የፑቲን ተቀናቃኝ ፖለቲከኛ አሌክሲ ናቫልኒ እስር ቤት ውስጥ መሞቱን ባለሥልጣናት ተናገሩ

የሩሲያው ተቃዋሚ ፖለቲከኛ አሌክሲ ናቫልኒ በእስር ላይ ሳለ ሕይወቱ ማለፉን የሩሲያ መንግሥት ባለሥልጣናት አስታወቁ።

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዋነኛ ተቺ የነበረው ፖለቲከኛ ናቫልኒ፣ እስር ቤት የገባው ከሁለት ዓመት በፊት በአውሮፓውያኑ 2021 ነው።

ባለፈው ታኅሣሥ ወር በጣም አስቸጋሪ ወደሚባለው እና ከዋና ከተማዋ ሞስኮ ሰሜን ምሥራቅ ሳይቤሪያ ውስጥ ወደ ሚገኘው ቀዝቃዛው የግዞት እስር ቤት ተዛዋውሮ ነበር።

ተቃዋሚ ፖለቲከኛ እና የቭላድሚር ፑቲን ቀንደኛ ተቺ የሆነው ናቫልኒ፣ በብዙዎች ፖለቲካዊ ነው ተብሎ በሚታመን ክስ የ19 ዓመት እስር ተፈርዶበት ነው እስር ቤት የገባው።

የነበረበት እስር ቤት ሞቱን ይፋ ባደረገበት ጊዜ ናቫልኒ ዛሬ አርብ ጠዋት የተወሰነ እንቅስቃሴ ካደረገ በኋላ “ህመም እንደተሰማው” እና ወዲያውኑ እራሱን እንደሳተ አመልክቷል።

እስር ቤቱ ባወጣው መግለጫ ይህንን ክስተት ተከትሎ በአስቸኳይ የህክምና እርዳታ ባለሙያዎች ተገኝተው ህክምና በመስጠት ሕይወቱን ለማትረፍ ሞክረው ሳይሳካ ቀርቷል ብሏል።

የናቫልኒ ጠበቃ ሊዮኔድ ሶሎቪዮቭ በጉዳዩ ላይ አስተያየት መስጠት እንደማይሹ ቢገልጹም፣ የቀርብ ረዳታቸው ሊዮኔድ ቮልኮቭ በኤክስ ገጻቸው ላይ “የሩሲያ ባለሥልጣናት ናቫልኒል እስር ቤት ውስጥ እንደገደሉት ያመኑበትን መግለጫ ይፋ አድርገዋል። ይህ ሁኔታ እውነት ይሁን አይሁን ምንም የምናረጋግጥበት መንገድ የለንም” ብለዋል።

የ47 ዓመቱ ናቫልኒ ሞትን በተመለከተ በሩሲያ አንድ ግዛት ውስጥ ጉብኝት ላይ ለሚገኙት ፕሬዝዳንት ፑቲን መነገሩን ቃል አቀባያቸው ዲሚትሪ ፔስኮቭ አረጋግጠዋል።

በሩሲያ ውስጥ ይካሄዳል የሚለውን መጠነ ሰፊ ሙስና በመቃወም ቅስቀሳ ሲያደርግ የነበረው አሌክሲ ናቫልኒ፣ እስር ቤት ከመግባቱ ከአንድ ዓመት በፊት ነርቭን በሚያጠቃ ንጥረ ነገር ተመርዞ ነበር።

አብዛኞቹ የፑቲን ተቺዎች እና ተቃዋሚዎች ከሩሲያ ሸሽተው በሌላ አገር የሚኖሩ ሲሆን፣ ናቫልኒ ግን የመመረዝ አደጋ ገጥሞት ለወራት በውጭ አገር በህክምና ላይ ቆይቶ ወደ አገሩ ተመልሷል።

ናቫልኒ ሩሲያ ውስጥ ከመተረዘ በኋላ ህክምና እንዲያገኝ በአውሮፕላን ወደ ጀርመን ተወስዶ ለወራት ታክሞ ወደ አገሩ እንደተመለሰ ወዲያውኑ ተይዞ እስር ቤት ገብቷል።

ናቫልኒ ለሩሲያ ፕሬዝዳንትነት በመቅረብ ፑቲንን ለመገዳደር ለረጅም ጊዜ ቢፈልግም በአውሮፓውያኑ 2018 በምርጫ እንዳይሳተፍ ተግዶ ነበር። በመጪው መጋቢት ወር በሚደረገው ሌላ ዙር ምርጫ ፑቲን ያለ ተፎካካሪ ለፕሬዝዳንትንት ይቀርባሉ።

የአሌክሲ ናቫልኒ ቃል አቀባይ የሆነችው ኪራ ያርምይሽ፣ ስለህልፈቱ አስካሁን ማረጋገጫ እንዳልተሰጣቸው በመግለጽ ምንም መረጃ እንዳላገኙ አመልክታለች።

“ናቫልኒ የነበረበት እስር ቤት ስለሞቱ መረጃ ዜና እያሰራጨ ነው። እኛ ግን መሞቱን የሚያረጋግጥ ምንም መረጃ የለንም” ስትል ቃል አቀባይዋ በኤክስ (ትዊተር) ላይ ገልጻለች።

አክላም የናቫልኒ ጠበቃ ወደ ሳይቤሪያ በአውሮፕላን በመጓዝ ላይ ሲሆን፣ እዚያ ደርሶ ስለሁኔታው መረጃ ሲያገኝ ይፋ እንደሚያደርግ አሳውቃለች።