በምዕራብ ኦሮሚያ ዘጠኝ ምዕመናን ከቤተ ክርስቲያን በታጣቂዎች ተወስደው መገደላቸው ተገለጸ

በምዕራብ ኦሮሚያ ቄለም ወለጋ ዞን ጊዳሚ ወረዳ ጊዳሚ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የመካነ ኢየሱስ ቤተ-ክርስቲያን ጸሎት ላይ የነበሩ ዘጠኝ ሰዎች በታጣቂዎች ተወስደው መገደላቸው ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ የወንጌል እና ቲዎሎጂ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ለሊሳ ዳንዴል ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ የአዳር ጸሎት ላይ የነበሩ የቤተ-ክርስቲያኗ አባላት በታጠቁ ኃይሎች ከተወሰዱ በኋላ ተገድለዋል ብለዋል።

በቤጊ-ጊዳሚ ሲኖዶስ በጊዳሚ ሰባካ ስር የምትገኘው የሃሞ ቶኩማ አጥቢያ ቤተ-ክርስቲያን አባላት የነበሩት ዘጠኙ ሰዎች የተገደሉት፣ ከሳምንት በፊት አርብ ኅዳር 14/2016 ዓ.ም. ሌሊት 8 ሰዓት አካባቢ ከቤተ ክርስቲያኗ ከተወሰዱ በኋላ ነው።

“የቤተክርስያኗ ሽማግሌዎች፣ የወጣቶች ኮሚቴ አባላት እንዲሁም ሌሎች አገልጋዮችን ጸሎት ላይ ሳሉ ሌሊት ስምንት ሰዓት ላይ በታጠቁ ሰዎች ተወስደዋል” ብለዋል ዶ/ር ለሊሳ።

ጸሎት ላይ የነበሩትን ምዕመናን ከቤተ ክርስቲያን አውጥቶ የገደለው ታጣቂ ቡድን ማን እንደሆነ ግልጽ አለመሆኑን የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን ገልጻለች።

“መገደላቸውን ነው ያረጋገጥነው። ይህን ግድያ ግን ማን እንደፈጸመ እስካሁን አላረጋገጥንም” ብለዋል ዶ/ር ለሊሳ።

የቤተ ክርስቲያኗ አባል የሆኑ እና የተገደሉትን ሰዎች በቅርበት አውቃለሁ የሚሉ አንድ ግለሰብ ዘጠኙ ሰዎች የተገለዱት ከሌሎች መካከል ተመርጠው ከተወሰዱ በኋላ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለደኅንነታቸው በመስጋት ስሜ አይጠቀስ ያሉት የቤተ ክርስቲያኗ አባል “ለቅዳሜ የአምልኮ ሥነ ሥርዓት ዝጅግት ጸሎት ላይ የነበሩት ሰዎች 12 ነበሩ። ሁለት ሴቶች እና አንድ በዕድሜ የገፉ አዛውንት እንዲቀሩ ተደርገው ሌሊት 8 ሰዓት ላይ ዘጠኙ ሰዎች ተመርጠው ተወስደዋል” ብለዋል።

እኚህ የቤተ ክርስቲያን አባል ዘጠኙን ሰዎች በመውሰድ የገደለው ማን እንደሆነ ባያውቁም፤ ሟቾቹ በሙሉ ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ተሳትፎ የሌላቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።

“የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እንጂ ምንም አይነት የፖለቲካ ተሳትፎ የላቸውም” ብለዋል።

ለሟቾቹ ቤተሰቦች መጽናናትን የተመኙት ዶ/ር ለሊሳ ኤሊያስ ጭካኔ በተሞላበት መልኩ ሕይወታቸውን ላጡ የቤተ ክርስቲያኗ አባላት ፍትሕ እንዲሰጥ መንግሥት ግድያውን እንዲመረምር ጠይቀዋል።

በምዕራብ ኦሮሚያ በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ባሉ ሰዎች ላይ ግድያ ሲፈጸም ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም።

ከአንድ ዓመት በፊት በምሥራቅ ወለጋ ዞን ታጣቂዎች በአምልኮ ላይ በነበሩ ሰዎች ላይ በፈጸሙት ጥቃት 15 ሰዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ አስታውቃ ነበር።

እሁድ ጥቅምት 27/2015 ዓ.ም. ለአምልኮ በተሰበሰቡት ምዕመናን ጥቃት የከፈቱት ከሌላ አካባቢ የመጡ ታጣቂዎች መሆናቸውን ቤተ ክርስቲያኗ አስታውቃ ነበር።

ባለፉት ዓመታት በምዕራብ ኢትዮጵያ በሚገኙ የኦሮሚያ አካባቢዎች ውስጥ በታጣቂዎች በሚፈጸሙ ጥቃቶች እና የመንግሥት ኃይሎች በሚወስዷቸው እርምጃዎች ሳቢያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸው ሲዘገብ ቆይቷል።

በተጨማሪም በርካቶች ለአካል ጉዳት ከመዳረጋቸው በተጨማሪ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ጥቃቶችን በመሸሽ ከቀያቸው ለመፈናቀል ተዳርገዋል።