ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በአርሲ 36 ምዕመኖቿ መገደላቸውን አጥብቃ አወገዘች
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በኦሮሚያ ክልል፣ አርሲ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች 36 ምዕመኖቿ መገደላቸውን አጥብቃ አወገዘች።
በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ላይ ያነጣጠረ ነው ባለችው ጥቃቶች በባለፈው ሳምንት ከተገደሉት በተጨማሪም በትናንትናው ዕለት በዲገሉ ማርያም ቤተ ክርስቲያን አምስት ምዕመኖቿ መገደላቸውንም ትናንት ባወጣችው መግለጫ አስፍራለች።
ከተገደሉት በተጨማሪም ሶስት የዕምነቱ ተከታዮች ደግሞ ቤታቸው ተቃጥሏል ብላለች።
ታጣቂዎች በሺርካ ወረዳ ትናንት ማለዳ 11፡ 00 ላይ በፈጸሙት ጥቃት አምስት ሰዎች መገደላቸውንም ቢቢሲ ከነዋሪዎች ሰምቷል።
ቤተ ክርስቲያኗ በአርሲ ዞን በሚገኙ ወረዳዎች በተለያዩ ጊዜያት ምዕመኖቿ ላይ በተደጋጋሚ ባነጣጠረው ጥቃትም 36 የእምነቱ ተከታዮች ተገድለዋል ብላለች።
ጥቃቱ የተፈጸመባቸው በሹርካ ወረዳ ሶሌ ሚካኤል፣ በዲገሎ ማርያም፣ በሮቤ እንደቶ ደብረ ምጥማቅ ማርያም አብያተ ክርስቲያናት መሆኑም ተገልጿል።
በባለፈው ሳምንት በሶሌ ዲገሉ እና ጢጆ ለቡ በተባሉ ቀበሌዎች 28 ምዕመናን ከየቤታቸው ተወስደው መገደላቸውን ያተተው መግለጫው ከእነዚህም ውስጥ ሰባቱ ሴቶች መሆናቸውንም ገልጿል።
በዚህ ጥቃት ዕድሜያቸው ከሰባ ዓመት አዛውንት እስከ ሃያ ስምንት ቀን ጨቅላ ህጻናትም ተገድለዋል ብሏል።
ከዚህ ቀደምም በምዕመኖቿ ባነጣጠረ ጥቃት በሮቤ አንዲቶ ደብረ ምጥማቅ ቤተክርስቲያን የማርያምን በዓል አክብረው ሲመለሱ ሶስት ምዕመናን መገደላቸው ተገልጿል።
ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው ከሳምንት በፊት ኅዳር 14 እና 17/2016 ዓ.ም. በአካባቢው ታጣቂዎች በሦስት መንደሮች ላይ በፈጸሙት ጥቃት ቢያንስ 36 ሰዎች መገደላቸውን ዘግቧል።ዒላማ የሆኑት “የኦሮቶዶክስ እምነት ተከታዮች በመሆናቸው” መሆኑን አንድ ነዋሪ ነግረውኛል ብሏል።
በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምዕመናን በተደጋጋሚ እና ሆን ተብሎ የሚፈጸሙ ጥቃቶች መሆኑንም ቤተ ክርስቲያኗ ገልጻለች።
“ይህ ዓይነት ሃይማኖት ጥቃት በምእመናን ላይ መድረሱ አግባብነት የሌለውና እምነትን በነጻነት የማራመድ መንግስታዊ መብትን የሚጥስ ነው” ብሏል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው እና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የቤተክርስቲያን ምንጭ በአካባቢው ከመስከረም ወር ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት በነዋሪዎች ላይ ግድያዎች መፈፀማቸው ገልጸው፣“እየሰበሰቡ ነው የሚረሽኗቸው። መሞታቸውን ብቻ ነው እኛ የምንሰማው” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እነዚህን ተደጋጋሚ ጥቃቶች በዝምታ ማለፉ ቤተ ክርስቲያኗ ከፍተኛ ቅሬታ እንዳሳደረባትም ነው የገለጸችው።
የሃይማኖት ጉባኤው ድርጊቱን በማውገዝ እንዲሁም ችግሩ ከመሰረቱ እንዲቀረፍ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር ተነጋግሮ መፍትሄ መፈለግ ይገባው ነበር ስትልም ወቅሳለች።
ጉባኤው እንዲህ ዓይነት በሃይማኖት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን ለመከላከል እና የሃይማኖት ተቋማት መብቶቻቸውን ለማስከበር ያቋቁሙት መሆኑንም በመግለጫዋ አስታውሳለች።
የአካባቢው ነዋሪዎች በከባድ ስጋት ውስጥ ሆነው ቀናት እየገፉ ሲሆን፣ ጥቃቱ የሚያስቆም አካል እንዳጡ አመልክተዋል። በተፈጠረው ስጋት ምክንያት አካባቢውን ለቀው የሸሹ ጥቂት እንዳልሆኑ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ቤተ ክርስቲያኗ በበኩሏ ምዕመናኑን በማጥቃት ላይ ተሰማርተው የሚገኙ አንዳንድ አካላት በመንግሥት በኩል የማያዳግም እርምጃ እንደተወሰደባቸው ኃገረ ስብከቱ በላከው ሪፖርት ማረጋገጧን ጠቅሳለች። መግለጫው ጥቃቱን ፈጽመዋል ያላቸውን አንዳንድ አካላት ያላቸውን ማንነት ያልጠቀሰ ሲሆን ስለተወሰደው እርምጃም ያለው ነገር የለም።
“ይህ ዐይነቱ ኦርቶዶክሳዊያን ላይ ያነጣጠረ ግድያ እንዲቆምና የወንጀሉ ፈጻሚዎችም ለፍርድ እንዲቀርቡ በሀገረ ስብከቱ በኩል ጥረት እየተደረገ መሆኑንም” አክሎ ገልጿል።
የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥታት የሚደርሱ ሃይማኖት ተኮር ጥቃቶች እንዲቆሙ እና መሰል ጥቃት እንዳይፈጸም ለኦርቶዶክሳዊያን ምዕመናን ከለላ እንዲሰጥም ቤተ ክርስቲያኗ ጥሪ አቅርባለች ።
የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ቅዳሜ ዕለት በሰጡት መግለጫ በአርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ በተፈጸመው ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን አረጋግጠዋል።
ባለሥልጣኑ ጥቃቱን የፈጸመው መንግሥት ሸኔ የሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እንደሆነ በመግለጽ ከሰዋል። ለዚህም ምክንያቱ መንግሥት በቡድኑ ላይ እየወሰደ ባለው እርምጃ እንደሆነ ገልጸው፣ “የተደናገጠው ሽብር ቡድኑ በሰላማዊ ዜጎች ላይ አሰቃቂ ርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል” ብለዋል።
አክለውም ታጣቂ ቡድኑ በአርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ ውስጥ በወሰደው “ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ ብዙ ዜጎችን ገድሏል። ቤት ንብረታቸውንም አቃጥሏል” በማለት ቡድኑ የመደራደር አቅሙን ከፍ ለማድረግ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ እርምጃ እየወሰደ ነው ሲሉ ከሰዋል።
የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በቀረበበት ክስ ላይ የሰጠው አስተያየት የለም።
መንግሥት በሽብር ቡድንነት የፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና የፌደራሉ መንግሥት ከሁለት ሳምንት በፊት ታንዛኒያ ውስጥ ሲያካሂዱት የነበረው ድርድር ያለውጤት መበተኑ ይታወቃል።