በኬንያ ባልተለመደ ሁኔታ መንታ ዝሆኖች መወለዳቸው ተነገረ

በዚህ ሳምንት በሰሜናዊ የኬንያ ክፍል በሚገኘው ብሔራዊ መካነ እንስሳት ውስጥ ባልተለመደ ክስተት መንታ ዝሆኖች ተወልደዋል።

ወንድ እና ሴት ሆነው የተወለዱት መንትያ ዝሆኖች ሳምቡሩ በተሰኘው የእንስሳት ማቆያ ውስጥ አስጎብኚዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ያያዋቸው በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ውስጥ ነበር።

'ቻሪቲ ሴቭ ዘ ኤልፋንት' የተሰኘ እና በዝሆኖች ጥበቃ ላይ የሚሰረ የሀገር ውስጥ ግብረ ሰናይ ድርጅት ይህን ክስተት ሲያጋጥመው ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን አመላክቷል።

ግብረ ሰናይ ድርጅቱ መንታ ዝሆኖች የመወለድ ዕድላቸው 1 በመቶ ብቻ እንደሆነ በመጠቀስ እንዲህ አይነት ክስተት ለመጨረሻ ጊዜ የተመዘገበው ከ16 ዓመት በፊት እንደ አውሮፓውያኑ በ2006 መሆኑን ገልጿል።

የግብረ ሰናይ ድርጅቱ መስራች ዶ/ር ኢየን ዳግላስ ሃሚልተን ለሮይተርስ ዜና ወኪል በሰጡት አስተያየት፤ የመጨረሻዎቹ መንታ ዝሆኖች ከተወለዱ በኋላ በሕይወት መቆየት አለመቻላቸውን አስታውሰው አሁን የተወለዱት መንትያ ዝሆኖች በሕይወት የመቆየታቸው እድል የሚወሰንበት በጣም ወሳኝ ጊዜ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

ብዙ ጊዜ ዝሆን እናቶች ሁለቱንም ልጆች ለመመገብ የሚያስችል በቂ ወተት አይኖራቸውም ያሉት መሰራቿ ሁሉም ሰው ዝሆኖቹ በህይወት እንዲቆዩ ሲመኝ ነበር ብለዋል።

የአፍሪካ ዝሆኖች ከማንኛውም አጥቢ እንስሳት በላይ ረጅም የእርግዝና ጊዜ አላቸው። በእርግዝና ለ22 ወራት ያህል የሚቆዩ ሲሆን በየአራት ዓመቱ ደግሞ ይወልዳሉ።

በዝሆን ጥርስ ንግድ እና በሌሎች ምክንያቶች ዝሆኖች በዓለም አቀፍ የተፈጥሮ ጥበቃ ማህበር ውስጥ በመጥፋት ላይ ያሉ ዝርያዎች ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል።

ከዚህ በተቃራኒ በኬንያ ባለፈው ዓመት ታትሞ በወጣው የመጀመሪያው የዱር እንስሳት ቆጠራ እንደሚያመለክተው የዝሆኖች ቁጥር በኬንያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየጨመረ መጥቷል።