የሸክላ ሙዚቃዎች ሽያጭ ከአስርት ዓመታት በኋላ ከሲዲዎች በለጠ

የሸክላ ሙዚቃዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአሜሪካ የሸክላ ሙዚቃዎች ከሶስት አስርት ዓመታት በኋላ ከሲዲዎች ሽያጭ መብለጡን አንድ ሪፖርት አመለከተ።

በባለፈው ዓመት ከ41 ሚሊዮን በላይ የሸክላ ሙዚቃዎች የተሸጡ ሲሆን በዚህም እስከ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ማግኘት ተችሏል።

በሌላ በኩል የተሸጡ ሲዲዎች 33 ሚሊዮን ሲሆን ገቢውም 483 ሚሊዮን ዶላር ነው።

በአሜሪካ በባለፉት ሰባት ዓመታት የታተሙ ሙዚቃዎች ሽያጭ እድገት ያሳየ ሲሆን ከፍተኛ የተባለው 15.9 ቢሊዮን ደርሷል።

በባለፈው ዓመትም የሙዚቃዎች ገቢ 6 በመቶ ጭማሬ ማሳየቱን የአሜሪካ ሬከርዲንግ ማህበር ሪፖርት ገልጿል።

ሪፖርቱ እንዳመለከተው በአውሮፓውያኑ 2020 ከተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ተገትቶ የነበረው ሽያጭ በቀጣዩ ዓመት በአስደናቂ ሁኔታ አንሰራርቷል።

በዚህም የሸክላ ሙዚቃዎች ሽያጭ 17 በመቶ ጭማሬ ሲያሳይ የሲዲዎች ገቢ 18 በመቶ አሽቆልቁሏል።

የታተሙ ሙዚቃዎች ቅጂዎች ከዲጂታል ሽያጭ የተሻለ ሁኔታ ላይ እንዳሉ ያሳየው ሪፖርቱ በዲጂታል ዳውንሎድ የሚደረጉ ሙዚቃዎች ገቢ 20 በመቶ አሽቆልቁሎ ያስገባው 495 ሚሊዮን ዶላር ነው።

በአውሮፓውያኑ 2012 ዲጂታል ሙዚቃዎች ከፍተኛ ሽያጭ ያስመዘገቡ ሲሆን በሙዚቃ ሽያጭም ረገድ 43 በመቶውን ይዘው ነበር። ነገር ግን ዲጂታል ሙዚቃዎች በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሳቸውን ተከትሎ ገቢው 3 በመቶውን ብቻ ይዟል።

ሆኖም በኢንተርኔት የሚከፈልባቸው፣ በማስታወቂያ የሚደገፉ አገልግሎቶች፣ ዲጂታል እና መደበኛ ሬድዮ፣ የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች፣ ዲጂታል የአካል ብቃት መተግበሪያዎች ያሉ ሙዚቃዎች 7 በመቶ ጭማሬ በማሳየት 13.3 ቢሊዮን ገቢ አስገኝተዋል።

የነዚህም ሙዚቃዎች ከአጠቃላይ ገቢው 84 በመቶ ድርሻ አላቸው።

በባለፈው ዓመት የታየው ከፍተኛ የሸክላ ሙዚቃ ሽያጭ በዘመናዊው ሙዚቃ እንዴት እየመሩ እንደሆነ የሚያሳይ ነው በማለት የማህበሩ ሊቀመንበር እና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሚች ግላዚየር ተናግረዋል።

ለዚህም የሙዚቃ አፍቃሪዎች በሸክላ ሙዚቃ ላይ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ድምጾች በማግኘታቸው እንደሆነም ተነግሯል።