አዘውትሮ ምሽት አራት ሰዓት አካባቢ መተኛት ለልብ ችግር የመጋለጥ እድልን ይቀንሳል- ጥናት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከምሽቱ 4 ሰዓት እስከ 5 ሰዓት ባለው ጊዜ አዘውትሮ መተኛት ለተሻለ የልብ ጤንነት እንደሚረዳ በ88 ሺህ በጎ ፈቃደኞች ላይ ጥናት ያደረጉ ተመራማሪዎች አስታወቁ።
በዩናይትድ ኪንግደም ባለ አንድ ቡድን በተደረገ ጥናት እንቅልፍ ከውስጣዊው የሰውነት ክፍላችን የጊዜ አቆጣጠር ጋር እንዲጣታም ማድረግ ለልብ ድካም እና ለስትሮክ የመጋለጥ እድልን እንደሚቀንስ ጠቁሟል።
የሰውነት ተፈጥሯዊ የ24-ሰዓት ምት ለደኅንነት እና ንቁ ለመሆን አስፈላጊ መሆኑን የሚገልጸው ጥናቱ እንደ የደም ግፊት ባሉ ሂደቶች ላይም ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል ይላል።
በአውሮፓ የልብ ጤና ጆርናል ላይ በታተመው በዚህ ጥናት ተመራማሪዎቹ በሰባት ቀናት ውስጥ በእንቅልፍ እና በእንቅልፍ ጊዜ ላይ ከጥናቱ ተሳታፊዎች መረጃን ለማሰባሰብ የእጅ ሰዓት የሚመስል መሳሪያ እንዲያጠልቁ አድርገዋቸዋል።
በመሳሪያው አማካኝነት በአማካይ በስድስት ዓመታት ውስጥ በልብ እና በደም ዝውውር ጤና ላይ ያለውን ሁኔታ ተከታትለዋል።
በዚህም ከ3,000 በላይ የሚሆኑ ተሳታፊዎች የልብ ችግር [የካርዲዮቫስኩላር] በሽታ ተገኝቶባቸዋል። በጥናቱ መሰረት ለዚህ ችግር የተጋለጡት ከምሽቱ 4 ወይም 5 ሰዓት ቀደም ብለው ወይም ዘግይተው ወደ አልጋ የማምራት ልምድ ያላቸው ሰዎች ላይ ነው።
ተመራማሪዎቹ እንደ ዕድሜ፣ የሰውነት ክብደት እና የኮሌስትሮል መጠን ያሉ የአንድን ሰው ለልብ ስጋት የሆኑ ሌሎች ነገሮችን ለማየት ሞክረዋል። ነገርግን ጥናታቸው መንስኤውንና ውጤቱን ማረጋገጥ አልቻለም።
ተመራማሪዎቹ እንደ ዕድሜ፣ የሰውነት ክብደት እና የኮሌስትሮል መጠን ያሉ አንድን ሰው ለልብ ችግር የሚያጋልጡ ሌሎች ነገሮችን ለማየት የሞከሩ ሲሆን ጥናታቸው መንስኤና ውጤቱን ማረጋገጥ እንዳልቻለ አስረድተዋል።
"በጥናታችን መንስኤው ላይ መደምደሚያ መስጠት ባንችልም በውጤቱ መሰረት ከመደበኛው የመኝታ ሰዓት ቀደም ብሎ ወይም ዘግይቶ መተኛት የሰውነትን አቆጣጠርን ሊያስተጓጉል ስለሚችል የልብና የደም ሥር ጤና ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያስከትል ጥናቱ አመላክቷል" ሲሉ አጥኚው ዶ/ር ዴቪድ ፕላን ገልጸዋል።
"በጣም ችግር የማስከተል ዕድል ያለው የእንቅልፍ ጊዜ ከእኩለ ሌሊት በኋላ ያለው ነው። ምክንያቱ ዘግይቶ የተኛው ሰው የጠዋት ብርሃንን የማየት እድሉን ሊቀንስ ስለሚችል የሰውነት አቆጣጠር እንደገና ይጀምራል" ሲሉም አክለዋል።
በብሪቲሽ የልብ ፋውንዴሽን ከፍተኛ የልብ ነርስ የሆኑት ራይጃና ጊብሊን "ይህ ትልቅ ጥናት እንደሚያመለክተው ከምሽቱ 4 እስከ 5 ሰዓት መተኛት ለብዙ ሰዎች ልባቸው ለረጅም ጊዜ ጤናማ እንዲሆን ምቹ ሊሆን ይችላል" ብለዋል።
"ሆኖም ይህ ጥናት መንስኤውን እና ውጤቱን ማረጋገጥ እንዳልቻለ ማስታወስ አስፈላጊ ነው። የእንቅልፍ ጊዜ እና ቆይታ ከልብ እና ደም ዝውውር በሽታዎች ጋር ስላለው ተያያዥነት ምርምሮች ያስፈልጋሉ" ሲሉ ገልጸዋል።
ነርሷ በቂ እንቅልፍ ማግኘታችን ለአጠቃላይ ጤንነታችን ብሎም ለልባችን እና ለደም ዝውውር ጤናማነት ጠቃሚ ነው። አብዛኞቹ ጎልማሶች ከሰባት እስከ ዘጠኝ ሰዓታት መተኛት ይጠበቅባቸዋል ሲሉም አስረድተዋል።
"ይህ ማለት ግን እንቅልፍ የልብ ጤና ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር የሚችል ብቸኛው ምክንያት ነው ማለት አይደልም። የደም ግፊት እና የኮሌስትሮል መጠንን ማወቅ፤ ጤናማ ክብደትን መጠበቅ እና በመደበኛነት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፤ የጨው እና አልኮል መጠጦችን በመቀነስ የአኗኗር ዘይቤን ማጤን በጣም አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም የተመጣጠነ ምግብ መመገብ የልብን ጤንነት ለመጠበቅ ይረዳል" ሲሉ ነርስ ራይጃና ጠቅሰዋል።
















