በፓኪስታን ቁርዓን አቃጥሏል የተባለው ግለሰብ በደቦ ፍርድ ተገደለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በማዕከላዊ ፓኪስታን ቁርዓን አቃጥሏል የተባለው ግለሰብ በደቦ ፍርድ መገደሉን ፖሊስ ገለጸ።
በፑንጃብ ግዛት ቅዳሜ ዕለት ከተፈጸመው ግድያ ጋር በተያያዘ ከ80 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ ገልጿል።
ህዝቡ ግለሰቡን ከመንጠቁ በፊት በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደነበር ዘገባዎች ጠቁመዋል።
አስከሬኑ ለቤተሰቦቹ የተሰጠ ሲሆን እሑድ ዕለት ስርዓተ ቀብሩ ተፈጽሟል።
የፓኪስታን ጠቅላይ ሚንስትር ኢምራን ካሃን በግድያው ጥፋተኛ የሚሆኑት በሕግ እንደሚጠየቁ ገልጸው ግለሰቡን የማዳን ተግባራቸውን ያልተወጡ የፖሊስ አባላት ላይ ሪፖርት እንዲደረግ ጠይቀዋል።
መንግስት "ከህግ ውጭ ፍርድ በሚወሰድ ሰው ላይ ምንም ትዕግስት የለውም" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
የፖሊስ ኃላፊው ሙናዋር ሁሴን በ40ዎቹ የዕድሜው ክልል ውስጥ የሚገኘውን ግለሰብ ራሱን ስቶ ዛፍ ላይ ታስሮ በፖሊሶች መገኘቱን ጠቁመዋል። ግለሰቡ የተገደለባት ካኔዋል ከላሆር በደቡብ-ምዕራብ 275 ኪሜ ርቀት ላይ ትገኛለች።
ሁሴን ለሮይተርስ የዜና ወኪል "ዱላ፣ መጥረቢያ እና የብረት ዘንግ የያዙ የመንደሩ ነዋሪዎች ግለሰቡን ገድለው ሰቅለውታል|" ብለዋል።
ክስተቱ በተፈጸመበት ቱላምባ የሚገኘው የፖሊስ ጣቢያ አዛዥ ሙናዋር ጉጃር ለኤፒኤን የዜና ወኪል አንደገለጹት ሟቹ ላለፉት 15 ዓመታት የአዕምሮ ህመም ነበረበት።
በተመሳሳይ ከሁለት ወራት በፊት ስሪላንካዊ የፋብሪካ ስራ አስኪያጅ የነበረ ግለሰብ በፑንጃብ ግዛት ውስጥ በሲልኮት ከተማ ሐይማኖትን ደፍሯል በሚል በደቦ ፍርድ ተደብድቦ ተገድሏል።
በፓኪስታን የሐይማኖት መድፈር ሕግ እስልምናን የሚሳደብ ሁሉ የሞት ፍርድ ይጠብቀዋል ይላል። ተቺዎች ግን ሕጉ በቁጥር አነስተኛ የሆኑ ሀይማኖቶችን ለማደን እና አናሳዎችን ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ዒላማ ያደረገ ነው ይላሉ።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች ሕጉ ከሃይማኖት ጋር አነስተኛ ወይም ምንም ግንኙነት በሌላቸው ጉዳዮች ላይ ጭምር ግላዊ ቅራኔዎችን ለመፍታት ጥቅም ላይ ውሏል ይላሉ።












