ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሆነ ብላ ኮቪድ-19 የተያዘችው ዘፋኝ ሕይወቷ አለፈ
ቼክ ሪፐብሊክ ውስጥ በሐገረሰብ ሙዚቃ አቀንቃኝነቷ የምትታወቀው ግለሰብ ሆነ ብላ ኮቪድ እንዲያዛት ካደረገች በኋላ ሕይወቷ ማለፉን ልጇ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ሃና ሆርካ የተሰኘችው የ57 ዓመቷ ዘፋኝ ክትባት ያልወሰደች ሲሆን ማሕበራዊ ድር አምባው ላይ ኮቪድ ቢይዘኝም እየተሻለኝ ነው ብላ ከፃፈች ከሁለት ቀናት በኋላ ነው ሕይወቷ ያለፈው።
ልጇ ጃን ሬክ እንዳለው እሱና አባቱ ኮቪድ ይዟቸው ሳለ ነው ኮቪድ ይዟቸው የነበረ ሰዎች የሚሰጣቸውን ወረቀት ለማግኘት ስትል ሆነ ብላ ኮቪድ የተያዘችው።
ቼክ ሪፐብሊክ ረቡዕ ዕለት እስካዛሬ ከታየው ቁጥር ያየለ የኮቪድ አሃዝ ይፋ አድርጋለች።
ሬክና አባቱ ክትባት ቢከተቡም በፈረንጆቹ ገና ሰሞን ነው ኮቪድ የያዛቸው። ነገር ግን እናቱ ከነሱ ላለመራቅ ስትል ሆነ ብላ ራሷን ለኮቪድ አጋልጣለች።
"እኛ ፖዘቲቭ በመሆናችን ለአንድ ሳምንት ያክል ጊዜ ከኛ ርቃ መቆየት ነበረባት ነገር ግን ሁሌም ከኛ ጋር ነበረች" ሲል ልጇ ተናግሯል።
ቼክ ሪፐብሊክ ውስጥ የተለያዩ ቦታዎችን ለምሳሌ ባር፣ ሲኒማ አሊያም ካፌ ለመጎብኘት የክትባት ወረቀት አሊያም ከዚህ በፊት ኮቪድ ይዞኛል የሚል ማስረጃ ማቅረብ ግድ ይላል።
የሬክ እናት ቼክ ሪፐብሊክ ውስጥ አሉ ከሚባሉ ነባር የሐገረሰብ ሙዚቃ ባንዶች አንዱ የሆነው አሶናንስ አባል ነበረች።
ኮቪድ እንዲያዛት ራሷን ያጋለጠችው የትኛውም ቦታ እንደፈለገች መንቀሳቀስ እንድትችል ነበር ይላል ልጇ።
ከመሞቷ ሁለት ቀናት አስቀድሞ "አሁን ሲኒማ፣ ሳውና እንዲሁም ኮንሰርት መታደም እችላለሁ" ስትል ለጥፋ ነበር።
እሑድ ዕለት ሕይወቷ ከማለፉ በፊት መልካም ጤንነት ላይ እንዳለች በመናገር ወጣ ብላ ለመመለስ ከተነሳች በኋላ ወገቤን ያዝ አድርጎኛል ብላ ወደ መኝታ ክፍሏ ገብታ ትጋደማለች።
"በ10 ደቂቃ ውስጥ ሁሉም ነገር አበቃለት። ሞተች" ሲል ልጇ ተናግሯል።
ምንም እንኳ እናቱ ባትከተብም ስለ ክትባት የሚነገሩ የሴራ ትንታኔዎችን እንደማታምን ሬክ ይናገራል።
"ኮቪድ ቢይዘኝና ብድን ይሻላል ከምከተብ ብላ ነበር የምታምነው። ብንከተብ ውስጣችን ይቀበራል ብላ ግን አታምንም ነበር።"
ጃን ሬክ እንደሚለው የእናቱ ባንድ አሶናንስ በሐገረሰብ ሙዚቃ "የተከበረ" ባንድ ነው።
ቼክ ሪፐብሊክ ውስጥ በኮቪድ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ጊዜ እየጨመረ መጥቶ ረቡዕ ዕለት 28 ሺህ 469 ሰዎች በበሽታው መያዛቸው ይፋ ተደርጓል።
10.7 ሚሊየን ሕዝብ ያላት ሃገረ ቼክ መንግሥት በሽታውን ለመቆጣጠር የተለያዩ ዘዴዎችን ይፋ አድርጓል። ከእነዚህ መካከል ለተማሪዎችና ሠራተኞች ምርመራ ማድረግ አንዱ ነው።
ኮቪድ የያዛቸው ነገር ግን የበሽታው ምልክት የማይታይባቸው ሰዎች ከዚህ በፊት ለ14 ቀናት ራሳቸውን አግልለው ይቆዩ የነበረው አሁን ወደ 5 ቀናት ተቀንሶላቸዋል።
ረቡዕ ዕለት የቼክ መንግሥት ለአንዳንድ የሕብረተሰቡ አባላት ግዴታ አድርገዋል ያለውን ክትባት መሰረዙን አስታውቋል።
በያዝነው ወር መባቻ በርካታ የዋና ከተማዋ ፕራግና ሌሎች ዋና ዋና ከተማ ነዋሪዎች ይህንን ሕግ በመቃወም ሰልፍ ወጥተው ነበር።
ከቼክ ሕዝብ 63 በመቶው ሙሉ በሙሉ ተከትቧል። በአውሮፓ ሃገራት አማካይ የክትባት መጠን 69 በመቶ ነው።