ቲፋኒ ሃዲሽ በዚምባብዌ “ትልቅ የመገበያያ መደብር” አላቸው ብላ መደነቋ ነዋሪዎችን አስቆጣ

ኮሚዲያን ቲፋኒ ሃዲሽ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቲፋኒ ሃዲሽ በዚምባብዌ “ትልቅ የመገበያያ መደብር” አላቸው ብላ መደነቋ ነዋሪዎችን አስቆጣ

አሜሪካዊቷ ኮሜዲያን ቲፋኒ ሃዲሽ በዚምባብዌ መዲና ሐራሬ ትልቅ የመገበያያ መደብር አላቸው ብላ መደነቋ ነዋሪዎችን አስቆጣ።

ተዋናይቷ አፍሪካ ውስጥ “በየቀኑ ጦርነት” አለ የሚለውን አመለካከት ለማጥፋት ያለመ ነው ስትል የሐራሬን ትልቅ የመገበያያ መደብር ስትጎበኝ የሚያሳየውን አወዛጋቢ የቲክ ቶክ ቪዲዮን ተከላክላለች።

ቲፋኒ ይህንን ቪዲዮ ከለጠፈች በኋላ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ከአንዳንድ ዚምባብዌውያን ተቃውሞ ገጥሟታል።

"ይህን ግሮሰሪ ተመልከቱ። ትልቅ ነው አፍሪካ ውስጥ ነው" ስትል ባለማመን ለስላሳ መጠጦች፣ የቀዘቀዘ ስጋ እና ትኩስ ፍራፍሬ የያዙ መደርደሪያዎችን እየቃኘች ተናግራለች።

ቪዲዮው ቲኪቶክ ላይ ከ200 ሺህ ጊዜ በላይ ታይቷል።

"ምን ያህል አላዋቂ ብትሆን ነው? አፍሪካውያን ከድንጋይ የሚገዙ መስሏት ይሆን? የበለጠ አገራትን ጎብኝታ ስለዓለም ያላትን አሳዛኝ የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ መፋቅ አለባት።” ሲል አንድ ግለሰብ ኤክስ ላይ ጽፏል።

ሌላ ግለሰብ ደግሞ “አንበሶችን እና የሜዳ አህያዎችን እያሳደድን እንደምንኖር ያስባሉ” ብሏል።

ሦስተኛው ግለሰብ በበኩሉ አሜሪካውያን “ስለአፍሪካ የተሳሳተ ግንዛቤ አላቸው። አፍሪካዊያን ኋላቀር አኗኗር እንደሚኖሩ ያምናሉ። በጭቃ ጎጆዎች ውስጥ ከመኖራቸውም በላይ ንፁህ ውሃ፣ ኤሌክትሪክ እና እንደኢንተርኔት ያሉ ዘመናዊ አገልግሎቶች የሉም” ብለው ያስባሉ ብሏል።

ቲፋኒ ስለአፍሪካ የውሸት ትርክት ስሰማ ነው የኖርኩት በማለት ለቀረበባት ትችት ኤክስ ላይ ምላሽ ሰጥታለች።

"እኔ አሜሪካዊ ነኝ። ጥቁር ሰው ነኝ። አፍሪካ ውስጥ ሰዎች እየተራቡ እንደሆነ ለዓመታት ሲነገረኝ እና ዝንቦች የወረሯቸው ጨቅላ ሕፃናትን ፎቶ ሳይ ነበር።"

አፍሪካውያን “እንዴት እርስ በርስ እንደሚገዳደሉ” እና “በየቀኑ ጦርነት” እንደሚከሰት የሚገልጹ “አስጨናቂ ታሪኮች” እንደተነገራት አክላ ተናግራለች።

ሆኖም የዚምባብዌ ጉዞዋ አይኖቿን እንደከፈተላት እና "ስለ አህጉሪቱ" እውነቱን እያጣራች እንደሆነ ተናግራለች።

“አሜሪካ ውስጥ አፍሪካውያን ምንም ነገር እንደሌላቸው የሚያምኑ ሰዎችን ስለማውቅ ያየሁትን የማካፍል መስሎኝ ነበር” ስትል ጽፋለች።

አንዳንዶችም ኮሜዲያኗን ተከላክለዋል።

"የእኛን ግሮሰሪ ስለወደድሽው ደስ ብሎናል። አንቺን ያስደነገጡሽ ምርቶች ሁሉ እዚህም መሰረታዊ ነገሮች ናቸው። በእውነቱ እኛ በዛፎች ላይ እየተንጠለጠልን ጫካ ውስጥ የምንኖር አይደለንም" ሲል ተዋናይቷን ደግፈዋል።

ኮሜዲያኗ አባቷ ኤርትራዊ ሲሆን እአአ በ2018 ለመጀመሪያ ጊዜ ኤርትራን ጎብኝታለች።

በዚህ ጉብኝቷም ወቅት በተቃዋሚዎቻቸው “አምባገነን” ሲባሉ የሚገለጹትን አገሪቱን የረዥም ጊዜ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን አሞካሽታለች።