በአሜሪካ ቴክሳስ የጎርፍ አደጋ 15 ሕፃናትን ጨምሮ የ51 ሰዎች ሕይወት አለፈ

በጎርፍ አደጋው የተጎዱ መኝታ ክፍሎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በጎርፍ አደጋው የ51 ሰዎች ሕይወት የጠፋ ቢሆንም የነፍስ አድን ሠራተኞች ፍለጋቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል

በማዕከላዊ ቴክሳስ በደራሽ ጎርፍ አደጋ 15 ሕፃናትን ጨምሮ 51 ሰዎች ከሞቱ በኋላ በመቶዎች የሚቆጠሩ የነፍስ አድን ሠራተኞች የጠፉ ሰዎችን ፍለጋ ተሰማሩ።

በጣም የተጎዳው ኪር የተባለው አካባቢ ሲሆን 43 ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ፤ በጓዳሉፔ ወንዝ አጠገብ በሚገኘው የክርስቲያን ወጣቶች ካምፕ የነበሩ 27 ሕፃናት ደግሞ ጠፍተዋል።

የአካባቢው የፖሊስ አዛዥ ላሪ ሊታ "ፍለጋው ይቀጥላል። ሁሉም ሰው እስኪገኝ ድረስ ሥራው ይቀጥላል" ሲል ቃል ገብቷል።

ትራቨስ እና ቶም ግሪን የተባሉ አካባቢዎችን ጨምሮ በሌሎች የግዛቱ ክፍሎች ሰዎች መሞታቸው ተረጋግጧል።

በማዕከላዊ ቴክሳስ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በርካታ የደራሽ ጎርፍ ማስጠንቀቂያዎች ወጥተዋል።

እስካሁን 850 የሚሆኑ ሰዎች በሕይወት መትረፍ ችለዋል።

የቴክሳስ ገዥ ግሬግ አቦት ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የፍለጋ ጥረቶችን ለማስፋፋት የአደጋ ጊዜ አዋጅ መፈራረማቸውን ተናግረዋል።

የአካባቢው ባለስልጣናት "በዚህ ክስተት ሰለባ የሆኑትን እያንዳንዱን ሰው ፈልገው እንዲያገኙ ለማድረግ ሌት ከቀን እንሰራለን" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የፍለጋ እና በሕይወት የማዳን ተልዕኮው እንደሚቀጥል የተናገሩት ባለስልጣናቱ፤ ይሁን እንጂ ጥረቱ በሕይወት የማዳን ጥረት አይደለም ብለዋል።

በጎርፉ ተጠርገው የተወሰዱ ሰዎችን ለማግኘት የነፍስ አድን ሠራተኞች ወደ ጓዳሉፔ ወንዝ እየወረዱ መሆኑንም ተናግረዋል።

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደራቸው ለአደጋው ምላሽ ለመስጠት ከአካባቢው ባለስልጣናት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የአየር ትንበያ ሠራተኞች ማዕከላዊ ቴክሳስ ተጨማሪ ጎርፍ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ማስጠንቀቂያ አውጥተዋል።

አብዛኛው የነፍስ አድን ስራ በጓዳሉፕ ወንዝ ዳርቻ በሚገኘው ሚስቲክ በተባለ የሴቶች የክርስቲያን የበጋ ካምፕ ላይ ያተኮረ ነው።

የቴክሳስ ምክትል ገዥ ዳን ፓትሪክ እንደተናገሩት ከ27ቱ የጠፉ ሴቶች መካከል አብዛኞቹ ከ12 ዓመት በታች ናቸው።

ከካምፑ የወጡ ምስሎች ብርድ ልብሶች፣ ፍራሾች፣ አሻንጉሊቶች እና ሌሎች እቃዎች በጭቃ ተውጠው ያሳያሉ።

ወንዙ ከአንድ ሰአት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ከስምንት ሜትር በላይ ከፍታ ሲጨምር አብዛኞቹ ተኝተው ነበር።

750 የሚሆኑ ሰዎችን የያዘው ሚስቲክ ካምፕ ለወላጆች በላከው ኢሜል በቀጥታ ስልክ ካልተደወለላቸው ልጆቻቸው አልተጎዱም ማለት እንደሆነ ተናግሯል።

ሕይወታቸው ስላለፉ ሰዎች ተጨማሪ ዝርዝሮች የወጡ ሲሆን፤ አንዳንዶቹ ገና የስምንት ዓመት እድሜ ያላቸው ናቸው።

በኖትር ዳም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እሁድ ዕለት ሕይወታቸው ላለፉ ሰዎች፣ ለጠፉት እና ለቤተሰቦቻቸው ልዩ የፀሎት መርሐ ግብር ካሂዷል።

በአደጋው የአሜሪካን የነጻነት ቀን ለማክበር የወጡ በርካታ ሰዎች የደረሱበት አልታወቀም።

ቤቷ እና ምግብ ቤቷ የወደመባት ሎሬና ጊሊየን በወንዙ አቅራቢያ ባለው መሬቷ ላይ በ28 ተሽከርካሪዎች የመጡ ሰዎች አርፈው ነበር ብላለች።

"ተጠርገው እየተወሰዱ ነበር። ራሳቸውን ለማዳን በዛፎች ላይ ተጣብቀው ነበር። ነገር ግን የአደጋ ሠራተኞች ሊደርሱላቸው አልቻሉም" ስትል እማኝነቷን ሰጥታለች።