ብሩንዲ መጠጥ ቤቶች በጊዜ እንዲዘጉ አዘዘች

የመጠጥ ጠርሙሶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ብሩንዲ በተወሰኑ ከተሞች የሚገኙ መጠጥ ቤቶች በጊዜ አንዲዘጉ ውሳኔ አስተላለፈች። መጠጥ ቤቶቹ በአገሬው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ ሶስት ሰዓት በኋላ እንዲዘጉ መወሰኑ ተሰምቷል።

ይህ ትዕዛዝ ተፈጻሚ የሚሆንባቸው ከተሞች በዋና ከተማዋ ቡጁንቡራ፣ ጊቲጋና በሰሜናዊ ሙያንጋ አውራጃ መሆኑ ታውቋል።

እስካሁን ድረስ ስለ መዝጊያ ሰዓቱ እንጂ ከስንት ሰዓት ጀምረው መጠጥ መሸጥ እንዳለባቸው የተደነገገ ነገር የለም።

የቡጁንቡራ ከተማ ከንቲባ ውሳኔው ሰዎች በልክ አንዲጠጡ ያለመ ነው ሲሉ ተናግረዋል። ብሩንዲያውያን ጠጪዎች ግን ይህ የመንግሥት ውሳኔ አስቆጥቷቸዋል። ይህ እርምጃ ከጸጥታና ደህንነት ጋር የተያያዘ እንጂ የምንጠጣውን ልክ ከመሥፈር ጋር አይያያዝም ሲሉም ተሰምቷል።

ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በቡጁንቡራ በሚገኝ መጠጥ ቤት ውስጥ በተተኮሰ ጥይት የሰው ሕይወት አልፏል።

በስራ ቀናት መጠጥ ቤቶች ከ11 ሰዓት እስከ 3 ሰዓት ድረስ እንዲሰሩ የተፈቀደ ሲሆን፤ ቅዳሜና እሁድ ግን ከ7 ሰዓት እስከ 3 ሰዓት ድረስ ብቻ ይሰራሉ ተብሏል።

"መጠጥ ቤቶች በጊዜ በራቸውን እንደሚዘጉ መስማት በጣም ያሳዝናል" ሲል ተናግሯል አንድ የጊቴጋ ነዋሪ ለቢቢሲ።

አንዲት የ28 ዓመት ወጣት በበኩሏ "በርካታ ወጣቶች ይህንን ትዕዛዝ በመተላለፋቸው ብቻ ወደ ዘብጥያ ይወርዳሉ ማለት ነው" ስትል ስጋቷን ተናግራለች።

ቡጁምቡራ የሚኖር አንድ ግለሰብ በበኩሉ የቡና ቤት ባለቤቶችና ሰራተኞች መጠጥ ቤቶች እንዲዘጉ የተወሰነበት ሰዓት ጠጪዎች ወደ መጠጥ ቤት የሚመጡበት በመሆኑ ማዘናቸውን ይናገራል።

"በርካታ ሰዎች ቀኑን ሙሉ በስራ የዛለ አእምሯቸውን የሚያፍታቱበት በዚያ ሰዓት ወደ መጠጥ ቤት ጎራ በማለት ነው" በማለትም "በርካታ ሰዎች ወደ መጠጥ ቤት የሚመጡት ለተለያየ ምክንያት ነው፤ ብዙ ጊዜ በሸጋ የግል ምክንያት። በመሪዎቻችን ትዕዛዝ እናምናለን፤ ነገር ግን ይህ ውሳኔ አያስደስተንም፤ የምንፈልገውን በምንፈልገው ሰዓት ለመውሰድ መከልከል አያስደስትም" ብሏል።

አንድ እድሜው በ30ዎቹ የሚገኝ ግለሰብ በበኩሉ ለቢቢሲ እንደሰጠው ቃል፤ የመንግሥት ውሳኔ በዋና ከተማዋ ያለውን የደህንነት ስጋት ያሻሽለዋል ብሎ ስለሚያመንን አንደሚደግፈው ተናግሯል።