የወባ መድኃኒት የኮቪድ-19 በሽተኞች ከማዳን ይልቅ ለሞት እየዳረገ ነው

የወባ መድኃኒት

የፎቶው ባለመብት, REUTERS

የምስሉ መግለጫ, የወባ መድኃኒት

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የኮሮናቫይረስ በሽተኞች ቢጠቀሙት ይበጃል ያሉት የወባ መድኃኒት በሽታውን ከመከላከል ይልቅ የሞትን ዕድልን እንደሚያሰፋ ተመራማሪዎች ተናገሩ።

ላንሴት የተሰኘው የሕክምና መፅሔት ላይ የወጣው የሳይንቲስቶች ጥናት እንደሚያሳየው የኮቪድ-19 በሽተኞችን በሃይድሮክሲክሎሮኪን ማከም ጉዳት እንጂ ጥቅም የለውም።

ፕሬዝደንት ትራምፕ በሽታው ባይኖርብኝም በሽታው ገሸሽ ለማድረግ የወባ መድኃኒት እየወሰድኩ ነው ማለታቸው አይዘነጋም። ነገር ግን የሕክምና ባለሙያዎች መድኃኒቱን መውሰድ ጥቅም አልባ ከሆኑም በላይ ከልብ ሕመም ሊዳርግ ይችላል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

የወባ መድኃኒቶች ዝናቸው የጎላው ትራምፕ ጠቃሚ ናቸው ካሉ በኋላ ነው።

ሃይድሮክሲክሎሮኪን ለወባ እንዲሁም ሉፐስና አርቲሪትስ የተሰኙትን በሽታዎች ለማከም ይረዳል። ክኒናው የኮሮናቫይረስን ለማከም እንደሚረዳ እስካሁን በጥናት አልተረጋገጠም።

አዲሱ ጥናት 96 ሺህ የኮቪድ-19 ታማሚዎችን ያሳተፈ ነው። 15 ሺህ ያክል ተሳታፊዎች ሃይድሮክሲክሎሮኪን ወይም ክሎሮኪን ተሰጥቷቸዋል። አንዳንዶች መድኃኒቱ ከባክቴሪያ መካለከያ ጋር ሲሰጣቸው ሌሎች ደግሞ ብቻውን እንዲወስዱ ተደረጉ።

ሃይድሮክሲክሎሮኪን የወሰዱ ሰዎች የመሞት ዕድላቸው 18 በመቶ ሲጨምር ክሎሮኪን የወሰዱ ደግሞ 16 በመቶ ጨምሯል። የወባ መድላኒቶችን ከባክቴሪያ መከላከያዎች ጋር ቀላቅለው የወሰዱ ደግሞ የሞመት ዕድላቸው ይበልጥ ከፍ ያለ ነው ተብሏል።

ጥናቱን ያካሄዱት ሰዎች የወባ መድኃኒቶች ለጥናት ካልሆነ በቀር እንዲሁ ማንም እንዳይወስዳቸው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ትራምፕ ምንም እንኳ ኮቪድ-19 ባይዘኝም የወባ መድኃኒት የምወስደው አዎንታዊ ተፅዕኖ ስላለው ነው ይላሉ።

የወባ መድኃኒት ለኮሮናቫይረስ ፍቱን እንደሆነ ለማየት ከ40 ሺህ በላይ የሕክምና ባለሙያዎች የሚሳተፉበት ጥናት እየተካሄደ ነው። ባለሙያዎቹ ከአፍሪካ፣ አውሮፓ፣ እስያና ደቡብ አሜሪካ የተውጣጡ ናቸው። አብዛኛዎቹ ሙያተኞች ከኮቪድ-19 በሽተኞች ጋር ንክኪ የነበራቸው ናቸው።

የዋይት ሃውስ ኮሮናቫይረስ መከላከል አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ዴብራህ ቢርክስ ስለ ጥናቱ ተጠይቀው የአሜሪካ ምግብና መድኃኒት አስተዳዳር የወባ መድላኒቶችን ለኮሮናቫይረስ ስለ መጠቀም በጣም ግልፅ የሆነ መልዕክት አስተላልፏል ብለዋል።

የአሜሪካ ምግብና መድኃኒት አስተዳደር የወባ መድኃኒቶችን ያለ ሐኪም ምክር ጭራሽ አትውሰዱ ይላል።

የዓለም ጤና ድርጅትም መድኃኒቶቹን ለኮሮናቫይረስ መውሰድ ሌላ የጤና እክል ሊያስከትል ይችላል ሲል ያስጠነቅቃል።

ኮሮና