ወርቅ ለማግኘት የከብት ጋጣ እየቆፈሩ ያሉት ደቡብ አፍሪካውያን

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ከቀናት በፊት የደቡብ አፍሪካዋ ስፕሪንግስ ከተማ ነዋሪዎች ወርቅ ማግኘታቸው ከተሰማ በኋላ በርካቶች በወርቅ ፍለጋ ተሰማርተዋል።

ከጆሀንስበርግ በቅርብ ርቀት የምትገኘው ከተማ ነዋሪዎች በስፋት ወደ ቁፋሮ ገብተዋል። ከዚህ ቀደም ከተማው የማዕድን ቁፋሮ የሚካሄድበት ነበር።

ኢ-መደበኛ በሆነ ሠፈራ በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች ድህነትን ለማሸነፍ ወርቅ መፈለግ ጀምረዋል።

ከቀናት በፊት የቀንድ ከብቶች ጋጣ ውስጥ ወርቅ መገኘቱ ሲነገር የበርካቶችን ትኩረት ስቧል። አሁን ደግሞ በጋጣው አቅራቢያ በርካታ ቁፋሮዎች ይታያሉ።

የአካባቢው ነዋሪዎች መዶሻ እና ወንፊት ይዘው መሬቱን ሲቆፍሩ ይውላሉ። ከአሥርት ዓመታት በፊት በደቡብ አፍሪካ ተመሳሳይ የወርቅ ፍለጋ ተካሂዶ ነበር።

ስፕሪንግስ ከተማ በአንድ ወቅት የወርቅ ቁፋሮ መዳረሻ ነበረች። ቁፋሮ የሚካሄድባቸው ጉድጓዶች ጥልቅ ከመሆናቸው የተነሳ ሥራውን በአነስተኛ ወጪ ማከናወን ስላልተቻለ ፕሮጀክቶቹ ተቋርጠዋል።

አብዛኞቹ የከተማው ነዋሪዎች ከአጎራባች አገራት የተሰደዱ ናቸው። የሚኖሩትም መደበኛ ባልሆነ ሠፈራ ነው።

የደቡብ አፍሪካ የማዕድን ኃብት ሚኒስቴር ሰሞነኛው የወርቅ ፍለጋ "ሕገ ወጥ" እንደሆነ ገልጿል። የወርቅ ቁፋሮው ከባቢ አየርን ስለሚጎዳ መቆም እንዳለበት አሳስቧል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ወርቅ ማግኘት እንደቻሉ ገልጸዋል። ያገኙትን ወርቅ በጥቁር ገበያ ላይ መሸጣቸውን የተናገሩም አሉ።

እንደ ሜርኩሪ እና ሶዲየም ያሉ ኬሚካሎች ወርቅን ከአፈር ለመለየት ይውላሉ። እነዚህ ኬሚካሎች ደግሞ እጅግ መርዛማ ናቸው።

ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ አንድ የአካባቢው ነዋሪ "ሕገ ወጥ እንደሆነ እናውቃለን። መንግሥት የማዕድን አውጪዎች ፈቃድ ይስጠን እና ሠርተን ግብር እንክፈል" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

የሁለት ልጆች አባት የሆነው ነዋሪው ልጆቹን ለመመገብ እና ለማስተማር የሚያስፈልገውን ገቢ ለማግኘት መጣጣሩን እንደሚቀጥል ይናገራል።

አንድ ሌላ ነዋሪ ደግሞ "የምናውቀው ሥራ ይሄ ብቻ ነው። አደገኛ ወንጀሎች ሠርተን ከመታሰር የዳንነው በዚህ ሥራ ነው" ብሏል።

አንድ ግራም ወርቅ 100 ዶላር ይሸጣል። በአንጻሩ በደቡብ አፍሪካ አነስተኛው ወርሀዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ 368 ዶላር ነው።

ቢቢሲ የቁፋሮ ሥፍራውን ሲጎበኝ ያገኛቸው ሰዎች ከሌሴቶ እንደሄዱ ተናግረዋል። ተማሪዎችም ከትምህርት ቤት ሲወጡ ቁፋሮውን ይቀላቀላሉ።

አብዛኞቹ ተማሪዎች የደንብ ልብሳቸውን ለውጠው ቤተሰቦቻቸውን በቁፋሮ ለማገዝ ይሞክራሉ።

ቁፋሮው በሚካሄድበት አካባቢ መሬቱ ሊንሸራተት ጫፍ ላይ መድረሱን ቢቢሲ ታዝቧል።

የደቡብ አፍሪካ የማዕድን ኃብት ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ "ቁጥጥር የማይደረግበት ቁፋሮ የመሬት መንሸራተት ያስከትላል። ሕጻናትን ጨምሮ የአካባቢው ነዋሪዎች ሕይወታቸውን ሊያጡ ወይም የአካል ጉዳት ሊደርስባቸው ይችላል" ብሏል።

በደቡብ አፍሪካ ሕገ ወጥ የማዕድን ቁፋሮ የተለመደ ሲሆን ባለፉት ዓመታት የበርካቶችን ሕይወት ቀጥፏል።

የአካባቢው ፖሊሶች የወንጀል ቡድኖችን ለማስቆም እና ሕገ ወጥ የማዕድን ቁፋሮን ለመግታት በሚያደርጉት ጥረት ከአገሪቱ ወታደሮች ድጋፍ እንደሚሰጣቸው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ አስታውቀዋል።

ሕገ ወጥ የማዕድን ቆፋሪዎች 'ዛማ ዛማ' በሚል ስም ይጠራሉ። አብዛኞቹ ከውጭ አገራት የገቡ እና ሰነድ አልባ ሲሆኑ መሣሪያም ይታጠቃሉ። በወንጀል ቡድኖች ውስጥ ባላቸው ተሳትፎም ይታወቃሉ።

ሆኖም ግን በስፕሪንግስ ከተማ እነዚህ ቡድኖች መሰማራቸውን የሚጠቁም መረጃ የለም።