ኬንያውያን ያለ ቪዛ ወደ ደቡብ አፍሪካ መጓዝ እንዲችሉ የአገራቱ መሪዎች ተስማሙ

የፎቶው ባለመብት, State House Kenya
የኬንያ ዜጎች ያለ ቪዛ ወደ ደቡብ አፍሪካ መጓዝ እንዲችሉ የሁለቱ አገራት ፕሬዝዳንቶች ከስምምነት ላይ ደረሱ።
ከሁለት ወራት ገደማ በኋላ በፈረንጆቹ 2023 መጀመሪያ ላይ ተፈጻሚ በሚሆነው ሕግ መሠረት ኬንያውያን ቪዛ ሳያስፈልጋቸው ለ90 ቀናት ወደ ደቡብ አፍሪካ ማቅናት ይችላሉ።
ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ናይሮቢ የሚገኙት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ከኬንያው አቻቸው ዊሊያም ሩቶ ጋር ከተወያዩ በኋላ ከዜጎቻቸው የጉዞ ፍቃድ በተጨማሪ በምጣሄ ሃብታዊ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ደርሰዋል።
ከዚህ ቀደም ኬንያውያን በደቡብ አፍሪካ 90 ቀናት መቆየት የሚያስችላቸውን ቪዛ ለማግኘት 40 ዶላር ከፍለው ማመልከት ይጠበቅባቸው ነበር።
ኬንያውያኑ በደቡብ አፍሪካ በሚኖራቸው ቆይታም ወጪያቸውን መሸፈን የሚያስችል ገንዘብ እንዳላቸው ማስረጃ እንዲያቀርቡም ይጠየቁ ነበር።
በአንጻሩ የደቡብ አፍሪካ ፓስፖርት የያዙ ተጓዦች ኬንያ ሲደርሱ በነጻ ቪዛ ይሰጣቸዋል።
ስምምነቱ ይፋ በተደረገበት ጊዜ የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ “ሲጠበቅ የነበረው የደቡብ አፍሪካ እና ኬንያ ከቪዛ ነጻ ጉዞ ስምምነት እውነት ለማድረግ ለደረስንበት ደረጃ አድናቆቴን ልገልጽ እፈልጋለሁ” ብለዋል።
የሁለቱ አገራት መሪዎች በስምምነታቸው ውስጥ የየአገራቱን የኢሚግሬሽን ሕግጋቶችን የሚተላለፉ ተጓዞች ወደ ትውልድ አገራቸው የሚመለሱበት የፖሊስ አፈጻጸም ላይም ተስማምተዋል።
የአየር መንገዶች ሽርክን ስምምነት
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሁለቱ ፕሬዝዳንቶች ከዚህ ቀደም የደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ እና የኬንያ አየር መንገድ በሽርክና ‘ፓን-አፍሪካን አየር መንድ’ ለመፍጠር የደረሱት ስምምነት ተፈጻሚነት ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ለበርካታ ዓመታት በአየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪ ውስጥ ውጤት የራቃቸው ሁለቱ አየር መንገዶች በሽርክና ‘ፓን-አፍሪካን’ አየር መንገድ ለማቋቋም ከስምምነት ደርሰው ነበር።
ፕሬዝዳንት ራማፎሳ፤ “ሁለታችንም በአህጉሪቱ ድርሻዎችን ይዘናል ስትራቴጂካዊ አጋርነት መፍጠር ፍላጎት አለ” ብለዋል።
ትርፋማ ያልሆኑት እና በመንግሥት ድጎማ የሚንቀሳቀሱት ሁለቱ አየር መንገዶች ከአንድ ዓመት በፊት የደረሱት ስምምነት ያለበት ደረጃ እስካሁን ግልጽ አይደለም።
ፕሬዝዳንት ራማፎሳ እና ፕሬዝዳንት ሩቶ ከሁለቱ አገራት የንግድ ሥራዎች ጋር በተያያዘም ስምምነቶችን ተፈራርመዋል።
መሪዎቹ ሦስት የመግባቢያ ስምምነቶች ፈረመዋል። ከስምምነቶች መካከል አንዱ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የንግድ ልዩነት ላይ ያተኩራል።
በአሁኑ ወቅት ሁለቱ አገራት ባላቸው የንግድ ልውውጥ ደቡብ አፍሪካ ብዙ ምርት ወደ ኬንያ ልካ በአንጻሩ ከምሥራቅ አፍሪካዊቷ የምታስገባው ምርት ያነሰ ነው።
እአአ 2021 ኬንያ 33 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን ወደ ደቡብ አፍሪካ የላከች ሲሆን፤ በተቃራኒው 408 ሚሊዮን ዶላር ከፍላ ምርቶችን ከደቡብ አፍሪካ አስገብታለች።












