የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ውጤት ካሳጡ ምክንያቶች መካከል አምስቱ

ኢትዮጵያ ካሜሩን በተዘጋጀው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፋ ሦስት ጨዋታዎችን አድርጋ ከነበረችበት ምድብ ማለፍ ባለመቻሏ ከውድድሩ ተሳናብታለች።

በምድብ 'ሀ' ከካሜሩን፣ ቡርኪናፋሶ እንዲሁም ኬፕ ቬርድ ጋር ተደልድላ የነበረችው ኢትዮጵያ በሁለቱ ጨዋታዎች ተሸንፋ በአንድ አቻ በመውጣት በአንድ ነጥብ ውድድሩን አጠናቃለች።

በአፍሪካ ዋንጫ ከተሳተፉ 24 አገራት መካከል በአማካይ ወጣት የሚባሉ ተጨዋቾችን ከያዙ ቡድኖች ውስጥ የተመደበችው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ዙር 16 መሻገር ተስኖት ወደ አገሩ ተመልሷል።

ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት በተሳተፈችበት የደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ዋንጫ በተመሳሳይ በሁለት ጨዋታዎች ተሸንፋ በአንድ አቻ ውጤት መሰናበቷ የሚታወስ ነው።

ለመሆኑ ዋሊያዎቹ በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፏቸው ወደ ቀጣይ ዙር እንዳይልፉ ያገዳቸው ምንድነው? ልምድ? ተጫዋቾች የሚፈፅሙት ስህተት? ወይስ ሌላ?

ከዚህ በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደፊት እንዳይገሰግስ ያደረጉ የተባሉ አምስት አበይት ምክንያቶችን እናያለን።

ልምድ

አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከመጨረሻው ጨዋታ በኋላ ለዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው ነበር።

በዚህ መግለጫቸው ወደቀጣዩ ዙር ላለማለፋቸው እንደ አንደኛው ምክንያት አድርገው የጠቀሱት የተጫዋቾች ልምድ ማነስ ነው።

"ብዙ ወጣት ተጫዋቾች አሉን። እነዚህ ተጫዋቾች ልምድ እያገኙ ሲሄዱ ነገሮች ይሻሻሉ። በሚቀጥለው የአፍሪካ ዋንጫ ተመልሰን እንመጣለን የሚል ተስፋ አለኝ" ብለዋል።

ለተለያዩ የስፖርት ትንታኔ አውታሮች በመፃፍ የሚታወቀው ፍሬው አሥራት ይህንን የአሰልጣኑን ሐሳብ ትክክል ነው በማለት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ልምድ ያንሳቸዋል ይላል።

"ሦስት ተጫቾች ብቻ ናቸው ቀደም ባለው የአፍሪካ ዋንጫ የተጫወቱት። ከእነዚህ መካከል ጀማል በሦስተኛ ግብ ጠባቂነት ቢሄድም አልተሰለፈም። ሽመልስንም በጉዳት ምክንያት አልሄደም። ጌታነህ ብቻ ነው መሰለፍ የቻለው።"

አሁን ካሜሩን ሄዶ በመጣው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ጥቂት ተጫዋቾች ሩዋንዳ ተካሂዶ በነበረው የቻን ውድድር ላይ እንደተሳተፉ ፍሬው ያስታውሳል።

ነገር ግን እንደ አፍሪካ ዋንጫ ዓይነት ትልቅ ውድድር ላይ የተሳተፉ ብዙ ተጫዋቾችን ያቀፈው ብሔራዊ ቡድኑ ልምድ ያንሰዋል ቢባል ስህተት አይደለም ይላል ፍሬው።

አሠልጣኝ ውበቱ አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች ከኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ የተገኙ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ከዚህ ውድድር አንድ ያገኙት ነገር ቢኖር ልምድ እንደሆነ ይናገራሉ።

"ልምድ በአንድ ጀንበር አይገኝም። ለዚህም ነው ጨዋታዎችን በማድረግ የተሻለ ልምድ ማግኘት አለብን ብዬ የማስበው።"

ነገር ግን ፍሬው "በዚህ የአፍሪካ ዋንጫ ታላላቅ ቡድኖችን ያሸነፉት ኢኳቶሪያል ጊኒና ኮሞሮስን ስንመለከት አብዛኞቹ ተጫዋቾች በፈረንሳይ፣ በጣልያንና በስፔን በሚገኙ ትናንሽ ዲቪዚዮኖች የሚጫወቱ ናቸው" ይላል።

"ይሄን ተመልክተን የእኛ ልጆች አገር ቤት በመጫወታቸው ነው የተጎዳነው ማለት ላያሳምን ይችላል። ምናልባት የእኛ ሊግ ትናንሽ ናቸው ከሚባሉት ዲቪዚዮኖች ያነሰ ይሆን? እኔ አላውቅም።"

ስህተት

ዋሊያዎቹ ከዚህ በፊትም የሚታሙበትን በ2021 የአፍሪካ ዋንጫም የተስተዋለባቸው አንድ ችግር ቀላል የሚባሉ ስህተቶችን መፈፀም ነው።

በፈረንጆቹ 2013 በደቡብ አፍሪካ ተካሂዶ በነበረው የአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታ ከዛምቢያ ጋር የተፋለሙት የዋሊያዎቹ ግብ ጠባቂ ከክልሉ ውጪ በፈፀመው ስህተት በቀይ ካርድ እንደተሰናበተባቸው የሚታወስ ነው።

ፍሬው ይህ በመጀመሪያው ጨዋታ የቡድን አባልን በቀይ ካርድ የማጣት ክስተት በዚህኛው የአፍሪካ ዋንጫ መደገሙ አሳሳቢ ነው ይላል።

"ቀይ ካርዱን [ያሬድ ባየህ የኬፕ ቬርድ ተጫዋች ላይ የፈፀመው ጥፋትን ተከትሎ የተሰጠው] ማንሳት ትችላለህ። ንቁ አለመሆኑ እና አደገኛ ኳሶችን ተመልክቶ በፍጥነት እርምጃ አለመውሰድ ይታይብናል።"

ቡድኑ በካሜሩን አራት ለአንድ እንዲሁም በኬፕ ቬርድ አንድ ለዜሮ ሲሸነፍ የተመዘገቡት እንዲሁም ከቡርኪና ፋሶ ጋር አቻ ሲለያይ የተቆጠረበት ግብ ሊወገዱ በሚችሉ ቀላል ስህተቶች የተፈጠሩ ናቸው ሲል ፍሬው ያምናል።

ፍሬው እንደሚለው ብሔራዊ ቡድኑ ተቀባብሎ ወደ መሃል ሜዳ ያሻገረው ኳስ ተመልሶ ዋሊያዎቹ ላይ አደጋ ሲፈጥር በተደጋጋሚ ይታያል።

ዋሊያዎቹ በማጣሪያ አሊያም የዋንጫ ውድድር ጨዋታዎች ላይ ሊወገዱ የሚችሉ ስህተቶች ሲፈፅሙ እንዲሁ የትኩረት ማጣት ሲታይባቸው ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም።

አሠልጣኝ ውበቱ አባተም በዚህ የሚስማሙ ይመስላሉ። ከካሜሩን ጨዋታ በፊት ለጋዜጠኞች አሠልጣኙ ሲናገሩ ኬፕ ቬርድ በመጀመሪያዋ አጋማሽ መገባደጃ ያስቆጠሩት ጎል የተጫዎች የትኩረት ማነስ እንደሆነ ተናግረው ነበር።

የአጨዋወት ስልት

የዋሊያዎቹን የምድብ ጨዋታዎች በአሃዝ ስንመለከት ከካሜሩንና ከኬፕ ቬርድ ጋር በነበሩ ጨዋታዎች ብልጫ እንደተወሰደባቸው መመልከት ይቻላል።

ምንም እንኳ በመጀመሪያው ጨዋታ ቡድኑ አብዛኛውን ክፍለ ጊዜ አንድ ተጫዋች ጎድሎበት በ10 ተጫዋቾች ቢጫወትም ኢትዮጵያ የምትታወቅበት ኳስን ተቆጣጥሮ የመጫወት ስልት ብዙ አልተስተዋለም።

በካሜሩን ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ብዙዎችን ያስደነቀ ብቃት ያሳዩት ዋሊያዎቹ በሁለተኛው አጋማሽ ፍፁም ብልጫ ተወስዶባቸው ታይተዋል።

"በተለይ በተጋጣሚዎች የግብ ክልል አቅራቢያ ብዙም አመርቂ ነገር አላሳየንም" ይላል ፍሬው።

ቡርኪና ፋሶ ተዳክማ በቀረበችበት፤ ዋሊያዎቹ ደግሞ የተሻለ ብቃት ያሳዩበትን የመጨረሻው ግጥሚያ የድኅረ-ጨዋታ ትንተናን ስንመለከት ዋሊያዎቹ ኳስን ቢቆጣጠሩም በተቀናቃኝ ግብ አካባቢ የነበራቸው ድርሻ ቀዝቀዝ ያለ ነበር።

"ኳስን መሥርቶ መጫወት የሚፈልግ ቡድን ቢሆንም ብዙዉን ጊዜ ኳሷን በራሱ ሜዳ የሚያንሸራሽር ስብስብ ሆኖ ነው ያገኘሁት። ወደፊት ያደርግ የነበረው እንቅስቃሴም ይህን ያህል አስፈሪ አልነበረም።"

ፍሬው ሌላው በቡድኑ ላይ ያስተዋለው ነገር ቢኖር "ፕላን ቢ እንኳን እንደሌለን ነው" በማለት፤ አንድ ተጫዋች በጉዳት አሊያም በካርድ ሲወጣ አሊያም ሲቀየር ሙሉ በሙሉ የቡድን የጨዋታ ስልት ይቀየራል በማለት ይናገራል።

የተጨዋቾች አቅም

አሠልጣኝ ውበቱ ከካሜሩን ሽንፈት በኋላ ተጫዋቾቼ የአቅም ማነስ የለባቸውም ምናልባት የሥነ ልቡና መዳከም ይሆናል ያለባቸው ሲሉ ተደምጠዋል።

ነገር ግን ፍሬው "ግልፅ የሆነ መደካም ነበር" በማለት በዚህ የአሰልጣኙ ሐሳብ አይስማማም።

"ጨዋታዎቹ ላይ 50/50 የሆኑ ኳሶችን ታግሎ መቀማት፣ በአየር የሚመጡ ኳሶችን ተሻምቶ ማሸነፍ፣ በመስመር በኩል ፈጣን አጥቂዎችን መቋቋም የሚችል ተከላካይ ነበረን?"

ፍሬውን ጨምሮም በርካታ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሐሳባቸውን ሲሰጡ የነበሩ የእግር ኳስ ወዳጆች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አባላት በተክለ ሰውነት ከሌሎቹ አነስ እንደሚሉ ትዝብታቸውን ሲያሰፍሩ ነበር።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ሌላው ሲነሳ የነበረው ጉዳይ ጋቶች ፓኖምን የመሰሉ ተጋጣሚዎችን መቋቋም የሚችል ተክለ ሰውነት ያላቸው ተጫዋቾች የመሰለፍ ዕድል አለማግኘታቸው የኳስ ወዳጆች መነጋገሪያ ነበር።

የአሠልጣኙ አሠላለፍ ስልት

አሠልጣኝ ውበቱ አባተ በተለምዶ 4-4-3 አሠላለፍ በመጠቀም ይታወቃሉ። ይህም አራት ተከላካዮች፤ ሦስት አማካዮች እና ሦስት አጥቂዎች ማለት ነው።

በዚህ አሠላለፋቸው አምበሉን ጌታነህ ከፊት ለፊት የ2013 የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ኮከብ ግብ አግቢ የሆነው አቡበከር ናስርን በግራ አማኑዔል ገብረሚካኤል አሊያም ዳዋ ሆጤሳን በቀኝ ማሠለፍን ይመርጣሉ።

ነገር ግን ከቡርኪና ፋሶ ጋር በነበረው የመጨረሻው የምድ ጨዋታ አሠልጣኙ በአራት ተከላካይ፤ በሁለት የተከላካይ አማካይ፤ በሦስት ወደፊት በሚገፉ አማካዮችና በአንድ አጥቂ ነው ወደሜዳ የገቡት።

በርካታ የእግር ኳስ ተንታኞችና ጋዜጠኞች እንደሚስማሙት ለምሳሌ አቡበከር ከኬፕ ቬርድ በቀኝ፣ ከካሜሩን ፊት ለፊት ከቡርኪና ጋር በግራ እንዲጫወት መደረጉ ያለውን አቅም አሟጦ እንዲያጠቀም አድርጎታል።

አቡበከር ብቻ ሳይሆን ሌሎቹም ተጫዋቾች በክለብ ደረጃ ከሚጫወቱበት በተለየ መልኩ ለብሔራዊ ቡድን እንዲሰለፉ መደረጋቸው አግባብ አይደለም የሚሉ ደምፆች ተሰምተዋል።

ፍሬው ከዚሁ ትይዩ ሊነሳ ይገባል የሚለው ወቅታዊ ብቃታቸው መልካም ያልሆነ ተጫዋቾች በቡድኑ መካከተታቸው አሊያም ጥሩ ብቃት ያላቸው ተጫዋቾች አለመጠራታቸው ነው።

የዋሊያዎቹ የወደፊት ዕጣ ፈንታ

ዋሊያዎቹ በሚቀጥለው የፈረንጆቹ ዓመት በሚደረገው የአፍሪካ ዋንጫ የመሳተፍ ዕድል አላቸው።

በእነዚህ ማጣሪያዎች ላይ ከላይ የተጠቀሱትን ጨምሮ ሌሎች ቡድኑ ያሉበትን ችግሮች መቅረፍ አስፈላጊ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ።

"የግድ ውድድር አሊያም ማጣሪያ መጠበቅ የለብንም። ከዚያ ይልቅ ቡድኑ እየተሰበሰበ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ማድረግ አለበት" ይላል ፍሬው።

ፍሬው አክሎም በሌሎች አገራት የሚጫወቱ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች ተፎካክረው የአገር ውስጥ ተጫዋቾችን የሚበልጡ ከሆነ ሊጠሩ ይገባል ይላል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ ከተሳተፉ ቡድኖች ከአፍሪካ ውጪ የመጣ ተጫዋች ያላካተተ ብቸኛው ስብስብ ነበር።

ፍሬው ጨምሮ ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች ከአገር ቤት ውጭ ሄደው መጫወት እንዳለባቸው ይሄ ደግሞ ለልምድ እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ ይጠቁማል።

የ2023 የአፍሪካ ዋንጫ በሚቀጥለው ዓመት በአይቮሪ ኮስት አዘጋጅነት እንደሚካሄድ ይጠበቃል። ውድድሩ ከቀደሙት በተለይ በክረምት ወራት ሰኔና ሐምሌ እንደሚካሄድ ይጠበቃል።

በዚህ ውድድር ኢትዮጵያ የማጣሪያ ጨዋታዋን ከየትኞቹ ቡድኖች ጋር እንደምታደርግ በቅርቡ ይታወቃል።