የሆንግ ኮንጓ መሪ የተቃዋሚዎችን ድርጊት አወገዙ

የሆን ኮንጓ መሪ ካሪ ላም

የፎቶው ባለመብት, AFP

የሆንግ ኮንጓ መሪ ካሪ ላም የትላንቱን የተቃዋሚዎች ድርጊት አውግዘዋል።

ትላንት ተቃዋሚዎች የሆንግ ኮንግን ሕግ አውጪ ምክር ቤት ጥሰው ገብተው እንዳልነበረ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ትላንት የመብት ተሟጋቾች በአደባባይ እያደረጉ የነበረው ተቃውሞ ተሳታፊ የነበሩ ግለሰቦች ከተቃውሞው ወጥተው ወደ ሕግ አውጪ ምክር ቤት በማምራት ለሰዓታት እቃ ሰባብረዋል።

መሪዋ ተግባሩን "የሚያሳዝንና ብዙዎች ያስደነገጠ" ብለውታል።

ትላንት ሆንግ ኮንግ ከእንግሊዝ አገዛዝ ነጻ ከወጣች በኋላ በቻይን ሥር የወደቀችበትን 22ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ሰላማዊ ተቃውሞ እየተደረገ ነበር።

እለቱ በየዓመቱ የሚታሰበው ስለዴሞክራሲ መስፈን በሚያወሳ ሰልፍ ሲሆን፤ ዘንድሮ ግን በሆንግ ኮነግ የነበረውን የሳምንታት ጠንካራ ተቃውሞ ተከትሎ መጥቷል። ሆንግ ኮንግ ውስጥ ወንጀል የሰሩ ሰዎች ለቻይና ተላልፈው ይሰጡ የሚል ረቂቅ ሕግ መቅረቡን ተከትሎ ሆንግ ኮንግ በተቃውሞ እየተናጠች ትገኛለች።

ትላንት ቀትር ላይ ይደርግ የነበረው ተቃውሞ አካል የነበሩ ጥቂት ሰልፈኞች ተነጥለው ወደ ምክር ቤት አቅንተው ጥቃት ሰንዝረዋል።

የምክር ቤቱን የመስታወት ወለል ሰባብረው ወደ ውስጥ በመዝለቅ፤ የሆንግ ኮንግን ሰንደቅ አላማ አንስተው፤ ግድግዳው ላይ በደማቅ ቀለም መልዕክት አስፍረዋል። የተለያዩ ቁሳቁሶችንም ሰባብረዋል።

ይህን ተከትሎ መሪዋ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ "ተግባሩን ሁላችንም ማውገዝ አለብን። ማህበረሰቡ ወደ ቀደመ ሰላሙ በቅርብ ይመለሳል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ" ብለዋል።

"መሪዋ ለተቃዋሚዎች ጥያቄ ምላሽ ባለመስጠታቸው ተቃዋሚዎች የወሰዱት እርምጃ ነው" በሚል የቀረበባቸውን የሰላ ትችት አጣጥለዋል።

የተቃዋሚዎች ጥያቄ ወንጀለኞች ለቻይና ተላልፈው የሚሰጡበትን ረቂቅ ሕግ ማስቀረት ብቻ ሳይሆን፣ የመብት ተሟጋቾችን ከእስር ማስፈታትና በፖሊስ ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎችን ጉዳይ መመርመርንም ያካትታል።

መሪዋ በበኩላቸው "መንግሥት ለጥያቄዎቹ ምላሽ አልሰጠም መባሉ ትክክል አይደለም። ረቂቅ ሕጉ ሕግ አውጪ ምክር ቤቱ በ2020 ሲከስም አብሮ ይከስማል። ለተጠየቀው ጥያቄ ቀና መልስ ተሰጥቷል" ብለዋል። በተቃዋሚዎቹ ላይ እርምጃ እንደሚወሰድም ገልጸዋል።

ተቃዋሚዎች ረቂቅ ሕጉን አጥብቀው መቃወማቸው መንግሥት ይቅርታ እንዲጠይቅ እንዲሁም ረቂቅ አዋጁን እንዲተወውም አስገድዷል። ነገር ግን ረቂቁ ሙሉ በሙሉ እስኪነሳ ተቃውሞው ይቀጥላል።

ተቃዋሚዎች መሪዋ ከስልጣናቸው እንዲነሱም ግፊት ማድረጋቸወንም ገፍተውበታል።