ሩሲያ ዝነኛውን የፑቲን ተቃዋሚ አሌክሲ ናቫልኒ በእንቁራሪት መርዝ እንደገደለችው ተገለጸ

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

እስር ቤት ውስጥ ሞቶ የተገኘው የፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዋነኛ ተቃዋሚ አሌክሲ ናቫልኒ በእንቁራሪት መርዝ መገደሉን ዩናይትድ ኪንግደም እና የአውሮፓ አጋሮቿ አስታወቁ።

'ዳርት ፍሮግ' ከተባለ የእንቁራሪት ዝርያ በሚገኝ መርዝ አሌክሲ መገደሉ ይፋ የተደረገው ተቃዋሚው ከሞተ ከሁለት ዓመት በኋላ ነው።

በሳይቤሪያ እስር ቤት ሳለ መሞቱን ተከትሎ ዩኬ እና አጋሮቿ ክሬምሊንን ተጠያቂ አድርገዋል።

ከዝነኛው ተቃዋሚ አሌክሲ አስከሬን በተወሰደ ናሙና ላይ የተደረገው ምርመራ ተመርዞ መገደሉን ይጠቁማል ተብሏል።

በሙኒክ በተካሄደ የደኅንነት ኮንፈረንስ ላይ ንግግር ያደረጉት የዩኬ የውጭ ጉዳይ ጸሐፊ የቬት ኩፐር "ናቫልኒ በሩሲያ እስር ላይ ሳለ ለመግደል ዕድሉም ፍላጎቱም የነበረው የሩሲያ መንግሥት ብቻ ነው" ብለዋል።

በምርመራ የተገኘው የመርዝ ዓይነት (epibatidine) በአሌክሲ ሰውነት ውስጥ የኖረበት ሌላ ምክንያት ሊኖር እንደማይችል አብራርተዋል።

ታስ የተሰኘው የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገበው፤ ሞስኮ "የመረጃ ዘመቻ" በማለት የምዕራባውያኑን የምርመራ ውጤት ውድቅ አድርጋለች።

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ማሪያ ዛክሀሮቫ "ምዕራባውያን ካሉባቸው ችግሮች ትኩረት ለማስለወጥ የከፈቱት የመረጃ ዘመቻ" ነው ማለታቸውም ተዘግቧል።

ዩኬ፣ ስዊድን፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ኔዘርላንድስ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል። የአሌክሲ ባለቤት ዩሊያ ናቫልኒያም ኮንፈረንሱ ላይ ተገኝታለች።

"ሩሲያ ናቫልኒ ያሰጋት ነበር። የተጠቀሙት መርዝ ምን ያህል አስከፊ እርምጃ የመውሰድ አቅም እንዳላቸው እና ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን እንዴት እንደሚፈሩ ማሳያ ነው" ሲሉ የዩኬ የውጭ ጉዳይ ጸሐፊ ተናግረዋል።

ምዕራባውያኑ አገራት በጋራ ባወጡት መግለጫ "ያንን አደገኛ መርዝ ለመጠቀም ዕድሉም ፍላጎቱም ያለው የሩሲያ መንግሥት ነው" ብለዋል።

በደቡብ አሜሪካ በብዛት የሚገኘው የእንቁራሪት ዝርያ በመርዛማነቱ ይታወቃል።

መርዛማ ኬሚካል ላለመጠቀም የተቀመጠውን መርሕ ሩሲያ መጣሷን ዩኬ አስታውቃለች።

አሌክሲን "ጀግና" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር "እውነትን ለመናገር ባለው ቁርጠኛነት ሁሌም ይታወሳል" ሲሉ ተናግረዋል።

ጨምረውም "ሕዝባችንን እና መርሐችንን ከሩሲያ እና ከፑቲን የግድያ ዘመቻ ለመታደግ የቻልኩትን ሁሉ አደርጋለሁ" ብለዋል።

በሩሲያ ዋነኛ ተቃዋሚ የነበረው አሌክሲ በተለይም በፀረ ሙስና ንቅናቄ ይታወቃል። በአውሮፓውያኑ 2024 እስር ቤት ውስጥ ሞቶ ሲገኝ 47 ዓመቱ ነበር።

በ2020 በኖቪቾክ ተመርዞ በጀርመን ሕክምና ተደርጎለታል። ከጀርመን ወደ ሩሲያ እየተመለሰ ሳለም በቁጥጥር ሥር ውሏል።

በምርመራ ተገኝቷል የተባለው የእንቁራሪት መርዝ ለሕመም ማስታገሻነት ይውላል በሚል ምርመራ ቢደረግበትም የመርዛማነት መጠኑ ከፍተኛ መሆኑ ተደርሶበታል።

የቶክሲኮሎጂ ባለሙያ ጂል ጆንሰን ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ ኤፒባቲድን የሚባለው የእንቁራሪት መርዝ ከሞርፊን ጋር ሲነጻጸር 200 እጥፍ አደገኛ ነው።

መርዙ ማእከላዊ የነርቭ ሥርዓት ላይ ጉዳት የሚያደርስ ሲሆን የጡንቻ መሸማቀቅ፣ የሰውነት መንዘፍዘፍ፣ የልብ ምት መዝገም እና የመተንፈሻ ሥርዓት ከጥቅም ውጭ መሆን በማስከተል ይገድላል።

መርዙን ለማግኘት ቀላል እንዳልሆነ ባለሙያዋ አስረድተዋል። በዱር በሚኖሩት እንቁራሪቶች ዘንድ በጣም በተወሰነ መጠን ብቻ የሚገኝ ነው።

እንቁራሪቶቹ በጥብቅ አካባቢዎች ቢኖሩ መርዙን እንደማያመርቱ ተመራማሪዎች ደርሰውበታል። ስለዚህም የመርዙ ምንጭ በሚኖሩበት አካባቢ የሚያገኙት ምግብ ሊሆን እንደሚችል መላ ምት አስቀምጠዋል።

እነዚህን እንቁራሪቶች ይዞ፣ መርዛማነት ያላቸውን መለየት እጅግ ከባድ እንደሆነ ባለሙያዋ አስረድተዋል።

ዩኬ እና የአውሮፓ አጋሮቿ የምርመራ ውጤታቸውን ይፋ ከማድረጋቸው አስቀድሞ የአሌክሲ ባለቤት ዩሊያ እስር ቤት ውስጥ መገደሉን በተደጋጋሚ ስትናገር ቆይታለች።

ከዚህ ቀደም ከአሌክሲ አስከሬን የተወሰዱ ናሙናዎች መገደሉን እንደሚጠቁሙ ገልጻለች።

"ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ ባለቤቴ ተመርዞ እንደተገደለ እርግጠኛ ነበርኩ። አሁን ደግሞ ማስረጃ ተገኝቷል" ብላለች።

አሌክሲ ለሦስት ዓመት ከታሰረ በኋላ ነው እስር ቤት ውስጥ ሞቶ የተገኘው። የሩሲያ ማረሚያ ቤት አሌክሲ ሕመም ተሰምቶት እንደነበር እና እራሱን ከሳተ በኋላ እንዳልነቃ አስታውቋል።