በሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚሰሩ ፊልሞች ኦስካር ሊያሸንፉ እንደሚችሉ ተገለፀ

ኦስካር የያዘ እጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሰው ሰራሽ አስተውሎቶችን ተጠቅመው የሚሰሩ ፊልሞች የኦስካር ሽልማቶችን ሊያሸንፉ እንደሚችሉ አዘጋጆቹ ገለፁ።

የሽልማቱ አዘጋጅ የሆነው 'ዘ አካዳሚ ኦፍ ሞሽን ፒክቸር አርትስ ኤንድ ሳይንስ' ሰኞ ዕለት አዲስ ባወጣው መመርያ ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) እና ሎሎች ዲጂታል መገልገያዎችን መጠቀም " የኦስካር ምርጫ ውስጥ ለመግባት አይረዳም፤ አይጎዳም" ሲል ተናግሯል።

ባለፈው መጋቢት ወር የሰው ሠራሽ አስተውሎትን በመጠቀም የተሰሩ ፊልሞች ተሸላሚ ሆነው ነበር።

አካዳሚው አሸናፊዎችን በሚመርጥበት ወቅት የሰዎችን ተሳትፎ ከግምት ውስጥ እንደሚያስገባ ገልጿል።

አካዳሚው የሰው ሰራሽ አስተውሎትን በፊልሞች ላይ መጠቀም ተገቢነት ላይ ከሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ካውንስል ምክረ ሀሳብ መቅረቡን ተናግሯል።

ሰኞ ዕለት ይፋ በሆነው አዲስ መመርያ መሰረት የአካዳሚው አባላት በእያንዳንዱ ዘርፍ የተመረጡ ፊልሞችን ወደ መጨረሻው ዙር ድምጽ አሰጣጥ ለማሳላፍ እና አሸናፊውን ለመምረጥ ሙሉ በሙሉ መመልከት ይኖርባቸዋል።

ባለፈው መጋቢት ወር ላይ በ'ዘ ብሩታሊስት' ፊልም አድሪያን ብሮዲ በምርጥ ተዋናይነት ካሸነፈ በኋላ ከፍተኛ መነጋገርያ ሆኗል።

በፊልሙ ላይ ተዋንያኑ ሀንጋሪያንኛ ሲናገር የሚስተዋለውን ዘዬ ለማስተካከል የሰው ሰራሽ አስተውሎት ጥቅም ላይ ውሏል።

በተመሳሳይ ኤሚሊያ ፔሬዝ በተሰኘው ሙዚቃዊ ፊልም ላይ የድምጻዊያኑን አዘፋፈን ለማስተካከል ተመሳሳይ ድምፅን የሚለውጥ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ውሏል።

ቴክኖሎጂው የተዋንያኑን ድምጽ፣ አተዋወን፣ አዘፋፈን፣ የአነጋገር ቅላጼ አወጣጥን በፍጥነት ለማስተካከል እና ለመዋሃድ ያለው አመቺነት በሙዚቃ እና በፊልም ባለሙያዎች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኘ እንዲመጣ አድርጎታል።

የሰው ሰራሽ አስተውሎትን የመጠቀም ጉዳይ ግን አሁንም አወዛጋቢ ሆኖ ቀጥሏል።

በፊልም ሙያ ላይ የተሰማሩ የጥበብ ባለሙያዎች ለሰው ሰራሽ አስተውሎት የተለያዩ ነገሮችን እያስተማሩ መሄድ በሕይወታቸው እንዲሁም በሙያቸው ላይ የሚኖረውን ተጽዕኖ በመግለፅ ስጋታቸውን ይናገራሉ።

ተዋንያን እና የፊልም ደራሲዎች በሰው ሰራሽ አስተውሎት የተነሳ ስራቸውን ሊያጡ እንደሚችሉ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2023 በሆሊውድ በነበራቸው ተቃውሞ ላይ ገልጸዋል።

ተዋናይት ሱዛን ሳራንደን ለቢቢሲ "ፊቴን፣ ሰውነቴን እና ድምጼን ወስደህ ምንም ምርጫ የሌለኝን ነገር እንድል እና እንድስራ የምታደርገኝ ከሆነ ጥሩ ነገር አይደለም" ብላለች።

የፊልም ደራሲዎች በበኩላቸው ስቱዲዮዎች ወጪን ለመቀነስ በሚል ጥናት ለማድረግ፣ የፊልም ጽሑፍን ለማሻሻል እንዲሁም ለመጻፍ ከሰው ይልቅ እንደ ቻት ጂፒቲ ዓይነት የሰው ሰራሽ አስተውሎትን ሊጠቀሙ ይችላሉ ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።