ጋቦን ወደ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እንደምትሻገር የጦሩ መሪ ገለጹ

ጄነራል ብሪስ ኦሊጉይ ንጉሜያ

የፎቶው ባለመብት, REUTERS

የጋቦን አዲሱ ወታደራዊ መሪ አገሪቱን ወደ ዴሞክራሲ ለመመለስ ቃል ገቡ።

አዲስ ምርጫ መቼ እንደሚካሄድ ግን አልገለጹም።

ጄነራል ብሪስ ኦሊጉይ ንጉሜያ እንዳሉት የመንግሥት ተቋማት የተሻለ ዴሞክራሲያዊ እንዲሆኑ ይደረጋል። በተቋማቱ ላይ የተጣለው ዕገዳም ጊዜያዊ እንደሆነ ገልጸዋል።

ሆኖም የጋቦን ተቃዋሚዎች ወታደራዊ ኃይሉ ሥልጣኑን ወደ ሲቪል አስተዳደር የማሸጋገር ፍላጎት አለማሳየቱን ተችተዋል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት አሊ ቦንጉ አሁንም የቁም እስር ላይ ናቸው።

ጦሩ ሥልጣን መያዙን የገለጸው ያሳለፍነው ረቡዕ ሲሆን፣ የቦንጎ ቤተሰብ የ55 ዓመታት አስተዳደር አክትሞለታል።

አሊ ቦንጎ ያለፈው ሳምንት ቅዳሜ ምርጫ ማሸነፋቸውን ቢገልጹም፣ ጦሩ ውጤቱን ሽሮታል። የአገሪቱ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችም በውጤቱ ደስተኛ አልነበሩም።

ጄነራሉ በብሔራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያ “የቀደሙት ሰዎች ሥልጣን ላይ እንዲቀጥሉ አድርገን የቀደመውን ስህተት አንደግምም” ብለዋል።

“በፍጥነት እርምጃዎች እንወስዳለን። ይህ ማለት ግን የተመሰቃቀለ ምርጫ እናካሂዳለን ማለት አይደለም” ሲሉም አቋማቸውን ገልጸዋል።

ዋነኛው ተቃዋሚ አሊያንስ 2023 ምርጫውን እንዳሸነፈ ገልጾ፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋቦን ወደ ሲቪል አስተዳደር እንድትመለስ ጫና እንዲያደርግ ጠይቋል።

“አሊ ቦንጎ ስለወረደ ደስ ብሎናል። ግን ወደ ሲቪል አስተዳደር መመለስ አለብን። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጦሩ ሥልጣን እንዲያስረክብ ጫና ማድረግ አለበት” ሲሉ ቃል አቀባዩዋ አሌክሳንድርያ ፓንጋ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ጀነራሉ እንደ ሽግግር መሪ የፊታችን ሰኞ ቃለ መሀላ ይፈጽማሉ መባሉ ተቀባይነት የሌለው እንደሆነም አክለዋል።

ከ2020 ወዲህ በማእከላዊ አፍሪካ በኒጀር፣ ማሊ፣ ጋያና፣ ቡርኪና ፋሶ እና ቻድ መፈንቅለ መንግሥት ተደርጓል።

የአፍሪካ ኅብረት እና የአውሮፓ ኅብረት አውግዘውታል።

ከ2009 ጀምሮ ሥልጣን ላይ የነበሩት አሊ ቦንጎ በቁም እስር ሳሉ “ወዳጆቼ ድምጻችሁን አሰሙ” ብለዋል።

ሆኖም ግን ከሥልጣን በመወገዳቸው የአገሪቱ ዜጎች ደስታቸውን ሲገልጹ ተስተውሏል።