በመላው ዓለም ተቋርጠው የነበሩ ድረ ገጾች መሥራት ጀመሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በመላው ዓለም የሚገኙ የግዙፍ ኩባንያዎች ድረ ገጾች ተቋርጠው ከቆዩ በኋላ ወደ ሥራ ተመለሱ።
ድረ ገጾቹ ለአንድ ሰዓት ያህል ተቋርጠው ቆይተዋል።
ዛሬ ማክሰኞ እኩለ ቀን አከባቢ ተቋርጠው ከነበሩ ድረ ገጾች መካከል የአማዞን፣ ሬዲ፣ ትዊች እና የዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ይገኙበታል።
gov.uk በሚል የሚጨርሱ የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ድረ ገጾችም ተቋርጠው ነበር።
እንደ ሲኤንኤን፣ ፋይናንሻል ታይምስ እና ዘ ጋርዲያን ያሉ መገናኛ ብዙሃን ድረ ገጾች ጭምር መሥራት አቁመው ነበር።
የአገልግሎት መቋረጥ ያጋጠማቸው ድረ ገጾች "Error 503 Service Unavailable" የሚል መልዕክት ያሳዩ ነበር።
ለችግሩ መፈጠር ምክንያቱ ደግሞ ፋስትሊ የተሰኘ የኢንተርኔት አገልግሎት አቅራቢው ድርጅት ነው ተብሏል።
ተቋርጠው የቆዩ ድረ ገጾች ወደ አገልግሎት መግባት የጀመሩ ሲሆን ለችግሩ መፈጠር ምክንያት ነው የተባለው ፋስትሊ ማስተካከያዎችን እያከናወንኩ ነው ብሏል።
ፋስትሊ የተሰኘው ኩባንያ ድረ ገጾችን ከጥቃቶች የመከላከል አግልግሎት በመስጠት እንዲሁም በድረ ገጾች ላይ የጎብኚዎች ቁጥር ሲበዛ የድረ ገጹ ፍጥነት እንዳይቀንስ በመሥራት ይታወቃል።
የአንድ ኩባንያ ችግር የበርካታ ድረ ገጾች አገልግሎት እንዲቋረጥ ማድረጉ መነጋገሪያ ሆኗል።
ኢሴት በተሰኘ ኩባንያ ውስጥ የሳይበር ደህንነት ባለሙያ የሆኑት ጄክ ሞር፤ በርካታ መሠረት ልማት ፈሰስ የተደረገባቸው ድረ ገጾች በአንድ ኩባንያ እጅ ላይ እንዲወድቁ ማድረግ አግባብ አይደለም ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።












