ኮሮናቫይረስ፡ 350 ህሙማንን ከኮቪድ-19 ፈወስኩ የምትለው አወዛጋቢዋ ዶክተር

የፎቶው ባለመብት, @STELLA_IMMANUEL
ዶክተር ስቴላ ኢማኑኤል 350 ያህል የኮሮናቫይረስ ህሙማንን በአወዛጋቢው የወባ መድኃኒት አማካይነት መፈወሷን በባለሙያዎች ፊት ስትናገር የሚያሳው ቪዲዮ ይፋ በተደረገ በአጭር ጊዜ ውስጥ በወረርሽኙ በተጨነቀው በሚሊዮን በሚቆጠር የዓለም ሕዝብ ታይቷል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕም ስለዚህ መድኃኒት ፈዋሽነት ደጋግመው ቢናገሩም ከህክምና ባለሙያዎች ዘንድ የሚሰማቸው ካለማግኘታቸው በተጨማሪ ለትችት ተዳርገው ቆይተዋል።
አሁን የእሳቸውን አቋም የምትጋራ ዶክተር በይፋ ወጥታ ስለመድኃኒቱ ስትናገር እጅጉን ነው የተደሰቱት። ስለዚህም ዶክተር ስቴላ ኢማኑኤል በትራምፕ ተወድሳለች።
ያለምክንያት አይደለም። ዶናልድ ትራምፕ እጅግ አድርገው ስለ ፈዋሽነቱ የሚሰብኩለትን ለአፍ ጥሪ እንኳ የማይመች ሀይድሮክሲክሎሮኪይን የሚባል መድኃኒትን እርሷም 'ፈዋሽ ነው' ስላለች ነው።
ሀይድሮክሲክሎሮኪይን ወትሮ ለወባ በሽተኞች የሚሰጥ መድኃኒት ነው።
ዶናልድ ትራምፕ ግን ለኮሮናቫይረስም ይሆናል ይላሉ። ትናንትና እንዲያውም "በዚህ መድኃኒት ዙርያ ጥልቅ ንባብ አድርጊያለሁ፤ ፈዋሽነቱ አሌ አይባልም፤ እመኑኝ፤ መቼም እኔ ያልኩትን ነገር ማጣጣል ትወዳላቸሁ" ለጋዜጠኞች ሲሉ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዚህች ካሜሮናዊት ሐኪም የተዘመረለትን የዚህን የወባ መድኃኒት የኮሮናቫይረስ ፈዋሽነት የሚመሰክረውን የዶ/ር ስቴላን ቪዲዮ ዶናልድ ትራምፕ ስላጋሩት እነፌስቡክና ትዊተር ቶሎ ብለው ከገጻቸው አንስተውታል። ምክንያቱ ደግሞ ሐሰተኛ መረጃን ይዟል፣ ሰውን ያሳስታል በሚል ነው።
ቪዲዮውን ፌስቡክ ከገጹ ከማንሳቱ በፊት የትራምፕ የበኩር ልጅም ለዓለም አጋርቶት ሚሊዮኖች ተመልከተውታል። ከዚህ በኋላ ነው ዶ/ር ሴቴላ ዝነኛ የሆነችው።
ዶ/ር ስቴላ ኢማኑኤል ማን ናት?
ዶ/ር ስቴላ የተወለደችው ካሜሮን ውስጥ ነው። አሁን የምትኖረው በበአሜሪካዋ ሂዩስተን ቴክሳስ ነው።
ዶናልድ ትራምፕ ስለ ዶ/ር ስቴላ ሲናገሩ፣ "እጹብ ድንቅ የሆነች ሐኪም ናት" ብለዋል።
"በመቶዎች የሚቆጠሩ በሽተኞችን መፈወሷን ተናግራለች፤ የእርሷ ንግግር እውነት ነው፤ እኔ ግን በግል አላውቃትም" ብለዋል ትራምፕ።
ዶ/ር ስቴላ ኢማኑኤል ሐኪም ብቻ ሳትሆን የፕሮቴስታንት ፓስተርም ናት። ባለፈው ሰኞ በአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በር ላይ በሚገኘው ደረጃ ላይ ቆማ ሰው በተሰበሰበበት ስብከት ስታደርግ ነበር። ያ ቪዲዮ ነጭ አክራሪዎች በሚያስተዳድሩት አንድ ድረ ገጽ ላይ ታትሟል።
በዚህ ስብክቷ ዶ/ር ስቴላ አሜሪካዊያን ፈውስ የሚያገኙበትን መድኃኒት ተከልክለዋል ስትል ይህን የወባ መድኃኒት ታሞካሽ ነበር።
"ማንም ሰው ከኮቪድ-19 መፈወስ ይችላል። ይህ ቫይረስ መድኃኒት አለው። መድኃኒቱም ሀይድሮክሲክሎሮኪይን ይባላል። እኔ ብቻ 350 ሰዎችን ፈውሼበታለሁ። አንድም ሰው አልሞተብኝም" ብላለች ዶ/ር ስቴላ።
ይህ ምስክርነት ለዶናልድ ትራምፕ ሠርግና ምላሽ ሆኖላቸዋል።
ዶናልድ ትራምፕ ሀይድሮክሲክሎሮኪይን ፈዋሽ ስለመሆኑና እርሳቸውም ለሁለት ሳምንት ያህል እንደወሰዱት በተደጋጋሚ ሲናገሩ ቆይተዋል።
ያም ሆኖ የዓለም ጤና ድርጅትም ሆነ የእራሳቸው መንግሥት የጤና አማካሪዎች መድኃኒቱ ለኮቪድ ፈዋሽነቱ ምንም ማረጋገጫ አልተገኘም ይላሉ። እንዲያውም ለከፍተኛ የልብ ሕመም ስለሚያጋልጥ ጥንቃቄ ይደረግ ነው የሚሉት።
ዶ/ር ስቴላ ግን ይህ መድኃኒት ምንም የጎንዮሽ ጣጣ አያመጣም፤ "በአገሬ ካሜሮን ብዙ ሰው ወባ ሲታመም ይወስደው የለም እንዴ?" ትላለች።

የፎቶው ባለመብት, DR STELLA IMMANUEL/TWITTER
ሰባኪዋ ዶክተር
እንደ አውሮፓዊያኑ በ1965 በካሜሮን የተወለደችው ዶ/ር ስቴላ ኢማኑኤል ሕክምና ያጠናቸው በናይጄሪያ ካላባር ዩኒቨርስቲ ነው። የቴክሳስ የህክምና ቦርድ እንዳረጋገጠው ዶ/ር ስቴላ የህክምና ፍቃድ አላት።
ከህክምናው ጎን ለጎን ዶ/ር ስቴላ ፓስተር ናት። በሂዩስተን ፋየር ፓወር ሚኒስትሪ ቤተ ክርስቲያንን አቋቁማለች።
ስብከቶቿ በዩትዩብ ላይ በብዛት ይገኛሉ።
ከአምስት ዓመት በፊት በስብከቶቿ መካከል ትናገራቸው የነበሩ ነገሮች ግን የሐኪም አይመስሉም። አስደንጋጭም ናቸው።
ለምሳሌ በአንድ ቪዲዮዋ ላይ "ሳይንቲስቶች ከመናፍስት ዲኤንኤ ናሙና ወስደው አዲስ ክትባት እየቀመሙ ነው። የክትባቱ ዋንኛ ዓላማ ታዲያ ሰዎች ሐይማኖት እንዳይኖራቸው የሚያደርግ ነው" ብላለች
መናፍስትና ሰይጣኖችን በምድር ላይ እየተከሰተ ላለው ምሰቅልቅል ተጠያቂዎች እንደሆኑ በመግለጽ ወደ ፊት የከፋ ነገር እንደሚያስከትሉም ዶ/ር ስቴላ ትናገራለች።
እየሱስ ፌስቡክን ሊዘጋው ነው
በዚህ ማክሰኞ ዕለት የዓለም ሚዲያ ትኩረትን ባገኘላት ቪዲዮ ላይ ዶ/ር ስቴላ ከኮቪድ-19 የፈወሰቻቸው ሰዎች ወደ መድረክ እንዲመጡ ስትጠይቃቸው ይታያል።
"እናንተ ካልመሰከራችሁ ሰዎች እኛን ይሰድቡናል" ስትል ፈወስኳቸው የምትላቸውን ሰዎች በኢንተርኔት ራሳቸውን እንዲገልጹ አበረታታለች።
ይህ የእርሷ የትዊተር መልዕክት 27 ሺህ ሰዎች አጋርተውት ሚሊዮኖች ተመልክተውታል።
ዶናልድ ትራምፕ ያጋሩትና እርሷም ከአሜሪካ ፍሮንትላይ ዶክተርስ ከተባለው ቡድን ጋር ሆና የምትታይበትን ቪዲዮ ፌስቡክ ሐሰተኛ ብሎ ካስወገደው በኋላ ዶ/ር ስቴላ ተቆጥታ መጣች። እንዲህም ስትል ተናገረች።
"ፌስቡክ የእኔን ቪዲዮ በአስቸኳይ ወደ ቦታው ካልመለሰ፤ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የፌስቡክን ሰርቨር ድምጥማጡን አጠፋዋለሁ ብሎኛል።"
ነገር ግን ፌስቡክ ቪዲዮዋን መልሶ አልለጠፈውም፤ ሰርቨሩም እስካሁን ምንም አልሆነም።
















