ኮሮናቫይረስ፡ ኢትዯጵያ በኮቪድ-19 መከላከል ባለፉት ስድስት ወራትና ወደፊት የሚጠብቋት ሥራዎች

የኢትዯጵያ ባንዲራና የኮሮናቫይረስ ስርጭትን የሚያሳይ ግራፊክስ

የፎቶው ባለመብት, mirsad sarajlic

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው በኮቪድ-19 የተያዘ ግለሰብ የተገኘው መጋቢት 4/2012 ነበር። ይህም እነሆ ዛሬ ስድስት ወራትን ደፈነ።

ከዚያ ጊዜ ወዲህ የወረርሽኙ መጠን እየጨመረ መጥቶ በአሁኑ ሰዓት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ60 ሺህ አልፏል።

በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 60 ሺህ 784 ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ 22 ሺህ 977 ሲያገግሙ፣ 949 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው እንዳለፈ በትናንትናው ዕለት የጤና ሚኒስቴርና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያወጡት ሪፖርት አመልክቷል።

በኢትዮጵያ፣ ወረርሽኙ በመጋቢት ወር ከተከሰተ በኋላ፣ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በባለፉት ሳምንታት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት አስታውቋል።

ካለፈው ወር ወዲህም ኢትዮጵያ በቀን 20 ሺህ ያህል ናሙናዎች ላይ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ማድረግ ጀምራለች። ይህም በአጠቃላይ በአገሪቱ የተደረጉ የኮሮናቫይረስ ምርመራዎችን ከአንድ ሚሊየን በላይ እንዲሆን አድርጎታል።

በአገሪቱ የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር ተብሎ ተደንግጎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ነሐሴ 30 ላይ አብቅቷል።

የተወሰዱ እርምጃዎችና የተገኙ ውጤቶች

በአዲስ አበባ የኮሮናቫይረስ የተያዙ እና ሕክምና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ተቀብለው ከሚያስተናግዱ የሕክምና ተቋማት መካከል ኤካ ኮተቤ እና ሚሌኒየም አዳራሽ ተጠቃሽ ናቸው።

ወደ እነዚህ የሕክምና ማዕከላት የሚገቡ ህሙማን ቁጥር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየጨመሩ መሆኑን ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሁለቱም ተቋማት ኃላፊዎች ገልፀዋል።

ኤካ ሆስፒታል 500 ለኮሮናቫይረስ ህሙማን የተዘጋጁ አልጋዎች ሲኖሩት፣ ከእነዚህ መካከል 20ዎቹ ለጽኑ ህሙማን የተለዩ መሆናቸውን የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ናትናኤል በኩረ ጽዮን ይናገራሉ።

ተቋሙ በኮሮናቫይረስ በጽኑ ታምመው የሚመጡትን ኮተቤ በሚገኘው ሆስፒታል ተቀብሎ የሚያስተናግድ ሲሆን፤ ቀለል ያለ ምልክት ያላቸውና ራሳቸውን ማግለል ለሚፈልጉ ደግሞ ገርጂ በሚገኘው የስፖርት አካዳሚ 200 አልጋዎች እንደተዘጋጁ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በአገሪቱ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ህሙማን ተቀብሎ የሚያስተናግደው የሚሌኒየም አዳራሽ ከ800 በላይ አልጋዎች እንዳሉት መረጃዎች ያሳያሉ።

ዶ/ር ናትናኤል ባለፉት ሁለት ወራት ወደ ሆስፒታላቸው ከሚመጡ የኮቪድ-19 ህሙማን መካከል በጽኑ ታመው የሚመጡ ግለሰቦች ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ የክፍሉን አልጋዎች እና የቬንቲሌተሮች ቁጥር ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በቀጣዮቹ ሳምንታትም በርካታ የቬንትሌተር ድጋፍ የሚፈልጉ ህሙማን እንደሚመጡ ያላቸውን ስጋት ይገልጻሉ።

መስመር

አቶ ኃይሌ ውብነህ እንዲሁም ዶ/ር አበባየሁ ንጉሴ የኀብረተሰብ ጤና ባለሙያ ናቸው።

ለሁለቱም ባለሙያዎች ኢትዮጵያ የመጀመሪያው በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች በተገኙበት ወቅት ያደረገችው ዝግጅትም ሆነ የሕብረተሰቡ ጥንቃቄ "እጅግ በጣም ከፍተኛ ነበር።"

አቶ ኃይሌ የኮሮናቫይረሰ ስርጭትን ለመግታት በዋና ከተማዋ አዲስ አበባም ሆነ በክልል ከተሞች የተለያዩ እርምጃዎች በፍጥነት መወሰዳቸውን ያስታውሳሉ።

በእርግጥ ይላሉ አቶ ኃይሌ፣ በከተማም በገጠርም ትምህርት ቤቶች እኩል መዘጋታቸው "ስህተት ቢኖረውም" በሽታውን ለመቆጣጠር አመርቂ ሥራ ተሰርቷል።

እንደ አቶ ኃይሌ ከሆነ ትምህርት ቤቶችን በአንዴ ዘግቶ ሁሉንም ህጻናት ከትምህርት ውጪ ከማድረግ ቀስ በቀስ ከተሞች አካባቢ እርምጃዎች እየተወሰዱ ወደ ገጠሩ አካባቢ ማስፋት ይቻል ነበር።

የፋሲካ ሰሞን የነበረው የበዓል ግርግር

እንደ አቶ ኃይሌ ከሆነ በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭት መስፋፋት የጀመረው የፋሲካ ሰሞን ከነበረው የበዓል ገበያ እና እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ ነው።

ዶ/ር አበባየሁ በበኩላቸው ቁጥሮችም የሚያሳዩን ይህንኑ ነው በማለት "በርግጥ በትክክል በዚያ ሰሞን የነበረው ለስርጭቱ መስፋፋት አስተዋጽኦ ማድረጉን ለመናገር ጥናት ቢጠይቅም" በማለት፣ ስብሰባዎች እንደልብ መደረጋቸው፣ የበዓል ሰሞን ባሉ እንቅስቃሴዎች ላይ የታዩ መዘናጋቶች ለስርጭቱ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ጠቅሰዋል።

የፋሲካ በዓል ካለፈ በኋላ በቫይረሱ ስርጭት የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ እንደመጣም ያስታውሳሉ። በተቃራኒው ደግሞ ሕብረተሰቡ የሚያደርገው ጥንቃቄ ላይ መላላት መታየቱን በማንሳት ለቫይረሱ መስፋፋት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ገልፀዋል።

ከዚህ በኋላ ሕብረተሰቡ የሚሰባሰብባቸው የተለያዩ አጋጣሚዎች መፈጠራቸውን በመግለጽ፣ ስብሰባዎች በቂ አየር በማይዘዋወርባቸው ስፍራዎች መካሄዳቸው፣ ሰልፎች መደረጋቸው እንዲሁም በዓላት መደራረባቸው ለስርጭቱ መስፋፋት ዋነኛ ምክንያት መሆናቸውን ይጠቅሳሉ።

ለአቶ ኃይሌ ኢትዮጵያ የምታደርገው የኮሮናቫይረስ ምርመራ መጠንን በከፍተኛ ቁጥር ብታሳድግ፤በቫይረሱ መያዛቸው የሚረጋገጥ ሰዎች ቁጥር ከፍ እንደሚል ጥርጥር የላቸውም።

ኢትዮጵያ እየመረመረች ያለችው ንክኪ ያላቸው፣ የተጠረጠሩ እንዲሁም ምልክት የታየባቸው እንደሚሆኑ በማንሳት ሰፊውን ሕዝብ ለመመርመር ቢሞከር አቅምን እንደሚፈትን ተናግረዋል።

ለዶ/ር አበባየሁ የምርመራ አቅምን ማሳደግ ጥሩ ቢሆንም፣ የሚመረመሩ ሰዎች በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎችን በመለየት በኩል ጉልህ አስተዋጾኦ እንዳለው ይናገራሉ።

ልክ አቶ ኃይሌ እንዳሉት ንክኪ ያላቸውንና ምልክት ያሳዩትን ብቻ መመርመር፣ እንዲሁም በጎ ፈቃደኞችን አልያም አጠቃላይ ማኅበረሰቡን መመርመር በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎችን ማግኘት ላይ ለውጥ ያመጣል ሲሉም ገልፀዋል።

የኢትዯጵያ ባንዲራና የኮሮናቫይረስ ስርጭትን የሚያሳይ ግራፊክስ

የፎቶው ባለመብት, Anton Litvintsev

የቫይረሱ ስርጭ የት ነው የጎላው?

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ያወጣው መግለጫ እንደሚያሳየው በከተማዋ በነሐሴ ወር በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች፣ ከሐምሌ ወር ጋር ሲነፃፀር በ9,384 ወይም 99.6 በመቶ ከፍ ብሏል።

በአዲስ አበባ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ የተከሰተው የሞት መጠንም በሐምሌ ወር 191 የነበረ ሲሆን፤ በነሐሴ ወር ደግሞ 446 ሰዎች በኮቪድ-19 ምክንያት ህይወታቸው አጥተዋል።

ከዚህም ከሁለት እጥፍ በላይ የነሐሴ ወር የሞት መጠን ጭማሪ ማሳየቱን መረዳት ይቻላል።

በአዲስ አበባ ከሽታው ጋር በተያያዘ በነሐሴ ወር ብቻ የነበረው የሞት ምጣኔ ባለፉት 5 ወራት ከሞቱት በሦስት ሳምንት ውስጥ ብቻ በእጥፍ ማደጉን መገንዘብ ይቻላል።

አቶ ኃይሌ አዲስ አበባ የቫይረሱ ስርጭት በስፋት የተከማቸባት ከተማ ብትሆንም፣ የተሰሩት ሥራዎችም ስርጭቱን ለመግታት የሚያስችሉ መሆናቸው ላይ ጥርጣሬ አላቸው።

የተለያዩ ክፍለ ከተሞች ያለው የቫይረሱ የስርጭት መጠን እንደሚለያይ በመጥቀስም፣ እንደ ልዩነቱ የሚሰራው ሥራና ትኩረት የሚደረግበት አካባቢ መለያየት እንደነበረበት ይገልጻሉ።

ነገር ግን ይላሉ አቶ ኃይሌ፤ የመከላከል ሥራው እየተሰራ ቢሆንም እንኳ "አይታይም።"

ዶ/ር አበባየሁ በአዲስ አበባም ሆነ በክልሎች የመከላከል አቅሙ የተሻለ የነበረው የተወሰነ ጊዜ እንደነበር በመጥቀስ አሁን የሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች አቅም "ወርዷል" ሲሉ ይናገራሉ።

በአዲስ አበባና በክልሎች መካከል ግን ያለው የነዋሪዎች ጥግግት መጠን እንደሚለያይ በመግለጽ፣ በአዲስ አበባ የስርጭቱ መብዛት ከዚህ ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ይገልጻሉ።

በአዲስ አበባ ያለው እንቅስቃሴ የትራንስፖርት አገልግሎት መጠቀም የሚያስገድድ መሆን፣ የእንቀስቃሴ ፍሰት ፈጣን መሆን የራሳቸው አስተዋጽኦ እንዳላቸውም አብራርተዋል።

የኤካ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ናትናኤል ወደ ሆስፒታል በጽኑ ታምመው የሚመጡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረው ለዚህ ምክንያቱ ያሉትን ሲጠቅሱ "ቸልተኝነት አንዱ ነው።"

በሕብረተሰቡ ዘንድ በሽታውን የመናቅ፣ ይያዘኝና ይለይልኝ የሚል ቸልተኝነት እንደሚስተዋል የሚጠቅሱት አቶ ኃይሌ "ይህ አደገኛ ውሳኔ ነው፣ ከሞቱ በኋላ መመለስ የለም፤ የሙከራ ሞት የሚባል ነገር የለም" ይላሉ።

አሁን በርካታ ከንክኪ ነጻ የሆኑ ሰዎች ቫይረሱ ያልደረሰባቸው አካባቢዎች በመኖራቸው የመከላከል ሥራውን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አቶ ኃይሌ ጨምረው ተናግረዋል።

የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል እንቅስቃሴ ገደብ መጣል ፈታኝ በመሆኑ ዘዴዎችን መቀያየር፣ ከተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር ያገናዘበ የመከላከል እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ መሆኑንም ይመክራሉ።

ክልሎች አካባቢ ያለው የቫይረሱ ስርጭት አነስተኛ መሆኑን የሚገልፁት አቶ ኃይሌ፤ ይህ ከክልሎችና ከባለሙያ አቅም ጋር አንደሚያያዝ ይገልፃሉ።

ክልሎች ማድረግ የሚችሉትን እያደረጉ ነው ያሉት አቶ ኃይሌ፤ በሽታው ወደ ክልሎች እንደሚዛመት በመግለጽ፤ የመመርመር አቅም እስካላደገ ድረስ ትክክለኛ የስርጭቱን መጠን ማወቅ እንደማይቻልም ይናገራሉ።

የአዲስ ዓመት ልዩ ጥንቅር

ወደፊት ምን ይደረግ?

በአሁኑ ጊዜ በርካታ ሕዝባዊ በዓላት እየመጡ ነው። አዲስ ዓመት ከቀናት በኋላ ይከበራል። የትግራይ ምርጫ ዛሬ እየተካሄደ ነው። እሬቻ እንዲሁም መስቀልን የመሳሰሉ የአደባባይ በዓላትም መኖራቸው ለቫይረሱ ስርጭት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ከዚህ ሁሉ ደግሞ ተማሪዎች የ2013 ትምህርታቸውን ለመጀመር ምዝገባ ማድረጋቸው ለአቶ ኃይሌ ስጋት ፈጥሮባቸዋል።

ሁለቱም ባለሙያዎች ሕዝባዊ በዓላት ከአሸንዳ አከባበር ትምህርት በመውሰድ በውስን ሰው ቢደረጉ መልካም መሆኑን ይመክራሉ።

እንደ አቶ ኃይሌ የቫይረሱ ስርጭት በሚጨምርበት ወቅት ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎችን መግታት፣ ትምህርት ቤቶችን መዝጋት፣ ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ማገድ እንደሚያስፈልግ ገልፀው፤ በዚህ ወቅት ትምህርት ቤት መክፈት ወደ ባሰ ማጥ ውስጥ እንደሚከት ገልፀዋል።

ዶ/ር አበባየሁ የኮሮናቫይረስን መከላከልን የሚመሩ ሰዎች በአዲስ ዓመት ያሉ በዓላትን ከግንዛቤ በማስገባት የመከላከል ሥራውን ከዚያ አንጻር መቃኘት እንደሚያስፈልጋቸው ይመክራሉ።

የበሽታው ስርጭት አሁን እየጨመረ መሆኑን በማንሳትም፣ በዚህ ወቅት ትምህርት ቤቶችን መክፈት የበለጠ አደጋ መጋበዝ መሆኑን አቶ ኃይሌ ቢገልፁም ዶ/ር አበባየሁ ግን በዚህ አይስማሙም።

አቶ ኃይሌ ትምህርት ቤቶች የሚከፈትበት ጊዜ ቢዘገይ እንዲሁም እንደ አካባቢውና ሁኔታዎች በሚፈቅዱት መንገድ ቢሆን ሲሉ ይመክራሉ።

ዶ/ር አበባየሁ ደግሞ ትምህርት ሲከፈት ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በማንሳት፣ በአንድ ክፍል የሚማሩ ተማሪዎችን ቁጥር መቀነስ፣ ንጽህና አጠባበቅን፣ እንዲሁም የክፍሎቹን የአየር ዝውውር አስቀድሞ ማዘጋጀት ያስፈልጋል ይላሉ።

ተማሪዎች አፍና አፍንጫ መሸፈኛ የሚጠቀሙበትን ሁኔታም ታሳቢ ማድረግ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ወሳኝ መሆኑን በማንሳት አስቀድሞ እነዚህን ሁሉ መስራት እንዳሚያስፈልግ ይናገራሉ።

ሁለቱ ባለሙያዎች በርግጥ ህጻናትና ወጣቶች በቫይረሱ የመያዝ እድላቸው ላይ ተጨባጭ የሆነ ጥናት ባይኖርም ቫይረሱን ወደ ቤተሰቦቻቸው ማዛመታቸው ግን አይቀርም ሲሉ ገልፀዋል።

የኮሮናቫይረስ ስርጭት በአንድ ወቅት ተከስቶ የሚጠፋ ባለመሆኑ ትምህርት አሰጣጡ ቀጣይ እና አሰልቺ ባልሆነ መልኩ መካሄድ እንዳለበትም ይመክራሉ።

በአሁኑ ወቅት "ምክንያት አልሆንም" የሚው ዘመቻ መካሄዱ መልካም መሆኑን የሚያነሱት ዶ/ር አበባየሁ፤ ምን ያህል ታች ድረስ ዘልቋል የሚለው ላይ ግን ጥያቄ አላቸው።

የኢትዮጵያውያን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አጠቃቀም በጣም አነስተኛ መሆኑን የሚናገሩት ዶ/ር አበባየሁ ይህንን ወደ 90 በመቶ ከፍ ማድረግ ቢቻል የቫይረሱን ስርጭት " በ40 እና በ50 በመቶ መቀነስ ይቻላል" ሲሉ ይመክራሉ።