ወላጆቻቸው የሚያጨሱ ልጆች አጫሽ የመሆን ከፍተኛ ዕድል እንዳላቸው ጥናት አመለከተ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ወላጆቻቸው የሚያጨሱ ታዳጊዎች እነሱም አጫሽ የመሆን አራት እጥፍ ዕድል እንዳላቸው በዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት አማካይነት የተሰራ አንድ አዲስ ጥናት አመለከተ።
በዚህም ምክንያት ዶክተሮች ሲጋራ የሚያጨሱ ወላጆችንና አሳዳጊዎችን ማጨስ እንዲያቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።
የፀረ ሲጋራ ማጨስ ዘመቻ እንቅስቃሴ እንዳለው ወላጆቻቸው የሚያጨሱ ታዳጊዎች 4.9 በመቶ እነሱም አጫሽ የመሆን ዕድል ሲኖራቸው፣ ወላጆቻቸው የማያጨሱ አቻዎቻቸው ግን የማጨስ ዕድላቸው 1.2 በመቶ ብቻ እንደሆነ አመልክቷል።
የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የጤና አገልግሎት ባዘጋጀው አዲስ ፊልም ላይ የጤና ባለሙያዎች በአዋቂዎች አጫሾችና ማጨስ በሚጀምሩ ልጆች መካከል ስላለው ግንኙነት ውይይት አድርገዋል።
የፀረ ማጨስ ዘመቻው አዋቂ አጫሾች በዙሪያቸው ባሉ ወጣቶች ሕይወት ላይ ስለሚፈጥሩት ተጽዕኖ በጥናት የተደገፈ መረጃን አቅርቧል።
አጠቃላይ ሐኪም የሆኑት ዶክተር ናያት አሪፍ እና የልጆች ሥነ ልቦና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ቤቲና ሆህነን ወላጆች ማጨስን እስከ መጨረሻው በመተው በልጆቻቸው ሕይወት ላይ የሚታይ በጎ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።
በውይይቱ ላይ የጤና ሚኒስትሯ ማጊ ትሮፕ፣ ይህ አዲሱ የጥናት ውጤት ወላጆች ማጨስ እንዲያቆሙ ተጨማሪ መነሳሻ ሊሆናቸው እንደሚችል ተስፋቸውን ገልጸዋል።
ሚኒስትሯ ጨምረውም የተጀመረው አዲሱ ፀረ ማጨስ ዘመቻ "ሲጋራ በትውልዶች መካከል ያለውን ተያያዥነት በማሳየት ወላጆች በልጆቻቸው ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ ያጎላል" በማለት ይህም "ከሲጋራ ማጨስ ለመገላገል ጥሩ አጋጣሚን ይፈጥራል" ብለዋል።
የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ለወላጆች፣ ለአሳዳጊዎች እንዲሁም ሲጋራ ማቆም ለሚፈልጉ ሰዎች የሚጠቅሙ የተለያዩ የድጋፍ አገልግሎቶች እንዳሉ ገልጸዋል።
ሲጋራ ለማቆም የሚያግዝ መተግበሪያ፣ በፌስቡክ ላይ የሚደረግ ድጋፍ፣ በየዕለቱ የሚላክ የኢሜይል እና የጽሁፍ መልዕክት እንዲሁም በኢንትርኔት ላይ የሚገኝ ግላዊ ሲጋራ የማቆም ዕቅድ መዘጋጀቱን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።














