለው ነገር የሚሆን አይመስለኝም" ሲል ተስፋ መቁረጡን ገልጿል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የተጎጂ ቤተሰብ አባላት እና የቤተ ክርስቲያን ኃላፊዎች ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች "በሃይማኖታቸው ምክንያት ዒላማ ተደርገዋል" የሚል እምነት አላቸው። በአካባቢው ተደጋጋሚ መሰል ጥቃቶች መፈጸማቸውንም ለዚህ በማሳያነት ይጠቅሳሉ።

ከመጀመሪያው ጥቃት በኋላ የጉና ወረዳ ኃላፊዎች ወደ ቦታው ተጉዘው በታጣቂዎች ላይ "የአጸፋ እርምጃ" ስለመውሰዳቸው ሪፖርት እንደደረሳቸው አንድ ከፍተኛ የቤተ ክርስቲያን ኃላፊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የሆንቆሎ ዋቤ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሐሰን መሐመድ ትናንት ረቡዕ በወረዳው ስለተፈጸመው ጥቃት ከቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ለቀረበላቸው ጥያቄ "አጣርተን በቂ መረጃ እንሰጣለን" ብለዋል።

በተመሳሳይ ቀን ስለ ጉዳዩ ጥያቄ የቀረበላቸው የአርሲ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኢብራሂም ከድር በበኩላቸው፤ "ሐሰት ነው" ሲሉ ተፈጽመዋል የተባሉትን ግድያዎች አስተባብለዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ረቡዕ ምሽት ባወጣችው መግለጫ በአርሲ ዞን በጥቅምት ወር ብቻ "ከ25 በላይ ሰዎች" መገደላቸውን አስታውቃለች።