ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ባለፉት ሳምንታት በርካቶች በተገደሉበት አርሲ ተጨማሪ አምስት ሰዎች በታጣቂዎች ተገደሉ
በኦሮሚያ ክልል፣ አርሲ ዞን፣ ባለፉት ሳምንታት ታጣቂዎች በነዋሪዎች ላይ ተከታታይ ጥቃት በፈጸሙበት ሺርካ ወረዳ ውስጥ [ዛሬ] ሰኞ ማለዳ በፈጸሙት ሌላ ጥቃት አምስት ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገለጹ።
ጥቃቱ በተለይ በወረዳው ባሉ የተለያዩ ቀበሌዎች በሚገኙ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ላይ ያነጣጠረ ነው ያሉት ነዋሪዎቹ፣ በተለይ በዚህ ዓመት ግድያዎች መፈጸም ከጀመሩ ወራት መቆጠራቸውን ተናግረዋል።
ነዋሪዎች ከዛሬ ነገ አካባቢው ይረጋጋ ይሆናል እያሉ ቢጠብቁም ዛሬ፣ ኅዳር 24/2016 ዓ.ም. ማለዳ 11፡00 ሰዓት ላይ የአንድ አካባቢ ነዋሪ የሆኑ አምስት ሰዎች በታጣቂዎች ተገድለዋል ብለዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው እና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የቤተክርስቲያን ምንጭ በአካባቢው ከመስከረም ወር ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት በነዋሪዎች ላይ ግድያዎች መፈፀማቸው ገልጸው፣“እየሰበሰቡ ነው የሚረሽኗቸው። መሞታቸውን ብቻ ነው እኛ የምንሰማው” ብለዋል።
ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው ከሳምንት በፊት ኅዳር 14 እና 17/2016 ዓ.ም. በአካባቢው ታጣቂዎች በሦስት መንደሮች ላይ በፈጸሙት ጥቃት ቢያንስ 36 ሰዎች መገደላቸውን ዘግቧል።ዒላማ የሆኑት “የኦሮቶዶክስ እምነት ተከታዮች በመሆናቸው” መሆኑን አንድ ነዋሪ ነግረውኛል ብሏል።
የቢቢሲ ምንጭም “መስከረም 2/2016 ዓ.ም. ቅርጫ ቀበሌ ምእመን እና ካህን፣ ጥቅምት 10 ጋዶ የሚባል ቦታ አንድ ወጣት፣ ኅዳር 13/2016 ዓ.ም. ሌሊት በሁለት ቀበሌ 17 እና 11 ሰዎች፣ በሌላ ቀበሌ ደግሞ 8 ሰዎች፣ ዛሬ ደግሞ 5 ሰዎች ተገድለዋል” ሲሉም እስካሁን በአጠቃላይ ከ40 በላይ ሰዎች መጨፍጨፋቸውን በዝርዝር አስረድተዋል።
“የመከላከያ ኃይል እንዲሁም ሌሎች የአካባቢው የፀጥታ አካላት አሉ። ዛሬ ይህ ቦታ ይረጋጋል ስንል፣ ሌላ ቦታ ደግሞ ግድያ ይፈፀማል። በዚህ ሁሉ ምዕመናን ያለ ሃይ ባይ እያለቁ ነው” ብለዋል።
ታጣቂዎቹ ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ የተጠየቁት ግለሰቡ “ክርስቲያን የሆኑ እና ስማቸው የአማራ የሆኑ ናቸው እየተገደሉ ያሉት። ከዚህ አንጻር ቤተክርስቲያንን እና ክርስቲያንን ማጥፋት ይመስላል ዓላማቸው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
የቤተክርስቲያኗ ተጠሪዎች እና ምእመናኑ በተለያየ ጊዜ እየተፈጸሙባቸው ስላሉ ግድያዎች ለዞኑ አገረ ስብከት ማሳወቃቸውን እና ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ሪፖርት ማድረጋቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
“ዛሬ የተገደሉትን ሰዎች አስከሬን ወደ አካባቢው አስተዳደር ድረስ ወስደን፣ አቤቱታ አቅርበን፣ ከዚያ ወጥቶ ነው የተቀበሩት” ሲሉ አንድ ግለሰብ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ከአስተዳደር በኩልም “አስክሬኖቹ ይቀበሩና እንነጋገራለን። ጠላት ነገሮች እንዳይበርዱ ፈልጎ ነው” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው፤ ነገር ግን ጥቃቱን ያስቆመ አካል እንደሌለ ገልጸዋል።
በጥቃቱ የቤተሰብ አባላት የተገደሉባቸው በሽርካ ወረዳ፣ የጥዮ ለቡ ቀበሌ ነዋሪ፣ ኅዳር 13/2016 ዓ.ም. ግድያው ሲፈፀም በአጋጣሚ በስፍራው ባለመኖራቸው እርሳቸው ቢተርፉም፣ አብዛኞቹ የቤተሰቦቻቸው አባላት እንደተገደሉባቸው ተናግረዋል።
በጥቃቱ “ባለቤቴ እና ልጄ፣ የአባቴ ልጆች፣ የአባቴ ሚስት፣ እህቶቼ እና ወንድሞቼ በአጠቃላይ ሰባት ቤተሰብ ተገድሎብኛል። ከቤት ወስደው ነው የጨፈጨፏቸው” ብለዋል በመሪር ሐዘን።
ቢቢሲ ባነጋገራቸው ወቅትም ከጥቃቱ የተረፉ የሁለት ዓመት እና የስምንት ዓመት ልጆቻቸውን አሳክመው እየተመለሱ እንደሆነ ተስፋ በቆረጠ ሁኔታ ገልጸዋል።
በወረዳው ሾሌ ዲገሊቡና ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ ሌላ ግለሰብም ባለፈው ሳምንት በተፈጸመው ጥቃት የ8 ልጆቻው እናት የሆነችው ባለቤታቸው እና የ12 ዓመት ሴት ልጃቸው እንደተገደሉባቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ጥቃት አድራሾቹ ኅዳር 14/2016 ዓ.ም ከምሽቱ 3፡00 ላይ እኔ እና አንድ ግለሰብ ግቢ ገቡ። እኔ ጋ ባለቤቴን እና የ12 ዓመት ልጄን ገደሉ።ሌላ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ 11 ሰዎችን ገደሉ፣ ባል እና ሚስት ገደሉ። የ15 ሰዎች አስክሬን ረፍርፈው ነው የሄዱት።” ሲሉ ስለሆነው አስረድተዋል።
የጥቃቱ ምክንያት የተጠየቁት ነዋሪው፤ “ዘር ማጥፋት እና የሃይማኖት ጦርነት ነው። የጥቃቱ ዒላማ የሆኑት ክርስቲያኖች ናቸው” ሲሉ በምሬት ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም አንድ ካህን እና ሌሎች ግለሰቦች በእነርሱ አጎራባች ቀበሌ ውስጥ ከተገደሉ በኋላ ስጋት እንደነበራቸው ነዋሪው ገልጸዋል።
አሁን ላይ ቤት ንብረታቸውን ጥለው ከቀያቸው መፈናቀላቸውን የሚገልጹት ነዋሪው፣ ጥቃት አድራሾቹን ለይተው ማወቅ ባይችሉም፣ በቀበሌያቸው አጠቃላይ ስብሰባ በተካሄደበት ወቅት “የአንድ ብሔረሰብ አባላት” እንደሆኑ ሰምተናል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም በተፈፀመው ጥቃት ከተገደሉት መካከል የ25 ቀን ሕጻንን ጨምሮ ነፍሰ ጡር ሴቶች እና አራሶች እንደሚገኙበትም የቤተክርስቲያን ምንጫችን ጨምረው ገልጸዋል።
ባለፉት ቀናት ከተገደሉት መካከል 11 የአንድ ቤተሰብ አባላት፣ እንዲሁም ሌሎች 8 የአንድ ቤተሰብ አባላት ይገኙበታልም ብለዋል።
ምንጫችን እንዳሉት ዛሬ የተገደሉት አምስት ምዕመናንም አንድ ሰፈር የሚኖሩ እና የየአንድ ቤተሰብ አባል ያህል ቅርበት ያላቸው ናቸው።
የአካባቢው ነዋሪዎች በከባድ ስጋት ውስጥ ሆነው ቀናት እየገፉ ሲሆን፣ ጥቃቱ የሚያስቆም አካል እንዳጡ አመልክተዋል። በተፈጠረው ስጋት ምክንያት አካባቢውን ለቀው የሸሹ ጥቂት እንዳልሆኑ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
እስካሁን ድረስ በፀጥታ አካላት በኩል ይህ ነው የሚባል እርምጃ የለም፣ በቤተ ክህነት በኩልም ሐዘኑን በሚዲያ ከመግለጽ ባለፈ የተሰጠ መግለጫ የለም የሚሉት ነዋሪ “ነዋሪዎች ለደኅንነታቸው በመስጋት እየተፈናቀሉ ነው። የሸሹ ሰዎችም እንዳይመለሱም ቤታቸውን እያቃጠሉ እና ንብረታቸውን እያወደሙባቸው ነው” ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ቅዳሜ ዕለት በሰጡት መግለጫ በአርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ በተፈጸመው ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደቸውን አረጋግጠዋል።
ባለሥልጣኑ ጥቃቱን የፈጸመው መንግሥት ሸኔ የሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እንደሆነ በመግለጽ ከሰዋል። ለዚህም ምክንያቱ መንግሥት በቡድኑ ላይ እየወሰደ ባለው እርምጃ እንደሆነ ገልጸው፣ “የተደናገጠው ሽብር ቡድኑ በሰላማዊ ዜጎች ላይ አሰቃቂ ርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል” ብለዋል።
አክለውም ታጣቂ ቡድኑ በአርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ ውስጥ በወሰደው “ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ ብዙ ዜጎችን ገድሏል። ቤት ንብረታቸውንም አቃጥሏል” በማለት ቡድኑ የመደራደር አቅሙን ከፍ ለማድረግ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ እርምጃ እየወሰደ ነው ሲሉ ከሰዋል።
መንግሥት በሽብር ቡድንነት የፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና የፌደራሉ መንግሥት ከሁለት ሳምንት በፊት ታንዛኒያ ውስጥ ሲያካሂዱት የነበረው ድርድር ያለውጤት መበተኑ ይታወቃል።