ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በጋና ባጋጠመ ፍንዳታ ቢያንስ 17 ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ
በምዕራባዊ ጋና በምትገኝ የማዕድን ማውጫ ከተማ አካባቢ በደረሰ ከፍተኛ ፍንዳታ ቢያንስ 17 ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ባለስልጣናት ገልጸዋል።
ፖሊስ እንዳለው ለማዕድን ቁፋሮ የሚያገለግሉ ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን ጭኖ ሲሄድ የነበረ ተሽከርካሪ ቦንጎሶ በምትባለዋ ከተባ ከሞተርሳይክል ጋር መጋጨቱን ተከትሎ ነው ፍንዳታው የደረሰው።
ሰዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች ባጋሯቸው ምስሎችና ተንቀሳቃሽ ምስሎች ላይ ፍንዳታው በደረሰበት አካባቢ ትልቅ ጥቁር ጭስ ጉዳት ከደረሰባቸው ትልልቅ ህንጻዎች ከፍ ብሎ ታይቷል። በአካባቢውም የህንጻዎች ፍርስራሽ ተከምሮ ተስተውሏል።
በሚዘገንን መልኩ የሞቱ ሰዎች አስክሬን በፍንዳታው አካባቢ ታይተዋል። አደጋው የደረሰበት መኪና የነበረበት ቦታ ደግሞ ትልቅ ጉድጓድ ፈጥሯል።
ቢያንስ 59 ሰዎች በዚሁ ፍንዳታ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን አንዲት ሴት ደግሞ በአስጊ ሁኔታ ውስጥ ሆና በሆስፒታል ህክምናዋን እየተከታተለች ነው ብለዋል የአገሪቱ የማስታቂያ ሚኒስትሩ ኮጆ ኦፖንግ ንኩርማህ።
የጋናው ፕሬዝዳንት ናና አኩፎ አዶ ደግሞ መከላከያ ኃይሉ በድንገተኛ ስራው እርዳታ ለማድረግ በቦታው መድረሱን ገልጸዋል።
ፕሬዝደንቱ አክለውም "ወታደሮች ሁኔታውን ለመቆጣጠር በቦታው ደርሰዋል። የአገራችን የአደጋ አመራር ኤጀንሲም ፈጣን የሆነ ምላሽ ለመስጠት ኃላፊነቱን ወስዷል'' ብለዋል።
"በእውነት በጣም የሚያሳዝን እና ልብ የሚሰብር አደጋ ነው" ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
በአሁኑ ሰዓት የድንገተኛ አደጋ ምላሽ ቡድን በህይወት የተረፉ ሰዎች ካሉ ለማዳን እና ሌሎች ሰዎችን ከአካባቢው ለማራቅ ርብርብ እየተደረገ ነው።
ፖሊስም አደጋው በደረሰበት አካባቢ የሚገኙ ከተሞች የትምህርት ቤት ክፍሎችን፣ የቤተ እምነት ተቋማትን እና ቤታቸውንም ቢሆን ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ድጋፍ ለማድረግ እንዲከፍቱ ጠይቋል።
"ማህበረሰቡ አሁን ላይ እንዲረጋጋ እንጠይቃለን። ሁኔታውን ለመቆጣጠርና የተረፉትን ለማዳን እንዲሁም የሞቱትን ለመሰብሰብ እየጣርን ነው'' ብሏል ፖሊስ።
ምናልባት ሁለተኛ ፍንዳታ እንዳያጋጥም በሚልም የፈንጂ አምካኝ ቡድን በስፍራው እንደደረሰም መንግሥት አስታውቋል።