በኤፍቢአይ መተግበሪያ አማካይነት ከ800 በላይ የወንጀል ተጠርጣሪዎች ተያዙ

ከ200 በላይ ተጠርጣሪዎች በአውስትራሊያ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Australian Federal Police

የምስሉ መግለጫ, ከ200 በላይ ተጠርጣሪዎች በአውስትራሊያ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

በመላው ዓለም ይንቀሳቀሱ የነበሩ ከ800 በላይ የሚሆኑ የወንጀል ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ።

የአሜሪካው የምርመራ ድርጅት ኤፍቢአይ የጽሁፍ መልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያ ሠርቶ ተጠርጣሪዎቹ እንዲጠቀሙበት ካደረገ በኋላ ነው የተያዙት።

ይህ ኦፕሬሽን የተመራው በአውስትራሊያ እና በኤፍቢአይ ነው። ኤኤንኦኤም (ANOM) የተባለ መተግበሪያን ተጠርጣሪዎቹ እንዲጠቀሙ ከተደረገ በኋላ ፖሊስ ሊከታተላቸው ችሏል።

መተግበሪያው ላይ ከሚለዋወጡት መልዕክት በመነሳት ስለ አደንዛዥ እፅ ዝውውር፣ ስለ ግድያ ሴራ እና ሕገ ወጥ ገንዘብን ሕጋዊ የማስመሰል ሂደት ማወቅ ተችሏል።

ክትትል እየተደረገ የነበረው በአደንዛዥ እፅ አዘዋዋሪዎችና በማፊያ ቡድኖች ነው።

ከአሥር በላይ በሚሆኑ አገሮች በተካሄደው ኦፕሬሽን አደንዛዥ እፅ፣ መሣሪያዎች፣ ቅንጡ መኪኖች እና ገንዘብ ተይዟል።

የተያዙት ስምንት ቶን ኮኬይን፣ 250 መሣሪያዎች፣ ከ48 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንዲሁም ክሪፕቶከረንሲን ጨምሮ የተለያዩ አገራት የገንዘብ ምንዛሬዎች ናቸው።

የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚንስትር ስኮት ሞሪሰን "ኦፕሬሽኑ የተደራጀ ወንጀልን አሽመድምዷል" ብለዋል።

የአውሮፓ ሕብረት የፖሊሲ ኤጀንሲ (ዩሮፖል) ትሮጃን ሺልድ የተባለውን ኦፕሬሽን "ሚሥጥራዊ ግንኙነትን በማጋለጥ ረገድ በጣም ትልቁ ሕግ የማስከበር ዘመቻ" ሲል ገልጾታል።

መተግበሪያው እንዴት ጥቅም ላይ ዋለ?

ኤፍቢአይ በሚሥጥራዊ መንገድ ኤኤንኦኤም የተባለው መተግበሪያ በወንጀለኞች ሰንሰለት ውስጥ ጥቅም ላይ እንዲውል አድርጓል።

ከዚህ በፊት ወንጀለኞች በሚሥጥር መልዕክት ለመለዋወጥ (ኢንክሪፕትድ) ይጠቀሙባቸው የነበሩ ሁለት መተግበሪያዎች በሕግ አስከባሪዎች ከተዘጉ በኋላ ነበር የኤፍቢአይ መተግበሪያ የተሰራጨው።

መተግበሪያውን ቀንደኛ ወንጀለኞች እየተጠቀሙበት እንደሆነ መረጃ ሲሰራጭ ሌሎች ወንጀለኞችም መተግበሪያው ላይ እምነት አሳድረው ይገለገሉበት ጀመሩ።

የአውስትራሊያ ፖሊስ እንዳለው፤ አንድ ወንጀለኛ እንደዚህ አይነት መተግበሪያዎችን የሚያገኘው ከሌላ ወንጀለኛ ነው።

በአደንዛዥ እፅ ዝውውር የሚጠረጠር አውስትራሊያው የሕግ ስደተኛ ሀካን አይክ ከፖሊስ ትዕዛዝ ተቀብሎ መተግበሪያውን ለወንጀለኞች አስተላልፏል።

"የፌስቡኩ ወሮበላ" በሚል ስም የሚታወቀው ሀካን እስርን ሸሽቶ ቱርክ ውስጥ በስደት ይኖራል።

ኤፍቢአይን መተባበሩ አደጋ ውስጥ ሊከተው ስለሚችል በፍቃደኝነት እጁን መስጠቱ እንደማይቀርም ተገልጿል።

በ100 አገሮች በሚገኙ 300 የወንጀል ቡድኖች 12,000 ሚሥጥራዊ መሣሪያዎች ጥቅም ላይ ውለዋል።

በክትትሉ ወቅት ምን ተገኘ?

ክትትል በተካሄደበት ወቅት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የወንጀል ሴራን የሚገልጹ የጽሁፍ መልዕክቶች ተገኝተዋል።

የአውስትራሊያ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር "የሚያወሩት ስለ አደገኛ እፅ፣ ስለሚገደሉ ንጹሀን ሰዎችና ሌሎችም ወንጀሎች ነው" ብለዋል።

በመላው ዓለም በዚህ ኦፕሬሸን የተሳተፉት ፖሊሶች ወደ 9,000 ይጠጋሉ።

የኤፍቢአይ የወንጀል ምርመራ ክፍል ባልደረባ ካልቨን ሺቨርስ "በተገኘው መረጃ አማካይነት ብዙ ግድያ እና ወንጀል ማስቆም ተችሏል" ብለዋል።

ለዝውውር የተዘጋጁ ከፍተኛ መጠን ያላቸው ኮኬኖችን ፎቶ ያገኙም ነበር።

እስካሁን በቁጥጥር ሥር የዋሉት እነማን እንደሆኑ በይፋ አልተገለጸም።

አውስትራሊያ ውስጥ በሞተርሳይክል የሚንቀሳቀሱ የወንጀል ቡድን አባላት እና ማፊያዎችን ጨምሮ 224 ተጠርጣሪዎች ተይዘዋል።

3 ቶን አደንዛዥ እፅ፣ 35 ሚሊዮን ዶላር፣ 20 የግድያ ዛቻዎችም ተደርሶባቸዋል።

የኒው ዚላንድ ፖሊስ 35 ተጠርጣሪዎችን እንዲሁም 2.7 ሚሊዮን ዶላር ይዟል። ስዊድን ውስጥ 70 ተጠርጣሪዎች፣ ኔዘርላንድስ ውስጥ 49 ተጠርጣሪዎች መያዛቸው ተዘግቧል።

የዩሮፓል ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዤንፊሊፔ ሎኮፍ ኦፕሬሽኑን "ድንቅ ስኬት የታየበት" ብለውታል።