በትግራይ ሙሽሪት ሰርጓ በተፈጸመ በአራተኛው ቀን በባለቤቷ መገደሏን ፖሊስ አስታወቀ

ሊዲያ ዓለም

የፎቶው ባለመብት, Social Media

የምስሉ መግለጫ, ሊዲያ ዓለም

በትግራይ ክልል ውቅሮ ከተማ ሊዲያ ዓለም የተባለች ግለሰብ ሰርጓ በተፈጸመ በአራተኛው ቀን በትዳር አጋሯ እንደተገደለች ፖሊስ አስታወቀ።

ሊዲያ ረቡዕ፣ጥቅምት 6/2017 ዓ.ም. ከሌሊቱ አስር ሰዓት ላይ መገደሏን የትግራይ ምሥራቃዊ ዞን ፖሊስ ኮማንደር ሙሉ ብርሃን ካህሳይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ተጠርጣሪው ባለቤቷ ግድያው ከተፈጸመ በኋላ ለፖሊስ እጁን እንደሰጠ እና በሕግ ቁጥጥር ስር እንደሚገኝ ኮማንደሩ አክለዋል።

የሊዲያ አጎት ነኝ ያሉት አቶ ግርማይ ፍሮዝ የእህታቸው ልጅ "አሰቃቂ ግድያ" የተፈጸመው ሐሙስ ጥዋት ላይ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ተጠርጣሪው ብርሃነ ገብረጨርቆስ የተባለው ግለሰብ የአራት ቀናት ባለቤቱን አንቆ እንደገደላት የውቅሮ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ገብረ መድኅን ገብረጊዮርጊስ መናገራቸውን ድምጺ ወያነ ዘግቧል።

ግለሰቡ እጁን ለፖሊስ ከሰጠ በኋላ ራሱን ለማጥፋት የተለያዩ ሙከራዎች አድርጎ እንደበረ የገለጹት ኮማንደር ገብረ መድኅን ፖሊስ አስፈላጊውን ጥበቃ እና ክትትል እያደረገለት መሆኑን አክለው ተናግረዋል።

የውቅሮ ተወላጅ እና በአዲስ አበባ በንግድ ይተዳደር የነበረው ተጠርጣሪው ሙሽራ በውቅሮ ባረፈበት ሆቴል ውስጥ ንብረቱ እንደተገኘ ኮማንደሩ ገልጸዋል።

ተጠርጣሪው እና የተገደለችው ሊዲያ ባለፈው ሳምንት እሁድ ጥቅምት 3/2017 ዓ.ም. በደማቅ የሰርግ ሥነ ሥርዓት ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት የጋብቻ ሥነ ሥርዓታቸውን መፈጸማቸው ተነግሯል።

አቶ ግርማይ ፍሮዝ ሟችን እንደ ልጃቸው እንዳሳደጓት ገልጸው፣ ዓመፀኛ እንዳልነበረች እና ሰላማዊ ህይወት መኖር ትፈልግ እንደነበር አክለዋል።

“ሊዲያ ግሩም ጸባይ ነበራት። በልጅነቷ እንኳን ሰዎችን እንደ ህጻናት አትሰድብም ... ወራዳ ቃላትን አትናገርም፤ በስነ ምግባር የታነጸች ልጅ ነች።"

ለእናቷ ብቸኛ ልጅ እንደነበረች የሚናገሩት አጎቷ፣ የእናቷን ' አግብተሽ ውለጂ' የሚለውን ቃል ለመፈጸም ትጓጓ እንደነበረ ያስታውሳሉ።

ለሁለት ዓመታት ከቆየችበት ደም አፋሳሽ ጦርነት ተጽእኖ ውስጥ ለመውጣት እየተጣረች ባለችው ትግራይ ውስጥ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እና ግድያዎች በተደጋጋሚ እየተሰሙ ነው።

ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ እና የተመረጡ ተማሪዎች በሚማሩበት በመቀለው አዳሪ ትምህርት ቤት ቃላሚኖ ተማሪ የነበረችው ቤተልሔም ገብረሚካኤል ለ10 ቀናት ደብዛዋ ከጠፋ በኋላ ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ አስከሬኗ መገኘቱ ይታወሳል።

ከቤቴልሔም በተጨማሪም ባለፈው ኣመት በትግራይ ክልል ጥቂት የማይባሉ ሴቶች እንግልት እና ሞት አጋጥሟቸዋል።

ከእነዚህም መካከል የመቀለ ከተማ ነዋሪዋ ዘውዱ ሐፍቱ በአሰቃቂ ሁኔታ ከተገደለች ዓመት ያለፋት ቢሆንም ፖሊስ አራት ተጠርጣሪዎችን እየመረመረ ከመሆኑ ውጪ ቤተሰቧ ፍትህ አላገኘም።

የአዲግራት ከተማ ነዋሪዋ አዳነሽ አብርሃም እንዲሁ እንቆቅልሽ በሆነ ሁኔታ ተገድላ አስከሬኗ ከ10 ወራት በኋላ ነበር የተገኘው።

በአድዋ ከተማ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ እና የ16 ዓመቷ ታዳጊ ማኅሌት ተኽላይም እንዲሁ ለትምህርት ወጥታ ታግታ ሦስት ሚሊዮን ብር የተጠየቀባት ሲሆን፣ ከሦስት ወራት በኋላ መገደሏ ታውቋል።

እነዚህ እንደማሳያ የቀረቡ ጥቃቶች ሲሆኑ፣ በትግራይ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ አሰቃቂ ጥቃቶች እና ግድያዎች ብቻ ሳይሆኑ መደፈሮችም ተበራክተው ቀጥለዋል።

በክልሉ በሴቶች ላይ እየተፈጸመ ያሉ ግድያዎች፣ እገታዎች እና ፆታዊ ጥቃቶች እንዲቆሙ በትግራይ ያሉ የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት አደባባይ ወጥተው ጠይቀዋል። ጊዜያዊ አስተዳደሩም ጥቃት ፈጻሚዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ እንዲያደርግ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።