ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ የዓመቱ የበጎ ሰው ሽልማት ተሸላሚ ሆኑ

የፎቶው ባለመብት, @seleshi_b_a
በኢትዮጵያ በጎ የሰሩ እና ለሌሎች አረአያ ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎችን ለማበረታታት እና እውቅና ለመስጠት በተዘጋጀው 9ኛው የዓመቱ በጎ ሰው ሽልማት በተለያዩ ዘርፎች እውቅና እና ሽልማት ተሰጥቷል።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት ትናንት እሁድ ዕለት በተካሄደው የዘንድሮው የዓመቱ የበጎ ሰው ሽልማት 10 ኢትዮጵያዊያን ሽልማት አግኝተዋል።
ለዘንድሮው የበጎ ሰው ሽልማት በአስር ዘርፎች ከ500 በላይ ዕጩዎች ቀርበው የነበረ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 30 ሰዎች የመጨረሻ ዕጩ ዝርዝር ውስጥ መግባት ችለዋል።
በዚህም የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ መንግሥታዊ የስራ ኃላፊነትን በብቃት የመወጣት ዘርፍ የዓመቱ የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሲነሳ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱ ሰዎች መካከል አንዱ የሆኑት ዶክተር ኢንጂኒር ስለሺ በቀለ በተለይ ከሱዳንና ግብጽ ጋር የግድቡን ግንባታ እና ኦፕሬሽን በተመለከተ በሚካሄደው ከባድ እና የተራዘመ ድርድር ኢትዮጵያን ወክለው ከፊት የሚቀርቡ መሪ ናቸው።
አዲስ አበባ፣ ካርቱም፣ ካይሮ፣ ዋሽንግተን፣ ኮንጎ ኪንሻሳ፣ ኒው ዮርክ እና በሌሎችም ስፍራዎች ሲካሄዱ በቆዩት የሕዳሴ ግድብ ድርድሮች ላይ ኢትዮጵያ ወክለው የሚደራደሩ ከፍተኛ የአገሪቱ ባለሙያዎችን በመምራት ተሳትፈዋል።
ዶክተር ኢንጂኒየር ስለሺ በቀለ ላበረከቱት አስተዋጽኦም መንግስታዊ የስራ ኃላፊነትን በብቃት የመወጣት ዘርፍ የዓመቱ የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ መሆን ችለዋል።
በእውቀቱ ስዩም በዘጠነኛው የዓመቱ በጎ ሰው የኪነጥበብ ዘርፍ ተሸላሚ ሲሆን በዘርፉ በርካታ ተግባራትን በማከናወን እና የተለያዩ መፅሃፍትን ለተደራሲያን በማድረሱ ነው አሸናፊ መሆን የቻለው።
በቅርስና ባህል ዘርፍ የዓመቱ በጎ ሰው ዘርፍ ደግሞ ኢስላማዊ ቅርሶችን በመሰብሰብና በመንከባከብ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን የሚታወቀው ቢላልሉል ሐበሺ ሙዝየም አሸናፊ ሆኗል።
ከዚህ በተጨማሪም በመምህርነት ዘርፍ ዶክተር ልዑልሰገድ አለማየሁ፣ በበጎ አድራጎት ዘርፍ አቶ አማረ አስፋው፣ በሳይንስ ዘርፍ ፕሮፌሰር አለማየሁ ተፈራ፣ በማህበራዊ ጥናት ዘርፍ ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ፣ ንግድና ስራ ፈጠራ ዘርፍ አቶ በላይነህ ክንዴ፣ በሚዲያና ጋዜጠኝነት ዘርፍ ዶክተር ንጉሴ ተፈራ እና ለኢትዮጵያ ዕድገት አስተዋፅዖ ያበረከቱ ዳያስፖራዎች ዘርፍ አቶ ኤሊያስ ወንድሙ አሸናፊ ሆነዋል።
ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሃብተወልድ ደግሞ በ9ኛው የበጎ ሰው ሽልማት ልዩ ተሸላሚ ሆነው ተመርጠዋል።
በቀዳማዊ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉት ፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሃብተወልድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲቋቋም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ኢትዮጵያዊ ናቸው።












