"ስብሰባ ያልተገኘ ሚኒስትር እንደ አመጸኛ ይቆጠራል" የጊኒ ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, EPA
በጊኒ መፈንቅለ መንግሥት አካሂደው ፕሬዝዳንት አልፋ ኮንዴን ከመንበራቸው ያወረዱት ወታደሮች የአገሪቱ ሚኒስትሮችን የማይቀርበት አስቸኳይ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ጠሩ።
በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ በተነገረው የስብሰባ ጥሪ ላይ እንደተገለጸው በካቢኔ ስብሰባው ላይ ሳይገኙ የሚቀሩ ካሉ እንደ አመጸኛ እንደሚቆጠሩ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።
ከሥልጣናቸው የተነሱት ፕሬዝዳንት ኮንዴ በወታደሮቹ ቁጥጥር ስር የሚገኙ ሲሆን ቀጣይ ዕጣ ፋንታቸው ምን ሊሆን እንደሚችል ግልጽ አይደለም።
የአፍሪካ ሕብረት፣ የተባባሩት መንግሥታት እና የምዕራብ አፍሪካ አካባቢያዊ ድርጅት የሆነው ኤኮዋስ መፈንቅለ መንግሥቱን አውግዘው አገሪቱ ወደ ሲቪል አስተዳደር እንድትመለስ ጠይቀዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ "የመንግሥትን ሥልጣን በጠመንጃ ኃይል መቆጣጠርን አጥብቄ እቃወማለሁ፣ ፕሬዝዳንት አፍፋ ኮንዴም በአስቸኳይ እንዲለቀቁ እጠይቃለሁ" ሲሉ በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።
መፈንቅለ መንግሥቱን ያካሄዱት ወታደሮች የአገሪቱን ሕገ መንግሥት ያገዱ ሲሆን፤ ድንበሮቿን በመዝጋት በመላዋ ጊኒ የሰዓት እላፊ ገደብ ጥለዋል።
ወታደሮቹ እሁድ ማታ በቴሌቪዥን ባስተላለፉት መግለጫ የክልል አስተዳዳሪዎች በሙሉ በወታደራዊ አዛዦች መተካታቸውንና ከሥልጣን የተነሱት የ83 ዓመቱ ፕሬዝዳንት በደህና ሁኔታ በቁጥጥር ስር መሆናቸውን አመልክቷል።
የጊኒ ልዩ ኃይሎች አዛዥ የሆኑት ኮሎኔል ማማዲ ዱምቡያ መፈንቅለ መንግሥቱን ተከትሎ እንደተናገሩት ሠራዊቱ እርምጃውን የወሰደው በአገሪቱ ስር የሰደደውን ሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግር ለማብቃት ነው ብለዋል።
ፕሬዝዳንት አልፋ ኮንዴ በዚህ ዓመት ጥቅምት ወር ላይ በተካሄደውና አወዛጋቢ በነበረው ምርጫ ለሦስተኛ የሥልጣን ዘመን ተመርጠው ነበር። ።
በተቃዋሚነት ለረጅም ዘመናት የቆዩት ኮንዴ ለመጀመሪያ ጊዜ በአገሪቱ በተካሄደ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማሸነፍ ከአስር ዓመት በፊት ነበር ወደ ሥልጣን የመጡት።
ፕሬዝዳንት ኮንዴ በመሪነት በቆዩባቸው ዓመታት ውስጥ አንዳንድ ምጣኔ ሀብታዊ መሻሻሎች በአገሪቱ የታዩ ሲሆን ተቺዎቻቸው ላይ በሚደርሱ ጥቃቶችና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሲከሰሱ ቆይተዋል።
በተፈጥሮ ሀብቷ ባለፀጋ እንደሆነች የሚነገርላት የምዕራብ አፍሪካዋ አገር ጊኒ ለዓመታት ባጋጠማት አለመረጋጋትና የመልካም አስተዳደር ችግር ምክንያት በዓለም ላይ ካሉ ደሃ አገራት መካከል ትገኛለች።













