ቻይና በርካታ አገራት ከቻይና በሚነሱ መንገደኞች ላይ የጣሉት የኮቪድ ገደብ 'ፖለቲካዊ' ነው አለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቻይና መንግሥት በርካታ አገራት ከቻይና በሚነሱ መንገደኞች ላይ የጣሉት የጉዞ ገደብ “ፖለቲካዊ” ነው ሲል አፀፋ ሊመልስ እንደሚችል አስጠነቀቀ።
ከቻይና የሚነሱ መንገደኞች አስገዳጅ የኮቪድ-19 ምርመራ እንዲያደርጉ ውሳኔ ካሳለፉ አገራት መካከል አሜሪካ፣ ሕንድ እና ዩናይትድ ኪንግደም ይገኙበታል።
ቻይና ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ጥላው የነበረውን ጥብቅ የኮቪድ 19 ገደብ ካላላች በኋላ በቅርቡ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። የቻይና መንግሥት በቫይረሱ የተያዙ እና የሞቱ ሰዎች ቁጥር በትክክል አልተገለጸም የሚል ስጋት አለ።
ቻይና ለመጨረሻ ጊዜ ያደረገችውና ከ10 ቀናት በፊት ያወጣችው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር እለታዊ ሪፖርት ከ5 ሺህ ያነሰ ነበር። ይሁን አንጂ የዘርፉ ተንታኞች በአንድ ቀን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከ2 ሚሊዮን የበለጠ እንደሆነ እና በዚህ ወርም ቁጥሩ አሻቅቦ ከአራት ሚሊየን ሊበልጥ እንደሚችል ይናገራሉ።
ቻይና በጉዞ ላይ የጣለችውን እገዳ ከአራት ቀናት በኋላ እንደምታቀል ማስታወቋ በርካታ አገራት ከቻይና የሚነሱ መንገደኞች በመዳረሻቸው ላይ ምርመራ እንዲያደርጉ ገደብ እንዲጥሉ አድርጓቸዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ቻይና ተጨባጭ የሆነ ተጨማሪ መረጃን እንድታጋራ አሳስቧል። የአገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማክሰኞ ዕለት ቤጂንግ ከዓለም ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል ፈቃደኛ መሆኗን ገልጸዋል።
ሆኖም ቃል አቀባይዋ ማኦ ኒንግ መንግሥት ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያደርገውን ጥረት ለፖለቲካዊ ዓላማ ለማዋል የሚደረጉ ሙከራዎችን አጥብቆ ይቃወማል ብለዋል። በዚህም ቻይና ተመሳሳይ እርምጃ እንደምትወስድ ቃል አቀባይዋ አስጠንቅቀዋል።
አብዛኞቹ የቻይና ድንበሮች ከአውሮፓውያኑ ሚያዝያ 2020 ጀምሮ ተዘግተዋል። በዚህም ምክንያት ወደ አገሪቷ ዘልቀው መግባት የሚችሉት ጥቂት የውጭ ዜጎች ሲሆኑ እነርሱም ምርመራ ማድረግና ራሳቸውን ማግለል ይጠበቅባቸው ነበር።
የአውሮፓ ኅብረት የበሽታዎች መከላከያ ኤጄንሲ እና የአውስትራሊያ የጤና መኮንኖች ኃላፊ ክትባት እና የበሽታ መከላከያ ኮቪድ የሚያስከትለውን ስጋት እንደሚቀንስ አሳስበዋል።
ቢሆንም ግን የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራትን ጨምሮ ሌሎች አገራት ከቻይና የሚነሱ መንገደኞች ምርመራ እንዲያደርጉ ገደብ ጥለዋል።
የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤልዛቤጥ ቦርን ማክሰኞ ዕለት “ እንዲመረመሩ በማድረግ ዜጎቻችንን የመጠበቅ ግዴታችንን እየተወጣን ነው። የዓለም ጤና ድርጅት ሕግጋትን በማክበር እየሰራን ነው፤ ይህን ማድረጋችንንም እንቀጥላለን” ብለዋል።
የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን በበኩሉ በርካታ አባል አገራቱ የጉዞ ገደቦችን ማስተዋወቃቸውን እንደሚደግፍ ገልጿል።
የተወሰኑ አገራት የጣሉትን ገደብ ያስተዋወቁ ሲሆን በሁሉም አባል አገራት ገደቡ ይራዘም አይራዘም የሚለው ውሳኔም ዛሬ እንደሚታወቅ ይጠበቃል።
አሜሪካም ከቻይና የሚነሱ መንገደኞች እንዲመረመሩ ማድረጓ በሳይንስ ላይ የተመሠረተ ብቻ መሆኑን ገልጻለች።
ቻይና በቫይረሱ ምክንያት ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ ስትገባ ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም።
እንደ አውሮፓውያኑ 2019 መገባደጃ ላይ ቫይረሱ በቻይና ዉሃን የተገኘ ሲሆን የቻይና መንግሥት የቫይረሱን መነሻ ለመመርመር የተደረገውን ሙከራ ተቃውሟል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ማክሰኞ ዕለት ቻይና የአውሮፓ ኅብረት ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ያስችላታል ያለውንና ቁጥራቸው ያልተገለጸ የኮቪድ 19 ክትባት ለመስጠት ያቀረበውን ጥያቄ “በቂ አቅርቦት አለኝ” ስትል ውድቅ አድርጋለች።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ቻይና ከ3.4 ቢሊየን ዶዝ ክትባት የሰጠች ሲሆን አብዛኞቹም ቻይና ሰራሽ ኮሮናቫክ ናቸው።
መንግሥትም ሕዝቡ ከሌሎቹ በምዕራባውያኑ ከተሰሩ ክትባቶች አንጻር እምብዛም ውጤታማ አይደለም የሚባለውን በቻይና የተሰሩ ክትባቶችን ብቻ እንዲጠቀሙ እያሳሰበ ነው።












