አዲሱ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ለምን አስፈለገ? ምን ውጤትስ ይኖረዋል?

ብር

የፎቶው ባለመብት, bbc/amensisa ifa

የኢትዮጵያ መንግሥት በገበያ ሥርዓት ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ተመንን ለመተግበር ውሳኔ አሳልፎ ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል።

ይህም ባለፉት 50 ዓመታት የአገሪቱ የምጣኔ ሀብት ታሪክ ውስጥ ጉልህ የሚባል የፋይናንስ ፖሊሲ ለውጥ ነው።

ውሳኔው ብርን በዓለም አቀፍ ገበያ ያለውን የመግዛት አቅም የሚያዳክም ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ከተላለፉ በርካታ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያዎችም አንዱ ነው።

ባለፉት ዓመታት ቴሌኮምን ጨምሮ ሌሎችም የፋይናንስ ዘርፎች ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዲሱ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ተመን ሥርዓት የውጭ አገር ኢንቨስትመንት እንደሚያሳድግ እና ገበያው የውጭ ምንዛሪ ተመንን እንዲወስን በማስቻል የምጣኔ ሀብት ዘርፉን እንደሚያረጋጋ ተስፋ ጥሏል።

ብሔራዊ ባንክ ይህ ለውጥ “ግብዓትን በተገቢው መንገድ ለማደላደል” እንዲሁም በውጭ ምንዛሪ “ግልጽነትን ለማስፈን” ጠቀሜታ እንዳለው አስታውቋል።

የተለወጠው ምንድን ነው?

በተደረገው ማሻሻያ መሠረት ከሰኞ ሐምሌ 22/2016 ዓ. ም. ጀምሮ በመላው አገሪቱ ያሉ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ የሚሸጡትም ሆነ የሚገዙት ከደንበኞቻቸው ጋር በሚደረግ ድርድር ይሆናል።

ከዚህ ቀደም የውጭ ምንዛሪ ግብይት ይከናወን የነበረው ብሔራዊ ባንክ በየቀኑ የሚያወጣውን ተመን በመከተል ነበር።

በአዲሱ አሠራር ብሔራዊ ባንክ የሁሉንም ባንኮች ዕለታዊ የውጭ ምንዛሪ ተመን በመሰብሰብ እንደ ዕለታዊ የውጭ ምንዛሪ ተመን ጠቋሚ (Indicative Daily Exchange Rate ወይም IDER) ይገልጻል።

ይህ የሚያገለግለው እንደ ማጣቀሻ እንጂ እንደ ውጭ ምንዛሬ ተመን ማውጫ አይሆንም።

ባንኮች ከዚህ በኋላ የውጭ ምንዛሪን ማከማቸት የሚችሉ ሲሆን፣ ይህም ለግል ዘርፉ የውጭ ምንዛሪ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚረዳ የብሔራዊ ባንክ መግለጫ ይጠቁማል።

ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር ከሳምንታዊ የውጭ ምንዛሪ ክምችታቸው 50 በመቶውን ለብሔራዊ ባንክ ማስገባት ይጠበቅባቸው ነበር።

ላኪዎች ከዚህ በኋላ ግማሽ ያህል የውጭ ምንዛሪ ገቢያቸውን ማከማቸት ይችላሉ።

በተጨማሪም፣ ከባንክ ውጪ ያሉ የውጭ ምንዛሪ አገልግሎት ሰጪዎች በአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ውስጥ እንዲሠሩ ተፈቅዶላቸዋል። ይህም በአሥርታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ግለሰቦችም ከውጭ በሚላክ ገንዘብ ወይም ከሌሎችም የገንዘብ ምንጮች የውጭ ምንዛሪ አካውንት መክፈት ይችላሉ።

ብር

ለውጡ ለምን አስፈለገ?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ለውጡን ባብራራበት መግለጫው ላይ እንዳለው፣ ከዚህ ቀደም የነበረው አሠራር “ጠንካራ መሠረት የሌለው” ትይዩ ገበያን የፈጠረ ሲሆን፣ ይህም ዶላር ከይፋዊ የግብይት ተመን እጥፍ በሆነ ዋጋ ለግብይት እንዲቀርብ መንገድ የከፈተ ነው።

ብሔራዊ ባንክ እንዳለው፣ በዚህ ምክንያት አገሪቱ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ስትፈተን ነበር። ይህም በዋነኛነት መሰናክል የሆነው ለግል ዘርፉ እንደሆነ ጠቅሶ “ጥቂት ሕገ ወጥ አካሎች እና ደላሎች የማይገባቸውን ጥቅም ሲያጋብሱ ነበር” ብሏል።

የውጭ ምንዛሪ እጥረት አገሪቱ ከገባችበት የማያቋርጥ ግጭት የተነሳ የውጭ ባለሃብቶችን መሳብ ባለመቻሏ የተከሰተ እንደሆነ ይገለጻል።

ያለፈው ታኅሣሥ ኢትዮጵያ በዓለም ገበያ ለሸጠችው የአንድ ቢሊዮን ዶላር ቦንድ መክፍል የሚጠበቅባትን የ33 ሚሊዮን ዶላር ወለድ ሳትከፍል ቀነ ገደቡ መጠናቀቁ ይታወሳል።

ባለፉት ጥቂት ወራት ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ አበዳሪዎች ጋር በመሆን ይህንን ዕዳ ስለምትከፍልበት መንገድ ምክክር ሲደረግ ነበር።

ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እና ከዓለም ባንክ ጋር አዲስ የ10.7 ቢሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት ላይ መድረስንም ያካትታል።

የገንዘብን የመግዛት አቅም ማዳከምን ጨምሮ ሌሎችም ትልልቅ የማክሮ ኢኮኖሚ ለውጦች አዲስ ብድር ለማግኘት እና ዕዳን ለማሸጋሸግ ቁልፍ መሆናቸውን ተንታኞች ይናገራሉ።

የብርን የመግዛት አቅም ማዳከም ኢትዮጵያ ካላት 120 ሚሊዮን ሕዝብ ጋር ሲደማመር አገሪቱን ለውጭ ኢንቨስትመንት ተመራጭ እንደሚያደርጋት የኢትዮጵያ መንግሥት ገልጿል።

ሆኖም ግን በዋናነት ኢንቨስትመንት የሚስበው የአገር መረጋጋት ነው።

በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ያሉት ግጭቶች ኢንቨስተሮች ከአገሪቱ ባለሥልጣናት የተሻለ የደኅንነት ማስተማመኛ እንዲያገኙ ማድረግ የግድ ይላል።

ለውጡ ምን ችግር ይኖረዋል?

አዲሱ የውጭ ምንዛሪ ግብይት አሠራር ሥርዓት ይፋ ከሆነ በኋላ ብር ከዶላር አንጻር ዋጋውን በአንድ ሦስተኛ አጥቷል።

ከዚህ ቀደም የብር የመግዛት አቅም ሲዳከም በተለይም ከውጭ በሚገቡ ሸቀጦች ላይ ከፍተኛ የዋጋ መናር ታይቷል።

ኢትዮጵያውያን አሁንም የዋጋ ንረት ይከሰታል የሚል ስጋት አላቸው።

ብሔራዊ ባንክ በበኩሉ የብርን የመግዛት አቅም መዳከም “እጅግ አስፈላጊ” ሲል ቢገልጸውም ሽግግሩ “ፈታኝ” ሊሆን አንደሚችል አምኗል።

ተግባራዊ በተደረገው የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ለውጥ በሚፈጥረው ጫና ምክንያት ተጋላጭ ለመሆኑት የመንግሥት ሠራተኞች ደሞዛቸውን “ለማሻሻል” ቃል የተገባ ሲሆን፣ ይህም የሚከናወነው “የበጀት እጥረትን በማያባብስ ሁኔታ” እንደሆነም ተገልጿል።

በምን መንገድ ይህንን ማሳካት እንደሚቻል ግን በዝርዝር የተገለጸ ነገር የለም።

ተንታኞች በበኩላቸው፣ ለውጡ በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ የዋጋ መናር አስከትሎ በከተማ ያሉ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ዋጋ ይከፍላሉ የሚል ስጋት አላቸው።