ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኦስትሪያ ክትባትን ግዴታ በማድረግ የመጀመሪያዋ የአውሮፓ አገር ልትሆን ነው
የኦስትሪያ የታችኛው ምክር ቤት አስገዳጅ የክትባት ሕግን ማጽደቁን ተከትሎ አገሪቱ የኮሮናቫይረስ ክትባት መውሰድን ግዴታ ለማድረግ ተቃርባለች።
ሕጉ የሚተገበረው ከየካቲት ጀምሮ ሲሆን፤ ክትባት መውሰድን ግዴታ በማድረግ ኦስትሪያ ከአውሮፓ የመጀመሪያዋ አገር ትሆናለች።
ክትባት ያልወሰዱ ጎልማሶች 2,994 ፓውንድ ይቀጣሉ።
እስካሁን ድረስ 72% ኦስትሪያውያን ተከትበዋል።
አስገዳጁ የክትባት ሕግ ለመተግበር በላይኛው ምክር ቤት መጽደቅ ይጠበቅበታል። ከዚያም ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ቫን ደር ቤሊን ይፈርሙበታል።
ሕጉ በአውሮፓውያኑ እስከ የካቲት 2024 ድረስ ተግባራዊ እንደሚሆን ተገልጿል።
መንግሥት ያልተከተቡ ሰዎች ማበረታቻ የሚሆን 1.4 ቢሊዮን ፓውንድ መድቧል።
የጤና ሚኒስትሩ ውልፍጋንግ ሙክስቲን ለምክር ቤት አባላት ባደረጉት ንግግር ሕጉን "ጠቃሚ፣ ፈር ቀዳጅ፣ ዘላቂ ለውጥ ፈጣሪ" ብለውታል።
ቫይረሱን ድል መንሳት የሚቻለው በክትባት በመሆኑ ሕጉን እንደሚደግፉ ቻንስለር ካርል ነህማር ተናግረዋል።
የምክር ቤቱ ቀኝ ዘመም አባላት እና ሦስት ተቃዋሚዎችም ሳይቀሩ ሕጉን ደግፈው፤ 137 ለ33 በሆነ ድምጽ አልፏል።
በሌላ በኩል ቀኝ ዘመሙ ፍሪደም ፓርቲን የሚመሩት ሐርበርት ኪክል "ሕጉ ኦስትሪያ አምባገነናዊ አገር እንድትሆን መንገድ ይከፍታል" ብለዋል። ክትባት ባለመውሰድ እስከመጨረሻው ድረስ ሕጉን እንደሚታገሉም ዝተዋል።
ሕጉን በመቃወም በመዲናዋ ቪየና እስከ 40 ሺህ የሚደርሱ ሰዎችን ያሳተፉ የተቃውሞ ሰልፎች ሲካሄዱ ቆይተዋል።
የክትባት ተቃዋሚዎች እና ቀኝ ዘመሞች በዋነኛነት ተቃውሞውን ያቀጣጥላሉ።
ግሪክን ጨምሮ ሌሎች አገሮችም አስገዳጅ የክትባት ሕግ እያወጡ ነው።
ኦስትሪያ ይህንን ሕግ ያወጣችው አንዳንድ የአውሮፓ አገራት የኦሚክሮን ስርጭት በመጠኑ ጋብ ማለቱን ተከትሎ ሕጋቸውን እያለሉ ሳለ ነው።