የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን በጥፊ ተመቱ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን በደቡባዊ ምሥራቅ ፈረንሳይ ጉብኝት እያደረጉ ሳለ በጥፊ ተመቱ።
ፕሬዝደንት ማክሮን ከቫለንስ ከተማ ወጣ ብሎ ወደሚገኝ የጋራ መኖሪያ እያቀኑ ሳለ በጥፊ ሲመቱ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተለቋል።
አረንጓዴ ካናቴራ ያደረገ ግለሰብ ነበር ማክሮንን በጥፊ የመታቸው። ጠባቂዎቻቸው ወዲያውኑ ከለላ ሰጥተዋቸዋል።
ክስተቱን ተከትሎ ሁለት ሰዎች በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ የፈረንሳይ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
በጥፊ የተማታው ግለሰብ "ማክሮኒዝም ይውደቅ" እያለ ነው ማክሮንን በጥፊ የመታቸው።
ማክሮን በጥፊ ከተመቱ በኋላ በድጋሚ ወደ ስፍራው ተመልሰው ከማኅበረሰቡ ጋር ሲነጋገሩ በተንቀሳቃሽ ምስሉ ታይቷል።
ማክሮንን በጥፊ የመታው ግለሰብ ማን እንደሆነና ምክንያቱም ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም።
የኤኤፍፒ ዘገባ እንደሚያሳየው፤ ይህ ግለሰብና አንድ ሌላ ነዋሪ በፖሊስ ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል።
ፖሊሶች ከክስተቱ በኋላ በቫለንስ ከተማ በስፋት መታየታቸውን አንድ ጋዜጠኛ ትዊት አድርጓል።
ፖለቲከኞች በበኩላቸው ድርጊቱን አውግዘዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ጄን ካስቴክስ፤ ዴሞክራሲ ማለት ክርክር እንዲሁም ጨዋነት የተሞላው አለመግባባት መሆኑን ገልጸው "ክፉ መናገር ወይም ኃይል መጠቀም ግን መቼም ቢሆን ተገቢ አይደለም" ብለዋል።
ግራ ዘመሙ መሪ ዣንሉክ ሜልንኮሀን በበኩላቸው "ከፕሬዘዳንቱ ጎን ነኝ" ብለዋል።
ቀኝ ዘመሙ መሪ ማሪን ለፔን "ዴሞክራሲ ክርክርን ያስተናግዳል። ለድብድብ ግን ቦታ የለውም" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ማክሮን በመላው ፈረንሳይ ጉብኝት እያደረጉ ነው። ከዚህ ቀደም በዛው አካባቢ አንድ ትምህርት ቤት ጎብኝተዋል።
ፈረንሳይ ባርና ሬስቶራንቶች ከሰባት ወር በኋላ እንዲከፈቱ ውሳኔ ለማሳለፍ በተዘጋጀችበት ወቅት ነው ፕሬዝደንቱ ጉብኝት የጀመሩት።
የሰዓት እላፊ ከምሽቱ 3፡00 ወደ 5፡00 ይሸጋሸጋል ተብሎም ይጠበቃል።
ማክሮን ትምህርት ቤቱን ከጎበኙ በኋላ "ነገ አዲስ እርምጃ ይወሰዳል። በሁሉም ግዛት ሕይወት ወደ ቀደመ ገጽታው ይመለሳል" ሲሉ ትዊት አድርገዋል።












