የቴክሳሱ የጅምላ ተኳሽ ከሥራ ተሰናብቶ ነበር ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ቅዳሜ ቴክሳስ ውስጥ የጅምላ ተኩስ ከፍቶ የነበረው ግለሰብ "ከሥራ ተባሮ ነበር" ሲሉ የአሜሪካ መገናኛ ብዙሀን ዘገቡ።
ግለሰቡ ተኩስ በከፈተበት ቀን ጠዋት ላይ ከሥራ መሰናበቱን፣ ጥቃት ከማድረሱ አስቀድሞም ለፖሊሶችና ለአገሪቱ የምርመራ ተቋም ኤፍቢአይ ስልክ ደውሎ እንደነበር ተዘግቧል።
ማይክል ገርኪ የተባሉ የፖሊስ ኃላፊ እንዳሉት፤ ግለሰቡ ከሥራ መባረሩን ተከትሎ ተቀጥሮ ይሠራበት የነበረው መሥሪያ ቤት ሰውዬውን በተመለከተ ለአገሪቱ የድንገተኛ አደጋ ጊዜ ደራሾች (911) ደውሎ ነበር።
ክሪስቶፈር ኮምብስ የተባሉት የኤፍቢአይ መርማሪ ደግሞ ተኳሹ ከሥራ ሲሰናበት ወደ 911 ደውሎ እንደነበር አስረድተው "ንግግሩ ግልጽ አልነበረም" ብለዋል።
መርማሪው እንዳሉት፤ ግለሰቡ የጅምላ ተኩስ የከፈተው ከሥራ በመባረሩ ምክንያት አይደለም። "በሥራ ቦታው ላይ ሲገኝም በንዴት ተሞልቶ ነበር" ብለዋል።
ግለሰቡ ባደረሰው ጥቃት ሳቢያ ሰባት ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ፤ 22 ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል። የፖሊስ ኃላፊዎች ተኳሹ ሴት አሮን አተር የተባለ የ36 ዓመት ጎልማሳ መሆኑን ይፋ አድርገዋል።
ጥቃት አድራሹ የጅምላ ተኩስ ከመክፈቱ በፊት ፍሬቻ ሳያበራ መንገድ ሲቀይር ያዩ ፖሊሶች ሊያስቆሙት ሲሞክሩ መተኮስ እንጀመረና ቴክሳስ ውስጥ ወደምትገኘው ኦዴሳ ከተማ መንዳቱ ተነግሯል።
ማንንም ኢላማ ሳያደርግ በአካባቢው ይንቀሳቀሱ የነበሩ ሰዎች ላይ ከተኮሰ በኋላ ራሱን ማጥፋቱም ተገልጿል።
የቴክሳሱ ከንቲባ ግሬግ አበት እንዳሉት፤ ግለሰቡ መሣሪያ ለመግዛት አመልክቶ የነበረ ቢሆንም የቀደመ ታሪኩ ከተጠና በኋላ እንዳይገዛ ተከልክሎ ነበር።
"መሣሪያ ወንጀለኞች እጅ እንዳይገባ ማድረግ አለብን" ብለዋል ከንቲባው።
ከአራት ሳምንት በፊት በቴክሳስ ኤል ፓሶ አንድ ታጣቂ የጅምላ ተኩስ ከፍቶ 22 ሰዎች መግደሉ ይታወሳል።
'ጋን ቫዮለንስ አርካይቭ' የተባለ የጥናት ተቋም እንዳለው ዘንድሮ በጅምላ ተኩስ ሳቢያ 10,000 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።












