ኢትዮጵያ ለኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ከቀናት በኋላ ልትጀምር ነው

 የኤሌክትሪክ የኃይል ሽያጭ የማስተላለፍ የሙከራ

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Electric Power

ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገር ኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ኅዳር 5/2015 ዓ.ም ልትጀምር መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የኤሌክትሪክ የማስተላለፍ የሙከራ ሥራ ጥቅምት 29/2015 ዓ.ም በስኬት መከናወኑን ተከትሎም ወደ ኬንያ የሚደረገው የኤሌክትሪክ ኃይል የወጪ ንግድ ሊጀመር እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ መለስ ዓለም ገልጸዋል።

አገራቱን በሚያገናኘው 500 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር ላይ የኃይል ማስተላለፍ የሙከራ ሥራ በይፋ መጀመሩን ያስታወቁት የፕሮጀክቱ የሳይት ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ አያሌው ናቸው።

ኤሌክትሪክ የማስተላለፍ ሙከራው በስኬት መከናወኑን ያስታወቁት ሥራ አስኪያጁ ይህም በቅርቡ አገሪቱ የምታደርገው የኃይል ሽያጭ በአስተማማኝ ሁኔታ እንደሚሄድ አመላካች ነው ማለታቸውን ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ከዚህ ቀደም የተለያዩ የኤሌክትሮ ሜካኒካል መሳሪያዎች ፍተሻዎች እንዲሁም ከቀናት በፊት የመገናኛ ሲግናል በመላክ ከኬንያ ኔትወርክ ጋር ማገናኘት መቻሉን ሥራ አስኪያጁ ማስታወቃቸው ተጠቅሷል።

የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፉ በይፋ ሲጀመርም በሕብረተሰቡ ላይ አደጋ እንዳይደርስ መስመሩ ከሚያልፍባቸው ዞኖች ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይትና የግንዛቤ ማስጨበጫ መካሄዱም ተገልጿል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ የኃይል ማስተላለፍ ሙከራው በሚከወንበትም ወቅት ምንም አደጋ አለመድረሱንም አቶ ቴዎድሮስ መናገራቸው ተጠቁሟል።

የግንባታ ሥራው በ2008 የተጀመረው የኢትዮ- ኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር 334.5 ሚሊዮን ዶላር እንደፈጀ ከተቋሙ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።

የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ የግንባታ ሥራ ከአራት ዓመት በፊት መጠናቀቁ ይታወሳል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ በኩል የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ግንባታ እና የፍተሻ እንዲሁም የሙከራ ሥራዎች ቢጠናቀቁም በኬንያ በኩል ቀሪ የዝርጋታ እና የግንባታ ሥራዎች እንዳሉ እየተነገረ መጀመር ከነበረበት ወቅት እየተጓተተ ረዘም ያሉ ወራት ተቆጥረዋል።

የማስተላለፊያ መስመር የግንባታ ሥራው ሲኢቲ በተሰኘ የቻይና ኩባንያ ሲከናወን የኮንቨርተር ጣቢያውና ሌሎች ተግባራት ደግሞ ሲመንስ በተሰኘ ኩባንያ መከናወኑ ተገልጿል።

ለምሥራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር ከፍተኛ ስፍራ ያለው ይህ ፕሮጀክት 1.3 ቢሊዮን ዶላር ፈጅቷል።

አገራቱን የሚያገናኘው የኤሌክትሪክ መስመር 500 ኪሎ ቮልትና ከኢትዮጵያ በኩል 440 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ በአጠቃላይ ከ1 ሺህ ሜትር በላይ ርዝማኔ ያለው ነው።

ወጪውም ከዓለም ባንክ በተገኘው ብድር 684 ሚሊዮን ዶላር፣ ለኢትዮጵያ 441 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ለኬንያ 27.4 ቢሊዮን ዶላር የተሸፈነ ነው።

የአፍሪካ ልማት ባንክም ይህንኑ በደቡብ ኢትዮጵያ ከሚገኘው የግልገል ጊቤ ሦስት ግድብ ጋር የሚያገናኘውን የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ድጋፍ ለኢትዮጵያ 232 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ለኬንያ 116 ሚሊዮን ዶላር አጽድቋል።

ለኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ እና ለሌሎች ሥራዎች በብድር ከተገኘው በተጨማሪ አገራቱም ይህንን ትልቅ ፕሮጀክት ለመስራት የራሳቸውን ወጪ አድርገዋል።

ፕሮጀክቱ በምሥራቅ አፍሪካ ባሉ አገራት መካከል ድንበር ዘለል የኃይል ንግድ እንዲሁም ትስስርን ለማስተባበር በአውሮፓውያኑ 2005 የተቋቋመው ቀጠናዊ ተቋም ኢስተርን አፍሪካ ፓወር ፑል አካል ነው።

በአጠቃላይ የኃይል ልማት እና ተግባር የማስተባበር ሥልጣን የተሰጠው ተቋም ዋና ጽህፈቱ በአዲስ አበባ የሚገኝ ሲሆን፣ አስራ አንድ አባል አገራት አሉት።

እነሱም ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሱዳን፣ ታንዛንያ፣ ኡጋንዳ እና ሊቢያ። ኮንጎ (ዲአርሲ)፣ ሩዋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ ናቸው።

ፕሮጀክቱ እነዚህንም አገራት በኃይል የማስተሳሰርና የማዋሃድ አቅም እንዳለው ይነገራል።

በሁለቱ አገራት የተዘረጋው የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመርም እስከ 2000 ሜጋ ዋት የመሸከም አቅም ያለው ነው።